1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕዝባዊ ስብሰባዎች በትግራይ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

"ህዝብ ያላመነባቸው፣ ህዝብ ልያገለግሉ እየተገባቸው ህዝብ እንዲያገለግላቸው የሚጠብቁ፣ በህዝብ ሀብት እና ግዜ የሚቀልዱ ሌላ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም። ከላይ በዞን ደረጃ የሚያስፈልገው ማስተካከል መደረግ አለበት፣ ከታች ደግሞ ይህ የማይሆንበት ነገር የለም።" አቶ ጌታቸው ረዳ

https://p.dw.com/p/4kERx
 Meeting on Current Affairs in Tigray 03.08.2024
ምስል Million Haileslasse/DW

የትግራይ ጊዚያዊ መስተዳደርና የሕዝብ ጥያቄዎች

በህወሓቱ ጉባኤ ከፓርቲው "እንደታገዱ" የተነገረላቸው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ወደ ተለያዩ የትግራይ ከተሞች በመጓዝ "ህዝባዊ ውይይቶች" እያደረጉ ነው። በቅርቡ በዓብይዓዲ፣ ዛሬ ደግሞ በዓዲግራት ከተማ ውይይቶች አድርገዋል። በእነ ዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት በበኩሉ የግዚያዊ አስተዳደሩ የሹምሽር እርምጃዎች እየተቃወመ ይገኛል። በሌላ በኩል በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ የህወሓት የውስጠ ፓርቲ ፍጥጫ ለትግራይ አደጋዎች ይዞ የሚመጣ በማለት ሁኔታው አውግዟል።

በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈልተከትሎ፥ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሰሞኑን ወደ የተለያዩ የትግራይ ከተሞች እየተዘዋወሩ ህዝባዊ ስብሰባዎች በማድረግ እንዲሁም በዓላት ላይ መታደምና ንግግሮች በማሰማት ላይ ተጠምደዋል። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በዓብይ ዓዲ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ያደረጉት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ለሳቸው ድጋፍ ያሳየ የተባለ አቀባበልም በከተማይቱ ተስተውሏል። በአክሱም እንዲሁ አቶ ጌታቸው ረዳ እና የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን የታደሙበት ስነስርዓቶች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተካሄደ ሲሆን፥ ዛሬም ይህ ቀጥሎ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በዓዲግራት በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው የተገኙበት የጎዳና ትእይንት እና ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዷል። ይህ እየሆነ ያለው ጉባኤ ያደረገው ህወሓት እነ ጌታቸው ረዳን ባገደበት፥ ግዚያዊ አስተዳደሩን የሚመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮችን ከዞን አስተዳዳሪነት እያነሱ በሌሎች እየተኩ ባሉበት አጋጣሚ ነው።

በዓብይ ዓዲ በነበረ ህዝባዊ ስብሰባ የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ የሚጠበቅባቸው ሐላፊነት የማይወጡ ያሏቸውን እንዲሁም ህዝብን ያማረሩ አመራሮች እንደሚቀይሩ ለተሰብሳቢዎች ተናግረዋል። "ህዝብ ያላመነባቸው፣ ህዝብ ልያገለግሉ እየተገባቸው ህዝብ እንዲያገለግላቸው የሚጠብቁ፣ በህዝብ ሀብት እና ግዜ የሚቀልዱ ሌላ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም። ከላይ በዞን ደረጃ የሚያስፈልገው ማስተካከል መደረግ አለበት፣ ከታች ደግሞ ይህ የማይሆንበት ነገር የለም። እዚህ ላይ ግልፅ መሆን አለብን" ብለዋል።

የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)ምስል Million Haileselassie/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ በቀጣይ በግዚያዊ አስተዳደሩ ያለው የስልጣን ድርሻ እንደሚጠይቅ አስቀድሞ የገለፀውህወሓት፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ እየወሰደው ባለ እርምጃ ቅሬታውን ገልጿል። በሌላ በኩል በአክሱም ከሃይማኖት መሪዎች እና የሃገር ሽማግሌዎች የተገናኙት የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ ከሌላው የህወሓት ክፍል ጋር አንድ ሁናችሁ ስሩ የሚል ሐሳብ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተደምጠዋል።

 "እውነቱ ማወቅም ጥሩ ነው። ዝም ብሎ 'አንድ ሁኑ' የሚል ብቻ ተዉት። አንድ መሆን የሚቻል ከሆነ ብቻ ነው አንድ የሚኮነው። ካልሆነ ስራችሁ በሰላም ስሩ ነው መባል ያለበት። አይደለም አንድ ፓርቲ ውስጥ የቆየን ይቅርና፥ ትግራይ ለሁሉም መሆን የምትችል ናት፣ ከሌላም ጋር መስራት መቻል አለብን" ብለዋል።

የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በሚያካሂዷቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች፥ ከህወሓት ጉባኤ ራሳቸው ካገለሉ የፓርቲው አመራሮች በተጨማሪ በግዚያዊ አስተዳደሩ በምክትል ፕሬዝደንት መዓርግ የያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ዘርፍ ሐላፊ ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ እየተሳተፉ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ የህወሓት የውስጠ ፓርቲ ፍጥጫ ለትግራይ አደጋዎች ይዞ የሚመጣ በማለት ሁኔታው አውግዞታል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ