ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 5 ከትዕይንት 1 እስከ 4) | በማ ድመጥ መማር | DW | 24.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

በማ ድመጥ መማር

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 5 ከትዕይንት 1 እስከ 4)

ወንጀል ተፋላሚዎቹ! አዲስ ተከታታይ ድራማ ጽሑፍ በፌስ ቡክ። በፈጣን የሴራ ፍሰት፥ በአጫጭር ትእይንቶች የተገነባው ድራማ በአይነቱ ለየት ያለ ነው። ይኽ የድራማ ጽሑፍ በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገፅ የሚቀርብ ሲኾን፤ ለሽልማት የሚያበቃ ነው። ስለ ተሳትፎ እና ውድድሩ ፌስቡክ ገጻችን ላይ በዝርዝር ይገኛል።

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 5 ትዕይንት 1)

ባለፈዉ ክፍል ድራማ የወንጀል መርማሪው ዓለሙ ቤቲን ለጥያቄ አቅርቧት ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግድያ ከተፈጸመበት ጳዉሎስ ጋር የፍቅር ግንኙነት ስለነበራት ነው፡፡ ነገር ግን በግድያው የተሳተፈች መሆኗን የሚያሳይ ማስረጃ እስካሁን አልተገኘም፡፡ ስለሆነም  መርማሪ ዓለሙ ቤቲን በነፃ አሰናብቷታል። የቤቲ የፍቅረኛ የሆነው ሙሳ ግን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመጣ ተደርጓል፤የተጠረጠረበት ጉዳይ ደግሞ በቅናት ተነሳስቶ ገድሎት ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ «ሚስተር ጂ»ንስ አስታወሳችሁ? አውሮፕላን ጣቢያ ለበረራ የተዘጋጀ የውጭ ወኪል ለ«ሚስተር ጂ» ይደውላል።

«ሄሎ ሚ/ር ዕቃው ደርሷል!»

ሚስተር ጂ (በስልክ በሹክሹክታ)   «አገሬን  ጠንቅቄ ስለማውቃት ፤ በኔ ጣለው ብዬህ ነበር እኮ።  ትንሽ ስኳር  ብጤ ማላስ ብቻ ነው የሚጠበቅብህ! »

የውጭ ወኪሉ (ኮስተር ብሎ)  «ሚ/ር ጂ የዕቃው መጠን ማነሱ ኪሳራ ውስጥ ስለጣለን ትንሽ ቅር ብሎናል። ለወደፊቱ  አቅርቦታችሁን መጨመር ይኖርባችኋል።»

«በርከት አድርገን ለማቅረብ እንሞክራለን። ያው ግን እንደበፊቱ በገፍ መጠበቅ አይኖርባችሁም።  መንግሥት ከፍተኛ ጫና እየፈጠረብን ነው፡፡ ለነገሩ ዝሆኖቹንም አድነን እየጨረስናቸው ነው!»

«ስሚ!  ዋና የዝሆን ጥርስ አቅራቢ እንደመሆንሽ  ሁኔታዎችን ማስተካከል ያቅትሻል ብዬ አልገምትም። በዛም አለ በዚህ ግን   ከጨዋታ ውጪ ልናደርግሽ እንደምንችልም አትዘንጊ።»

«ልታስፈራራኝማ አትሞክር! ባልከው መንገድ እኛም አጸፋውን መመለስ አያቅተንም እኮ!»

«ለማንኛው ቁጭ ብለን በርጋታ መነጋገር ይኖርብናል። አይመስልሽም?» (ስልኩ ይቋረጣል የውጭ ወኪሉ ለራሱ ያወራል) «እኛ  እንደሆነ ወዳጄ አውሮፕላናችን ውስጥ ተሳፍረናል!»

ምንም እንኳን ሻንጣዎቹን የሞሉት ሕገ-ወጥ ነገሮች ቢሆኑም፤ የውጭ ወኪሉ ማንም ሳይጠረጥረው  በረራውን ጀምሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ዓለሙ በጳውሎስ አሰቃቂ ግድያ ውስጥ የሙሳ እጅ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሙሳን በመመርመር ላይ ነው።

***

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 5 ትዕይንት 2)

የምርመራ ክፍል ውስጥ ሙሳ በጠረጴዛው ማዕዘን በኩል ግራ ተጋብቶ ተቀምጧል። ከውጭ የእግር ኮቴ ይሰማና መርማሪ ዓለሙ ይገባል። የያዘውን ዶሴ ጠረጴዛው ላይ ይወረውራል።

«ይኽ ሁሉ ምንድነው መርማሪ? ፍቅረኛዬ ቤቲስ የት ነው ያለችው?»

«ጓደኛህ ቤቲ ደህና ነች።  ይልቅ አንተ ባለፈው በ15 ማታ የት ነበርክ?»

«ሥራ ላይ ነኛ!»

«የት?»

«እንዴ! በቦቩ ደን ዉስጥ ፎቶግራፍ እያነሳሁ ነበራ።»

«ጫካው ውስጥ ያየኽ ሰው አለ ወይንስ ብቻህን ነበርክ? የጳውሎስ ግድያን በተመለከተ ምርመራ እያደረግን ነው።»

«ሆ...! እናንተ ሰዎች ለምንድን ነው ጊዜዬን የምታባክኑብኝ! እኔ ጳዉሎስን እንደማላውቀው ፥ከግድያውም ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደሌለኝ ደጋግሜ ነግሬያችኋለሁ።»

«ስለ ጳዉሎስ ግድያ ምንም አታውቅ አይደል?!»

«ምን ለማለት ፈልገህ ነው? የማለውቀውን ሰው እንዴት እገድላለሁ?

« እንደውም ለምን እቅጩን አልነግርህም?! ፍቅረኛህ  ቤቲ ከጳዉሎስ ጋር እንደምትማግጥ ደረስክባት እና ደረቱ ላይ ያን ሳንጃ ሻጥክበት!»

(ግራ በመጋባትና በመደነቅ) «ቤቲ እንደምትማግጥ?! ቤቲማ አትማግጥም!»

«እሱን ለእኛ ተወው። አሁን መሄድ ትችላለህ። ተጨማሪ ጥያቄዎች ሲኖሩን ግን እንጠራሀለን። ለማንኛውም ስንፈልግህ እንዳናጣህ።»

***

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 5 ትዕይንት 3)

የእንስሳት መብት ተከራካሪዋ ዶ/ር ሰናይት ለድምፅ አልባዎች መከራከር ከምንም በላይ የሚያስደስታቸው ነገር ነው። በአሁኑ ሰአትም በዋናው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተገኝተው ስለ እንስሳት መብት በመከራከር ላይ ናቸው። የውይይቱ መሪ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል።

«ዉይይታችንን ለመጀመር ያኽል፤ / ሰናይት ዝኆኖች በጣም አስፈላጊ ናቸው የሚሉት ለምንድነው? እርስዎስ እንስሳቱን ከጥቃት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉትስ ለምንድነው

«ዝኆኖች በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ይፈጽማሉ። ለምሳሌዛፎችን ይገነድሳሉ። መቼም እንደጥፋት ይቆጠራል አይደል

«እህ

«ይህ ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው! እነዚህ እንስሳት ይኽን በሚያደርጉበት ወቅት ለሌሎች እንስሳት የሚሆን የግጦሽ መስክ በማመቻቸት እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ዝኆኖች ሌሎች እንስሳት ጥማቸውን ሊቆርጡበት የሚችሉትን ውሃ ማቆር የሚችሉ ጉድጓዶችንም ይቆፍራሉ። ስለሆነም ብዝኃ ሕይወት ሚዛንን ለመጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ይፈጽማሉ ማለት ነው።»

በቲቪ የሚሰራጨው ማብራሪያ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ለሕገ-ወጥ አዳኞቹ ቁብም አልሰጣቸው! አሁንም ዝኆኖችን በማደን ላይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፀረ ሕገ ወጥ አደን መርማሪ ፖሊስ ከበደ እና ባልደረቦቹ የሕገ-ወጦቹን ዱካ በማነፍነፍ ላይ ናቸው።

***

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 5 ትዕይንት 4)

ጥቅጥቅ ባለው ጫካ ውስጥ የበርካታ ሰዎች የእግር ዳና ይሰማል። የፀረ ሕገ-ወጥ አደን መርማሪ ፖሊስ ከበደና ባልደረቦቹ የሕገወጦቹን ዱካ በማነፍነፍ ላይ ናቸው። ከበደ ባልደረቦቹን ያስጠነቅቃል።

«ቀስ! እነዚህን ጭራሮዎች እንዳትረግጧቸው፤ ተጠንቀቁ ጎበዝ! ሕገ-ወጥ አዳኞቹ ኮሽታ ከሰሙ ሊፈረጥጡ ይችላሉ፤ በዛ ላይ ጦር መሣሪያ ታጥቀዋል።»

ከርቀት ጥድፊያ የተሞላበት ሹክሹክታ ይሰማል።

«ኧረ አለቃ! እዚህ ጋር ተመልከት የሆነ ነገር አለ። ተመልከተው!»

«ምንድን ነው?»

«የዝኆን ጥርስ፤ በጣም ብዙ የዝኆን ጥርስ!»

«ያንት ያለህ! ይኼ ሁሉ የዝኆን ጥርስ!?»

«ሽሽሽ! የሆነ ሰው እየመጣ ነው!»

ሁለት ሰዎች ጭራሮዎቹ ላይ በጥድፊያ ሲራመዱ ይሰማል። እየቀረቡ ነው። ጭንቀት በተሞላበት ድምፀት ያወራሉ።

«በቃ እዚህ ጋር እናድፍጥ!»

«ወይኔ! ዛሬ፤ እነዚያ ዝኆኖች ካመለጡን በቃ አከተመልን! ሚ/ር ጂ ጠብሶ ነው የሚበላን! ኧረ! ቆይ ቆይ!»

«ምንድን ነው ምን ሰማህ?»

«እሽ! መሣሪያህን ወድር!» ጦር መሣሪያ ይቀባበላል። ሁለቱ ሕገ-ወጥ አዳኞች ይሮጣሉ። ተደጋግሞ ይተኮሳል። አንደኛው በጥይት ተመትቶ ይወድቃል። ይጮሃል። እግሩን ነው የተመታው።

«ተገኝተዋል! ሁሉንም በእጀሙቅ ጠፍርልኝ! ዝኆኖቹን ስትጨፈጭፉ ብትከርሙም፤ ዛሬ ግን ቀኑ ጨምልሞባችኋል።» እነዚህ ወንጀለኞች ፖሊሶቹን ወደ ሚ/ር ጂ መርተው ይጠቁሙ ይሆን?

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር1 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ሁለተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 2 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ሦስተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 3 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን አራተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 4 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 6 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 7 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 8 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

ጀምስ ሙሃንዶ

ማንተጋፍቶት ስለሺ