ሕንድና ፓኪስታን ነፃነትና ጦርነት | ዓለም | DW | 14.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሕንድና ፓኪስታን ነፃነትና ጦርነት

ሳዳር ፓታል የተባሉ ፖለቲከኛ ነፃነት ከመታወጁ አንድ ሳምንት በፊት ባደረጉት ንግግር «ብሪታንያዎች የክፍፍሉ ምክንያት የሒንዱ እና የሙስሊሞች ጠብ ነዉ ይላሉ ግን በሁለቱ ትከሻ ላይ ሸክሙን የጫነዉ ማነዉ? እስከ እኔ ብሪታንያን ላንድ ሳምንት እንድገዛ ፍቀዱልኝ።ኢንግላንድ፤ዌልስ ስኮትላንድ ለዝንተ ዓለም የሚጋጩበትን ጠብ መፍጠር እችላለሁ።»አሉ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:35 ደቂቃ

ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ነፃነት እና ክፍፍል

ነሐሴ 14 1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)፤ ደልሒ።«ዛሬ እከለ ሌት ዓለም ሲተኛ ሕንድ የነፃነት ብርሐን ለመፈንጠቅ ትነቃለች።» የመጀመሪያዉ የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጀዋሐራል ኔሕሩ።በርግጥም ነፃነት ነዉ።ግን ክፍፍል።ካራቺ፤ «ሒንዱስታን እና ፓኪስታን ዉስጥ የሚመሰረቱት የተረጋጉና ዘላቂ መንግሥታት እንደ ወዳጅና ጎረቤት፤እንደ ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ በመተባበር እንደሚኖሩ ተስፋ አለኝ።»

የመጀመሪያዉ የፓኪስታን መሪ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ።ተስፋ፤ ግን ጥፋት።ደስታ።ሰባ ዓመት የዘለቀ ነፃነት፤ ሰባ ዓመት የደፈነ ክፍፍል፤ ሰባ ዓመት ያልበረደ ጠብ።የሁለቱ ሐገሮች ወግ።ላፍታ እንዘክረዉ።

የቬኒሲያዉ ነጋዴና አገር አሳሽ ማርኮ ፖሎ የምሥራቁን ሐብት፤ ባሕል እና ፖለቲካዊ አስተዳደር ለምዕራቡ ካስተዋወቀበት ከሺሕ ሁለት መቶዎቹ ማብቂያ ጀምሮ አዉሮጶች ያንን ቅመም-አትክልት የሚታፈስ፤ ማዕድን የሚዛቅ፤ ሐር-ጥጥ የሚጋዝበትን ሰፊ ንዑስ ክፍለ ዓለመ ለመቆጣጠር እንደቋመጡ ነበር።ከምሥራቅ ይልቅ

ደቡብ አሜሪካ ላይ አገዛዛቸዉን የተከሉት የስጳኝና የፖርቱጋል ጠንካራ ክንድ እየዛለ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ጡንቻ ባበጠበት ዘመን የለንደን-ፓሪስ ገዢዎች የቆየ ምኞታቸዉን ገቢር ለማድረግ ወደ ምሥራቅ ሲያማትሩ በቀላሉ የማይጋፉት ጠንካራ ሐይል መኖሩን ተረዱ።

ከ1526 ጀምሮ ርዕሰ-መንበሩን ከአግራ፤ ፋቴፑር ሲኪሪ፤ ከሻሐጃናባድ፤ ደልሒ እየቀያየረ እስከ አፍቃኒስታን የተዘረጋዉን ሰፊ ምድር የሚገዛዉ የሙስሊሞቹ የሙግሐል ሥርወ-መንግሥት፤ ቀንድ፤ጥፍር ጥርሳቸዉ በቅጡ ላልደረጀዉ አዉሮጶች የሚደፈር አልነበረም።

ይሁንና ጠንካራዉን የሙስሊሞች ሥርወ-መንግሥት ሰርስረዉ የሚገቡ፤ገዝግዘዉ የሚጥሉበት ብልሐት፤ ተንኮልና ትዕግስት ሞልቶ ተርፏቸዉ ነበር።ፖርቱጋሎች፤ ፈረንሳዮች፤ ሮሞች በንግዱም፤ በክርስትና ሰበካዉም፤በጉብኝት፤ በመደለያ ስጦታዉም ብለዉ እዚያ ምድር እግራቸዉ ለመትከል ይፍረመረሙ ገቡ።እንደ ብሪታንያዎች የተሳካለት ግን አልነበረም።

በ1600 የጆን ኩባንያ ብለዉ የመሠረቱትን  ኩባንያ በ17መቶዎቹ አጋማሽ፤ «የምሥራቅ ሕንድ ኩባንያ» በሚል አዲስ ሥም አደራጅተዉ ወደዚያ ትልቅ ግዛት አዘመቱት።ጥጥ፤ሐር፤ጨዉ፤ ሽይ ቅጠልን የመሳሰሉ

ትናንሽ የፍጆታ ምርቶችን መነገድ የጀመረዉ ትንሽ ኩባንያ የአዉሮጳ ተቀናቃኞቹን እየፈነገለ፤ የትልቁን ክፍለ ዓለም ትላልቅ ገዢዎች እያታለለ፤ እየሰለለ፤ ሕዝቡን እየከፋፈለ በመቶኛ ዓመቱ ተልዕኮዉን ከግብ አደረሰ።ብሪታንያዎች ራጅ ያሉት የንዕስ ክፍለ-ዓለሙ አገዛዝ  በቀጥታ በለንደን ነገስታት እጅ ወደቀ።1858።

                   

የብሪታንያን ቅኝ አገዛዝ ለመቃወም ቀድመዉ ያመፁት የገዢነቱ ሥልጣን በአዉሮጶች ተወሰደብን የሚሉት ሙስሊሞች ነበሩ።ፀረ-ቅኝ ግዛቱን ትግል የሚመራ እና የሚያስተባብር የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረቱት ግን ሒንዱዎች ናቸዉ።በ1885 ቦምቦይ ወይም ሙባይ የተመሠረተዉ የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ የተባለዉ የፖለቲካ ፓርቲ መላዉን ሕንዳዊ እንደሚወክል መሥራቾቹ መፃፍ-መናገራቸዉ አልቀረም።

ከ73 የፓርቲዉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት 54ቱ ግን የሒንዱ እምነት ተከታዮች ናቸዉ።በያኔዋ ሕንድ ብዙ ቁጥር ይዘዉ ከነበሩት ሙስሊሞች ለፓርቲዉ ከፍተኛ ሥልጣን የበቁት ሁለት ብቻ ነበሩ።እኩል ቅኝ በሚገዙት፤ እኩል መታገል በሚፈልጉት ወይም እንፈልጋለት በሚሉት የሐገራቸዉ ልጆች የተገለሉ የመሰላቸዉ ሙስሊሞች ቅሬታቸዉን አልሸሸጉም።

 

በ1906 ዳሐክ-ባንግላዴሽ ዉስጥ ሙስሊም-ሊግ ያሉትን የፖለቲካ ማሕበር መሠረቱ።የፓርቲዉ መስራችና ኋላ የመጀመሪያዉ የፓኪስታን መሪ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ እንዳሉት ግን ፓርቲያቸዉ ሙስሊሙ የሚያደርገዉን ትግል ከማስተባበር ባለፍ ትልቁን ግዛት የመከፋፈል ሐሳብ አልነበረዉም።

የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በየሥፍራዉ እንደሚያደርጉት ሁሉ ደከም ያለዉን ደገፍ፤ ጠንከር ያለዉን ኮርኮም እያደረጉ የሁለቱን

ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ወደ ጠብ፤ የሁለቱን ኃይማኖት ተከታዮች ወደ ግጭት ይገፏቸዉ ያዙ።ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የሚደረጉ ፀረ ቅኝ አገዛዝ አመፅ፤ አድማ፤ሰልፎች ሁሉ ፈራቸዉን እየለቀቁ በሙስሊም-ሒንዱዎች ጠብና ግጭት ያሳርግ ገባ።

መሐመድ ዓሊ ጂናሕ፤ መሐተመ ጋንዲ እና ጀዋሐራል ኔሕሩ በተደጋጋሚ ያደረጉት ድርድር ዉይይትም አንድነትን ለመጠበቅ የተከረዉ የለም።መሐመድ ዓሊ ጂናሕ ካንድነት ወዲያ ያለዉን አማራጭ ግልፅ አደረጉ።

                                   

«በሰፊዉ የሕንድ ንዑስ-ክፍለ ግዛት ከሚኖሩት በርካታ ጎሳና ኃይማኖች መሐል ሁለት ዋና ዋና ብሔሮች አሉ።ሒንዱ እና ሙስሊም።በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች አናሳ ሊባሉ አይችሉም።በሕንድ ምዕራባዊና ምሥራቃዊ ቀጠና ብቻ ያለነዉ ከሰባ ሚሊዮን እንበልጣለን።በነዚሕ አካባቢዎች ከሚኖሩት ሒንዶዎች ጋር ሲነፃፀር ቁጥራችን ከሰባ ከመቶ ይበልጣል።ሕንድ በሂንዱስታንና ፓኪስታን ለሁለት እንዲከፈሉ እንፈልጋለን። ለሒንዱዎችም ለሙስሊሞቹም ነፃነትን የሚያረጋግጠዉ ይሕ ብቻ ነዉ።»

በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ልጅ-አባት- ባል ዘመዱን ያጣዉ፤ ሐብት ንብረቱ የወደመበት የብሪታንያ ሕዝብ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችልን እንደ ድል አድራጊ  ጀግና ማድነቅ፤ማወደስ-ማሞገሱ አልቀረም።በ1945 በተደረገዉ ምርጫ ግን ቸርችልና  ፓርቲያቸዉን አልመረጠም።በምርጫዉ ያሸነፈዉ የሌበር ፓርቲ መሪ ክሌመንት አትሌ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን እንደያዙ ሕንዶች ነፃ እንዲወጡ ወሰነ።1947።የነፃነት ደንብ የተባለዉን ሕግ ንጉስ ጆርጅ አራተኛ ለማፅደቅ ጊዜ አልፈጁም።

የሕንድ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ሕጉ ከመፅደቁ በፊት የጀመሩትን ድርድር እና ዉይይት አላቋረጡም።ግንቦት 1947።

                                 

«አንድነቷን የጠበቀች ሕንድን ለመመሥረት የተደረገዉ ሙከራ ከሸፈ።ጋንዲ እራሳቸዉን ከፖለቲካ አገለሉ።የሙስሊም ሊግ መሪ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ እና የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ ጀዋሐራል ኔሕሩ ሕንድን ለመክፈል ተስማሙ።»

ሁለቱ ዋና ዋና ፖለቲከኞች ከብሪታንያ አገረ ገዢ ሎርድ አድሚራል ሉዊስ ሞሰንትባት ጋር ሆነዉ ነፃነቱም ክፍፍሉም አንድ ቀን እንዲሆን ወሰኑ።ነሐሴ 14 1947።ደረሰ።ተባለም።

                                

«በታሪክ ብዙም የማይታይ አጋጣሚ ነዉ።አረጌዉን አልፈን ወደ አዲሱ እንሸጋገራለን። አዲሲቱን ሐገራችንን እንረከባለን።ለረጅም ጊዜ የተጨቆነችዉ ሐገር በስተመጨረሻዉ ትንሳኤ ታገኛለች።»የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጀዋሕራል ኔሕሩ።ካራቺ ላይም ተመሳሳይ አዋጅ፤ ደስታ ፌስታ ነበር።ፑንጃብ ግን በእሳት ትጋይ ጀመር።ቃሲም መሐመድ ከዕልቂቱ ከተረፉት አንዱ ነበር።

                                    

«ነሐሴ አስራ አምስት ነፃነት ሆነ።የማቃጠል፤ የመዝረፍ እና የመግደል ነፃነት።ደልሒ እና ካራቺ በደስታ ሲፈነድቁ፤ ማዕከላዊ ፑንጃብ ትጋይ ነበር።»

ግድያ፤ ዘረፋ፤ስደቱ በፑንጃብ አልተገታም።ስድስት ሚሊዮን ሙስሊሞች ከዛሬዋ ሕንድ ወደ ዛሬዎቹ ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ተሰደዱ።አራት ሚሊዮን የሚበልጥ ሒንዱ ከፓኪስታንና ከባንግላዴሽ ወደ ሕንድ ፈለሰ።ጓዝ ለመስበስብ ጊዜ አልነበረም።ሙስሊም-ከሕንድ፤ ሒንዱ ከፓኪስታን ቅሌን ጨርቄን ሳይል እየተግተለተለ ተሰደደ።አንድ ሚሊዮን አለቀ።

ጋንዲ ከ1914 ጀምሮ ሠላማዊ የነፃነት ትግልን ሠብከዋል።የትግል ሥልታቸዉ አብነት በመላዉ ዓለም ናኝቷል።ወገናቸዉን ግን አልተቀበላቸዉም።ተከፋፋለ፤ ተላለቀ፤ ተሰደደ።

                               

«ብዙ ጥፋት ደርሶብናል።ብዙ ተፈትነናል።ጠንካራ ትግል አድርገናል።ይሕ ሁሉ ትግል ፈተና ከዝናቡ ወደ ጎርፉ ለመግባት ነበር።ይሕ እዉነት አይደለም።የተለያየ ኃይማኖት ተከታዮች ነን።ግን ሁላችንም ወንድማማቾች ነን።ወንድማማቾች ይተቃቀፋሉ።»

አሁንም የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።እንዲያዉም ሐይማኖት የሚጋራቸዉ ሒንዱ ፅንፈኛ ገደላቸዉ።ምዕራባዊ ፓኪስታን የተባለችዉ ሙስሊማዊቱ ባንግላዴሽም ከሙስሊማዊቷ ፓኪስታን ተነጥላ ሌላ ነፃ መንግሥት መሠረተች።ሕንድና ፓኪስታን ባለፉት ሰባ አመታት አራቴ ተዋግተዋል።ከአራቱ ሰወስቱ በካሽሚር ግዛት ሰበብ የተጫረ ነዉ።ሙስሊሞች የሚበዙበት የካሽሚር ገሚስ ግዛት በሒንዱዎች እጅ በመቅረቱ ዛሬም ያጋጫል፤ ያጋድላል።

ሳዳር ፓታል የተባሉ ፖለቲከኛ ነፃነት ከመታወጁ አንድ ሳምንት በፊት ባደረጉት ንግግር «ብሪታንያዎች የክፍፍሉ ምክንያት

የሒንዱ እና የሙስሊሞች ጠብ ነዉ ይላሉ» አሉ «ግን በሁለቱ ትከሻ ላይ ሸክሙን የጫነዉ ማነዉ? እስከ እኔ ብሪታንያን ላንድ ሳምንት እንድገዛ ፍቀዱልኝ።ኢንግላንድ፤ዌልስ እስኮችላንድ ለዝንተ ዓለም የሚጋጩበትን ጠብ መፍጠር እችላለሁ።»

የሕንድ ይሁን የፓኪስታን፤ የዓረብ ይሁን የአፍሪቃ ፖለቲከኛ የዉጪዉ ሲዘዉረዉ እንድሜ ልኩን የሚሾርበት ምክንያትም በርግጥ ያጠያይቃል።ብቻ ሁለቱ ሐገራት ዛሬ ኑክሌር ታጥቀዋል።ሠላም የላቸዉም።ሰባ ዓመታቸዉ።በዚሁ ይቀጥሉ ይሆን? 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic