ሕወሓት ኢሕአዴግን በብርቱ ወቀሰ | ኢትዮጵያ | DW | 13.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ሕወሓት ኢሕአዴግን በብርቱ ወቀሰ

ሕወሓት "የኢሕአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ" መኮላሸት ኢትዮጵያን ለቀውስ እንደዳረጋት አስታወቀ። ፓርቲው "ሀላፊነት የተሸከመው አመራር ኢሕአዴግ ከሚታወቅበትና ከሚለይበት መሰረታዊ እምነቶች ያፈነገጠ፣ የአገሪቱ እውነታ ወደ ጎን በመተው ቅጥ ባጣ ደባል አመለካከት የተበረዘ" ነው ብሏል። የኢሕአዴግ ውኅደት እንደማይሳካም አስጠንቅቋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:23

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ

ከመጋቢት 30 ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 3/ 2011 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ሲያደርገው የነበረው መደበኛ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ የወጣው የፓርቲው የፅሑፍ መግለጫ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እንዲሁም አካባቢያዊ ጉዳዮች የዳሰሰ ነበር።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ በመደበኛ ስብሰባው በዝርዝር ካያቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ሁኔታ የሚመለከት እንደነበረ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ የተሰጠው መግለጫ ያመለክታል፡፡ የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አጋጣሚዎች ከግዜ ወደ ግዜ እየተበራከቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ተደርሷል ያለው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ፣ በሀገር ደረጃ ኢህአዴግ የጀመረው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ሳይሳካ መቅረቱ አትቷል፡፡

ሀገር የሚበትን ተግባር እንዲፈፀም፣ የህዝቦች ስቃይና መከራ እንዲቀጥል አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ሀይሎች ዕድል እንዲያገኙ ያደረገው የኢህአዴግ ድክመትና የአመራሩ ክፍተት መሆኑ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ እየተነሳ ስላለው ግንባሩ ወደ አንድ ውሁድ ፓርቲ የማሸጋገር ተግባር አቋሙ የገለፀው ህወሓት፣ ኢህአዴግ አንድ ውሁድ ፓርቲ የማድረግ እንቅስቃሴ በየጊዜው ሲነሳ የቆየና በጥናት ላይ መሰረት ተደርጎ እንዲመለስ አቅጣጫ ተሰጥቶ የነበረ መሆኑ በማስታወስ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች በመሰረታዊ ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂ፣ አመለካከትና እምነት አንድ  ጥምር እይታ በሌለበት ወደ አንድ ጥምር ፓርቲ መሸጋገሩ የሚታሰብ አይደለም ሲል መግለጫው አብራርቷል፡፡

በሕገ መንግስት ጉዳዮች ዙርያ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው ሕገ መንግስት ሲመችህ የምታከብረው፣ ሳይመችህ ሲቀር የምትጥሰው አይደለም ያለ ሲሆን ሕገ መንግስቱ በማንኛውም ግዜና ሁኔታ ሊከበር ይገባዋል ሲል ገልፅዋል፡፡ ቀጣይ ዓመት ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ በግዜው ስለመፈፀሙ ከሕገመንግስታዊ ስርዓት ውጭ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አግባብነት የጎደለው ነው ሲል የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

ከሀገራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ስለትግራይ ክልል የወጣቶች ስራ አጥነት፣ የከተማና ገጠር መሬት፣ ካሳና ተዛማጅ አጀንዳዎች የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ መክሮ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጡ ገልፅዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ አንድነት ሊሸረሽሩ እየሰሩ ነው ያላቸው ሃይላት ያወገዘው መግለጫው የህዝብ ድህንነትና ህልውና ጉዳይ ለገበያ ማቅረብ ታሪካዊ ስህተት ብሎታል፡፡

ሚሊዮን ሐይለስላሴ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic