ሕይወት ያጠፋዉ የባሌ ደን እሳት | ጤና እና አካባቢ | DW | 17.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ሕይወት ያጠፋዉ የባሌ ደን እሳት

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሮን ለማድነቅ፤ በሌሎች አካባቢ የማይገኙ አዕዋፍና የዱር እንስሳትን ለመመልከትና ተራሮችን የመዉጣት ፍቅር ያላቸዉን ቱሪስቶች በመሳብ ይታወቃል። በበጋ ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት ቃጠሎ እየተነሳ ጉዳት ማድረሱ ይደጋገማል። በንብረትና በተፈጥሮ ሀብት ላይም ቀላል የማይባል ችግር ሲያስከትል ይሰተዋላል።

በበጋ ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት ቃጠሎ እየተነሳ ጉዳት ማድረሱ ይደጋገማል። በንብረትና በተፈጥሮ ሀብት ላይም ቀላል የማይባል ችግር ሲያስከትል ይሰተዋላል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ የባሌ ተራሮች አካባቢ የተከሰተዉ የእሳት አደጋ ግን ለአካባቢ ተፈጥሮ የምትቆረቆር ሕይወትንም አልማረም። ከሌላ አንፃር እሳቱ ያደረሰዉ የጉዳት መጠን ገና እየተጠና ነዉ ቢባልም ምንም ዋጋ ቢከፈል መልሶ የማይተካ ዉድ የሰዉ ሕይወት ግን ላይመልስ ነጥቋል።

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሮን ለማድነቅ፤ በሌሎች አካባቢ የማይገኙ አዕዋፍና የዱር እንስሳትን ለመመልከትና ተራሮችን የመዉጣት ፍቅር ያላቸዉን ቱሪስቶች በመሳብ ይታወቃል።

ከብዙ በጥቂቱ የምኒልክ ድኩላ፤ ኒያላ፤ የባሌ ጦጣዎችና ሌሎችም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የዱር እንስሳት የባሌ ብሔራዊ ፓርክና አካባቢዉን መኖሪያቸዉ አድርገዉ ይገኛሉ። የብዝሃሕይወት ስብጥር ያበለፀገዉ ይህ አካባቢ ሰሞኑን የእሳት አደጋ እንደገጠመዉ ተሰምቷል። ወደስፍራዉ በመሄድ ሁኔታዉን ተመልክተዉ የተመለሱት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ዘዉዴ አሁን እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን ይገልጻሉ።

ቃጠሎዉ ወደነበረበትአካባቢዉ ደዉለን ያነጋገርናቸዉ የባሌ ብሔራዊ ፓርክ ሠራተኛ መሆናቸዉን የገለፁልን አቶ አስቻለዉ ጋሻዉ፤ በተራራዉ ዙሪያ ለተነሳዉ እሳት ምክንያት ነዉ ተብሎ የሚገመተዉ ሠዉ ሠራሽ መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ያመለክታሉ። እንዲያም ሆኖ መንስኤዉን ለማጣራትና እጃቸዉ ሳይኖርበት አልቀረም የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ የአካባቢዉ ፖሊስ የማጣራት ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዉናል።

በዚህ ስፍራ ከየካቲት 24 ቀን ጀምሮ እንደተነሳ የተሰማዉ እሳት ጉዳቱ በአካባቢ ተፈጥሮዉ ላይ ብቻ ሳይገታ ተፈጥሮን በማድነቅና በመንከባከብ የምትታወቅ የወጣት ባለሙያን ነፍስም ማጥፋቱ የብዙዎች መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

Landschaft in Äthiopien

የማኅበረሰብ ቱሪዝም ባለሙያ ነዉ። ጊዜና ሕይወቱን ተፈጥሮን በማድነቅና የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መኖሩን በቅርብ የሚያዉቁት ይናገሩለታል። በመናገር ብቻ ሳይሆን በተግባርም የአካባቢ ተፈጥሮ ወዳጅነቱን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ባከናወናቸዉ ተግባራት ተከታዮችም አፍርቷል። የ33ዓመቱ ወጣት ብንያም አድማሱ አስታ የተባለዉ ተክል በእሳት እየነደደ እሳቱም ወደሌላ አካባቢ እንዳይስፋፋ ጥረት እያደረጉ ከነበሩ ወገኖች ጋ ሆኖ የሚመለከተዉን ለሚቀርበዉ ሰዉ ደዉሎ እንዲህ አዋይቶ ነበር። ሄኖክ ስዩም አደጋዉ ከመድረሱ ከቀናት በፊት በስልክ አግኝቶታል።

በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የተነሳዉ የእሳት ቃጠሎ አሁን በቁጥጥር ሥር መዋሉ መልካም ዜና ቢሆንም ለእሳቱ መነሻ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የሚጠረጠረዉ የከብቶች መኖ የሆነዉን ተክል የማቃጠል ልማድ ሌላ መፍትሄ እንዳለዉ ባለሙያዎች ቢመረምሩት መልካም ይሆናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic