«ሐይሚ አርት» በጀርመን | ባህል | DW | 05.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

«ሐይሚ አርት» በጀርመን

ሥነ-ጥበብ የሕይወትን እውነታ መልሰን እንድንመለከት እና እድንመዝን የሚረዳን የጥበብ ዓይነት መሆኑን የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ስመጥር ከሆኑት ኢትዮጵያን ሰዓልያን መካከል ገብረ ክርስቶስ ደስታና፤ እስክንድር ቦጎስያን በጀርመን የሥነ-ጥበብ ክህሎትና ሥራቸዉ በሰፊዉ ይታወቃል።


የራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት አቅራቢያ በሚገኘዉ ኮለኝ ከተማ በሚገኝ አንድ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ከጎርጎረሳዉያኑ ከ1957 ዓ,ም እስከ 1961 ዓ,ም የስዕል እዉቀቱን በከፍተኛ ትምህርት ያዳበረዉ ሁለገቡ ጥበበኛ፤ ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ

ደሰታ ከትምህርት ማዕከሉ በከፍተኛ ዉጤት ማጠናቀቁ ይነገርለታል። በአሁኑ ወቅት የሰዓሊና ገጣሚ የገብረ ክርስቶስ ደስታን ፈለግ ይዘዉ በጀርመን የሥነ- ጥበብ ሥራዎቻቸዉን እያስተዋወቁ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ጥቂቶች አይደሉም። በጀርመን «ሐይሚ አርት» በመባል የምትታወቀዉ ወጣትዋ ሰዓሊ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች የሚያንፀባርቁትን ስዕሎችዋን ይዛ በመዉጣትዋ በተለይ ባለፈዉ ዓመትና ወራቶች እዚህ በጀርመን ታዋቂነትን እያገኘች መታለች። በቅርቡ የሥነ-ጥበቡን መድረክ የተቀላቀለችዉ ወጣትዋ ሐይማኖት መሰለ፤ የስዕል ክህሎት እንዳላት ያወቀችዉ በድንገት ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑን ገልፃለች። የዕለቱ ዝግጅታችን ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለን ማለትም « ሐይሚ አርትን » ያስተዋዉቀናል። ከዚህ ቀደም ማለት በህፃንነትዋም ሆነአልያም በትምህርት ቤት ምንም አይነት ስዕል ሞክራ እንደማታቅም ገልፃለች።


በጀርመን ሃገር ስትኖት ወደ 19 ዓመት እንደሆናት የምትናገረዉ ወጣት ሐይማኖት መሰለ የስዕል ሥራ ጥበብ በዉስጥዋ የፈነጠቀዉ ከሁለት ዓመት በፊት እንደሆነና ይህ ክህሎትዋ በአሁኑ ወቅት መተከዣዋ፤ ጓደኛዋ ፤ ጊዜ ማሳለፊያዋ እንዲሁም ባህልዋን ማስተዋወቅያዋ ማንነትዋን መግለጫዋ እንደሆነም ገልፃለች። ግን በትርፍ ጊዜ ከመደበኛ ሥራ ዉጭ የምትተገብረዉ በመሆኑ ትንሽ እንደሚከብዳት ሳትናገር አላለፈችም።


« ሐይሚ አርት » በሚል በጀርመን በመታወቅ ላይ የምትገኘዉ ወጣትዋ ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለ በስዕል ሙያ ላይ ያላትን ተፈጥሮሂዊ ክህሎት ይበልጥ ለማሳደግ በጀርመን ምቹ ሁኔታን እንዳገኘችና፤ የተለያዩ ትምህርቶችን በመከታተል ላይ መሆንዋንም ተናግራለች። በውስጥዋ ታምቆ የነበረው የፈጠራ ስሜትም በአጋጣሚ ልቆ በአሁኑ ወቅት ስዕሎችዋን በተለያዩ አጋጣሚዎች በእግዚቢሽነት በማቅረብ በርካታ ወዳጆችን ማፍራትዋን ገልፃለች።


ስዕሎችዋ አብዛኞቹ ባህላዊ ነገሮችን ያንፀባርቃሉ ፤ እንደገለፀችዉም በተለይ በጀርመን በዓዉደ ርዕይነት ለጀርመናዉያን የምታቀርባቸዉ ስዕሎች በአብዛኛዉ ባህልን የሚያንፀባርቁ እንደሆኑ ነዉ ወጣትዋ ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለ ተናግራለች። ከጀርመናዉያን ምን በርካታ ገንቢ አስተያየትንና አድናቆትን ማትረፍዋንም ገልፃለች።


ተቀማጭነቱን በሙኒክ ከተማ ያደረገዉ አፕኮአ ኤግዚቢሽን ማዕከል ዉስጥ በደንበኞች አገልግሎች ቢሮ ተቀጣሪ ሆና በማገልገል ያለችዉ ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለ ፤ ለሊትና በትርፍ ግዜዋ የምትተገብረዉን የስዕል ክህሎት ለማሻሻል የተለያዩ የስዕል ትምህርት ኮርሶችን ወስዳለች። በባቫርያ ግዛት በሚገኝ የባህል ማዕከልና በአንድ የልዩ ልዩ ትምህርት ማሰልጠኛ ተቋም ዉስጥ የስዕል ትምርት የሚሰጡት ስዊዘርላዳዊ ማርቲን ቫግነር ለወጣትዋ ሰዓሊ ለሐይማኖት የተለያዩ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል ፤ ቫግነር የሐይማኖት የስዕል ስራዎች ይላሉ፤


«የሥነ-ጥበብ ሥራዎችዋ ባህላዊ ይዘት ያለዉ ሆኖ የምዕራቡን የአሳሳል ሥልትም ይንፀባረቅበታል። ስዕሎችዋ እዉነታዊ ገፅታን የያዙና ደማቆች ናቸዉ። አንዳንድ ስዕሎችዋም አብስትራክት ማለት ረቂቅ አይነት ይዘትም ይታይባቸዋል። በዚህም ሐይማኖት ጥሩ የመሳል ክህሎት ያላት ሰዓሊ ናት። ደሞ በጣም ደስ የሚለዉ ነገር ቶሎ የመማር ችሎታም አላት»
ሐይማኖት የመማር የመማር ፍላጎትዋ እጅግ ከፍተኛ ነዉ የሚሉት የስዕል መምህሩ ቫግነር በመቀጠል፤


«አዎ ክህሎት እንዳላት ያወቀችዉ በቅርቡ ነዉ፤ የጠቀማትም ቶሎ የመቅሰም የመማር ችሎታዋና ፍላጎትዋ ነዉ። ከዝያ በተጨማሪ እና ዋንኛዉ ነገር እዚህ ከሚገኙ የሥነ-ጥበብ ሰዎች ጋር መነጋገር የምትችልበትን ቋንቋ አጥርታ ማወቅዋ ነዉ። ጀርመንኛ ቋንቋን ጥሩ ትናገራለች። ቋንቋን ጠንቋቃ ማወቅዋ ለምትሰራዉ ሥራ ትልቅና ጥሩ መሰርት ሆንዋታል። በርግጥ በምትስለዉ ስዕልም ያላትን ሃሳብ መግለፅ ትችላለች ግን እንድያም ሆኖ በዉይይት እና በሃሳብ ልዉዉጥ በቀለም ወረቀት ላይ የምታሳርፈዉን ሃሳብዋን ይበልጥ ማሻሻል ትችላለች»በርግጥ ሐይማኖት በከፍተኛ ተቋም ገብታ የስዕል ትምህርትን መከታተል ይኖርባት ይሆን? እንደ ማርቲን ቫግነር
«በስዕል ትምህርት መቀጠል ትችላለች። በአጠቃላይ ሲታይ የሰዉ ልጅ በህይወት ዘመኑ መማርን ማቋረጥ የለበትም። የሰዉ ልጅ በህይወት ዘመኑ ሁልግዜም ቢሆን አዲስ ነገሮችን ያገኛል። ያንን ደግሞ ለማሳደግ ያንን ለማስተካከል ይማራል፤ ዳግም አዲስ ነገርን ያገኛል። ያ ማለት ደግሞ የሰዉ ልጅ በህይወት እስካለ ድረስ ይማራል፤ እስከመጨረሻዉ ድረስ በትምህርቱን ይቀጥላል። በሐይማኖት የስዕል ህይወትም የሚያበቃ አይሆንም በየዕለቱ አዲስ ነገርን ትማራላች በዝያም ያንን ነገር በትምህርት ታጎለብታለች። እኔም ብሆን በየቀኑ ከተማሪዎቼ አዲስ ነገርን እማራለሁ፤ ይህ ሁኔታ መስጠትና መቀበል ሆኖ በህይወት የሚቀጥል ነገር ይሆናል»

Haimanot Messele und Martin Wagner

ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለ ከአስተማሪዋ ማርቲን ቫግነር ጋርበሐይማኖት ስዕሎች ኢትዮጵያን በይበልጥ አዉቄያለሁ ያሉት ስዊዘርላንዳዊዉ የስዕል አስተማሪ ማርቲን ቫግነር ፤ «በሐይማኖት ሥዕሎች በርግጥ፤ ይበልጥ ስለ ኢትዮጵያ አዉቄአለሁ። ኢትዮጵያን ጎብኝቼ ባላዉቅም ግን ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ ከ 30 ዓመታር በላይ ከቤተሰቦቼ ጋር ስለኖርኩ እንብዛም አዲስ አልሆነብኝም። ይህን ያህል ዓመታት በአፍሪቃ በመኖሪም ስለ አፍሪቃ ሥነ-ጥበብ ጉዳይ ብዙ ተምሪአለሁ አዉቄአለሁም። ሐይማኖት እዚህ በምትስላቸዉ ስዕሎች ሃገርዋን ወክላ ባህልዋን እያስተዋወቀች ነዉ ።የምመኝላት ስዕሎችዋን ወደ ሃገርዋ ይዛ ሄዳ እዚህ በጀርመን በዓዉደ ርዕይነት ያቀረበችዉን ሥዕሎችዋን በሀገርዋ ላይ እንድታሳይ ነዉ። በሥነ-ጥበብ ዓለም ይህ ዓይነቱ የክህሎት ልዉዉጥ ይታያል። ለምሳሌ ታዋቂዉ የሥነ-ጥበብ ሰዉ ፒካሶ በስራዎቹ በርካታ አፍሪቃዊ ይዘት ያላቸዉ ስዕሎቹን ማቅረቡ የሚጠቀስ ነዉ»ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለ የስዕል ሥራዎችዋን ይዛ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዛ መዲና አዲስ አበባ ላይ ዓዉደ ርዕይ ለማዘጋጀት ዝግጅት ላይ እንደሆነች ገልፃለች። ወጣትዋ ሰዓሊ የጀርመናዉያኑን የስዕል አሳሳል ስልትን እንዲህ ትገልፃለች።
ፊስ ቡክ በተሰኘዉ የማሕበራዊ መገኛኛ መረብና በሌሎች ድረ ገፆች ሐይሚ አርት «Haimi Art » በሚል እንደምትገኝ የገለፀችዉ ወጣትዋ ሰዓሊ ሐይማኖት መሰለ ከኢትዮጵያዉያን የሥነ-ጥበብ አፍቃሪዎችና ባለሞያተኞች ሃሳብና ክህሎትን ለመለዋወጥ ጉጉት እንዳላት ሳትገልፅ አላላፈችም። አድማጮች ስለ ባህል መድረክ ዝግጅት ያላችሁን አስተያየት ላኩልን፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic