ሐራሬ፤ ምናንጋግዋ በፕሬዝደንትነት ቃለ መሐላ ፈጸሙ | ዓለም | DW | 24.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሐራሬ፤ ምናንጋግዋ በፕሬዝደንትነት ቃለ መሐላ ፈጸሙ

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1987ዓ,ም ጀምሮ በሮበርት ሙጋቤ አስተዳደር ሥር የቆየችዉ ዚምባቡዌ ዛሬ አዲስ ፕሬዝደንት አገኘች። ርምጃዉ ችግር ዉስጥ ላለችዉ ሀገር የአዲስ ዘመን መባቻ እንደሆነ ተገምቷል። ከሁለት ሳምንት በፊት በሙጋቤ ከስልጣናቸዉ ተባረዉ ደ/አፍሪቃ የከረሙት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት በመሆን በዛሬዉ ዕለት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

የሙጋቤ የቀኝ ተደርገዉ ይታዩ የነበሩት ምናን ጋግዋ በቃለ መሐላዉ ወቅት ለዚህ ኃላፊነት በፓርቲያቸዉ መመረጣቸዉ ጥልቅ ትህትና እንዳሳደረባቸዉ ከመግለፅ በተጨማሪ ለሙጋቤ አክብሮታቸዉን በአደባባይ ገልጸዋል።

«ይህን ታላቅ ሕዝብ፣ የዚምባቡዌ ሪፑብሊክን በፕሬዝደንትነት እና በዚምባቡዌ መከላከያ ኃይል በጦር አዛዥነት ከዛሬ ጀምሮ  እንዳገለግል በፓርቲው ዛኑ ፒኤፍ በመወሰኑ ጥልቅ ትህትና ይሰማኛል። በዚህ ደረጃም ከሀገራችን መሥራች አባቶች በብቸኝነት በሕይወት ለሚገኙት ጓድ ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ ልዩ አክብሮቴን ልግለጽ። በትግላችን ወቅት ሀገራችንን ወደ ነፃነት መርተዋል፤ ወሳኝ እና በጣም ፈታኝ በሆነ ወቅትም ኃላፊነት ተረክበዉ ለሕዝባችን የተሻለ ነገር ለመሥራት ጥረዋል። ያ ደግሞ ሁሌም ሊነገር እና ሊከበር ይገባል።»

ምናንጋግዋ ቃለ መሐላዉን የፈፀሙት 60 ሺህ መቀመጫዎች ባሉት የሐራሬ ስታዲየም ሲሆን በዉስጥ ሆነ ዉጭ የተሰበሰበዉ ሕዝብ የተሻለ ዕድል በሀገሪቱ የማየት ተስፋ መሰነቁን አመላክቷል። የ62 ዓመቱ ፒተር ማፉሲሬ እንዲህ ይላሉ፤

«ይህ መንግሥት አዲስ የሥራ ቦታዎችን እንዲፈጥር፤ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን እንዲያስፋፋ እና፤ከመንግሥት ዉስጥ ሙስናን እንዲያጠፋ እንጠብቃለን። ከማዕቀብም ነፃ እና ከአድሎም የፀዳ እንዲሆን እንሻለን።»

የገዢዉ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍን ሊቀመንበርነትም የተረከቡት ምናንጋግዋ የሙጋቤ ዘመነ ስልጣን እስከሚያበቃበት መጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጨረሻ ድረስ በፕሬዝደንትነት ይቆያሉ። ቀጣዩ የምርጫ ጊዜ ገና ይፋ አልሆነም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ