ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 12 2017የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝ ሀገር በተካሄደው እና በተለያዩ ዘርፎች ውድድር በሚካሄድበት በእንግሊዝኛ ስያሜው International Green Gown Award የ2024 አሸናፊ መሆን መቻሉን የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ገለፁ።ዩኒቨርሲቲው ከመወዳደሪያ ምድቦቹ ኔቸር ፖዘቲቭ በሚለው ምድብ በሀረማያ ሀይቅ ላይ ያመጣውን ለውጥ ለውድድሩ ማቅረቡም ተገልጧል ።ከአካባቢው ገፅ ለአመታት ጠፍቶ ዳግም የተመለሰው የሀረማያ ሀይቅ በአሁኑ ሰዓት በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይስሀቅ ዩሱፍ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይስሀቅ ዩሱፍ ለዶይቼ ቬለ ዩኒቨርሲቲው በስምንት ምድቦች በተካሄደው አለም አቀፍ ውድድር በሀረማያ ሀይቅ ላይ የሰራውን ስራ ለውድድር አቅርቦ ማሸነፉን ገልፀዋል።ዶ/ር ይስሀቅ ሽልማቱ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል ።በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሀረማያ ከተማ የሚገኘው የሀረማያ ሀይቅ ለአመታት ከአካባቢው ገፅ ጠፍቶ ዳግም ከተመለሰ በኃላ ስላለበት ይዞታ የተጠየቁት ዶ/ር ይስሀቅ "በጥሩ ሁኔታ" ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ዳግም የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለማህበረሰቡ የተለያየ ጠቀሜታ እያበረከተ ያለው የሀይቁ ውሀ ዳግም እንዳይጠፋ ሌሎች ስራዎች ቢሰሩ መልካም ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።International Green Gown Award ከ2004 ጀምሮ በአለም ደረጃ ዘላቂነት ያለው ለውጥን ለሚያመጡ ዩኒቨርሲቲዎች አንድ የመወዳደርያ መድረክ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
መሳይ ተክሉ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ