ሐምሌ 4 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 11.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ሐምሌ 4 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.

በአውሮጳ እግር ኳስ የዋንጫ ፍጻሜ ትናንት በፖርቹጋል አንድ ለዜሮ የተረታችው ፈረንሳይ አጥቂ አንቶኒዮ ግሪዝማን ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተመረጠ። በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ላይ ጽጋቡ ገብረማሪያም ግርማይ በአጠቃላይ ነጥብ ደረጃውን እያሻሻለ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:57

ስፖርት

ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ በቱር ደ ፍሯንስ ሲሰለፍ ጽጋቡ የመጀመሪያው ነው። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዎስ ሐሚልተን ዳግም አሸናፊ ኾኗል። በሜዳ ቴኒስ ፉክክር አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስን የሚስተካከል አልተገኘም። በዌምብልደን ለሰባተኛ ጊዜ አሸናፊ ኾናለች።

የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት በአውሮጳ እግር ኳስ የዘንድሮ ውድድር ኮከብ ግብ አግቢ የኾነው የፈረንሣዩ አጥቂ አንቶኒዮ ግሪዝማንን ምርጥ ተጨዋች ሲል ሰየመ። ፈረንሣይ ትናንት ለዋንጫ ብትደርስም በፖርቹጋል አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት የተሸነፈችው ባለቀ ሰአት ነበር።

በትናንቱ ምሽት ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሁለት ጊዜያት አንብቷል። አንድም በጉዳት ከሜዳ ሲወጣ አንድም ተቀይሮ የገባው አጥቂ ኤደር በባከነ ሰአት አዘጋጇን ሀገር ጉድ አድርጎ ፖርቹጋሎችን ሲያስፈነጥዝ። የዓለማችን ምርጡ ተጨዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ደጋግሞ አንብቷል። በእርግጥም ሮናልዶ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስን የተካ እስኪመስል ድረስ ለተጨዋቾች መመሪያ ሲሰጥ ነበር።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

በጭንቀት ተውጠው የነበሩት አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስን ብዙዎች የተቀያሪ ወንበር እንዲያሞቅ ነው ያመጡት ይባል የነበረው ኤደር ባለቀ ሰአት በእግር ኳሱ ዓለም ማብቂያ የሌለው ደስታ አጎናጽፏቸዋል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስን ከፊት ያስቀደመው የፖርቹጋል ቡድን ዛሬ ዋንጫውን ይዞ ፖርቹጋል ሲገባ በዓሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በደስታ ተቀብሎዋቸዋል።

የዘንድሮ የአውሮጳ ዋንጫ ከ16 ቡድኖች ወደ 24 ማደጉ እንደፖርቹጋል የጠቀመው ሀገር የለም። በዘንድሮ ውድድር ከእያንዳንዱ ስድስቱም ምድብ ሁለት ቡድኖች በጥቅሉ 12 ቡድኖች በቀጥታ ሲያልፉ፤ ከእያንዳንዱ ምድብ ምርጥ ሦስተኛ ሆኖ የጨረሱ አራት ቡድኖችም ማለፍ ችለዋል። ፖርቹጋል በዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠ ዕድል ተጠቅሞ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮጳ ዋንጫን ማሸነፍ የቻለው። ፖርቹጋሎች በትናንቱ ድል ከፈረንሳይ ሊዛቦን፤ ከበርሊን እስከቦን በመላው ዓለም በደስታ ሲፍነከነኩ ዋንጫውን ለሦስተኛ ጊዜ እናስቀራለን የሚል ተስፋ ሰንቀው የገቡት ፈረንሳዮች ሕልማቸው መክኗል። አዘጋጇ ፈረንሳይ ውስጥ የዝግጅቱ አጠቃልይ ድባብ እና የውድሩ መንፈስ ምን ይመስል ነበር? ስቱዲዮ ከመግባቴ አስቀድሞ የፓሪሷ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህን በስልክ አነጋግሬያት ነበር።

እግር ኳስ አፍቃሪያን በፓርሲ ከተማ ተሰባስበው

እግር ኳስ አፍቃሪያን በፓርሲ ከተማ ተሰባስበውየትናትናውን የፈረንሳይ ሽንፈት በተመለከተ ጋዜጦች ከሰጧቸው አስተያየቶች መካከል ለ ፓሪዚየን የተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣ «አቤት ጭካኔ» ሲል አቢይ ርእስ አድርጎ አውጥቶታል። «በጋራ ደስታ ለመቦረቅ እጅግ ጓጉተን ነበር፤ እጅግ ያሳዝናል» ሲል ጋዜጣው የፈረንሳይ እግር ኳስ ደጋፊዎችን ስሜት አንጸባርቋል።

ብስክሌት
እጅግ ከባድ ፉክክር በሚታይበት የቱር ደ ፍሯንስ ተከታታይ ውድድር ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ጽጋቡ ገብረማርያም ግርማይ በትናንቱ 9ኛ ዙር ውድድር ከ193 ተወዳዳሪዎች 54ኛ ወጥቷል። ጽጋቡ በቱር ደ ፍሯንስ ውድድር በመሳተፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው። የ24 ዓመቱ ወጣት በየጊዜው በዚህ ውድድር ላይ የሚደነቅ መሻሻል እያሳየ ነው።

በትናንቱ ውድድር የኤርትራው ናትናኤል ብርሐኔ ከ193 ብስክሌተኞች 29ኛ በመውጣት ጠንካራ አትሌት መሆኑን አስመስክሯል። እስከ ዛሬ በተከናወኑት 9ኝ ውድድሮች በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊው ጽጋቡ 89ኛ ደረጃን ሲይዝ፤ የኤርትራው ናትናኤል 103ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ውድድር

የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ውድድር

እስካሁን 9 ዙር ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን፤ ዛሬ ረፍት ይደረግና 10ኛው ዙር ነገ ይቀጥላል። በነገው ውድድር ብስክሌተኞቹ 197 ኪሎ ሜትር ርቀት ይወዳደራሉ። ውድድሩ በተከታታይ ዘልቆ የመጨረሻው እና 21ኛው ዙር ሽቅድምድም የሚከናወነው ከሁለት ሳምንት በኋላ እሁድ ሐምሌ 17 ቀን ነው። እስከዚያ ድረስ ተወዳዳሪዎች በየደረጃው ለማሸነፍ ይፎካከሩና አጠቃላይ 21 ዙር ላይ ያመጡት ነጥብ ተደምሮም የመጨረሻ አሸናፊው ይለያል።

የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የሚኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ አሽከርካሪዎቹ ሌዊስ ሀሚልተን እና ኒኮ ሮዝበርግ መፎካከራቸውን ቀጥለዋል። በትናንቱ ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን በድጋሚ አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ኾኗል። የቡድኑ አባል ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ በሦስተኛነት አጠናቋል። የብሪታኒያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የትናንትና ድሉ በአምስት ሽቅድምድሞች አራተኛ ሆኖ ተመዝግቦለታል። እስካሁን ሌዊስ 47 ውድድሮች ላይ ማሸነፍ የቻለ ብርቱ አሽከርካሪ ነው። የመርሴዲስ ቡድኑ በዚህ የውድድር ዘመን ከ10 ውድድሮች ዘጠኙን ማሸነፍ ችሏል።

የዌምብልደን አሸናፊዋ ሴሬና ዊሊያምስ

የዌምብልደን አሸናፊዋ ሴሬና ዊሊያምስ

ኒኮ ሮዝበርግ በሁለተኛነት ቢያጠናቅቅም በሬዲዮ መነጋገሪያ ምክር በመቀበሉ ዓሥር ሰከንድ ተቀጥቶ ሦስተኛ ኾኗል። በዚህም መሠረት ሦስተኛ ኾኖ ያጠናቀቀው የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ኔዘርላንዳዊው ማክስ ፈርሽታፐን ሁለተኛ ደረጃ ተሰጥቶታል።

የሜዳ ቴኒስ
በዌምብልደን የሜዳ ቴኒስ ውድድር በሴቶች ፉክክር ዝነኛዋ አሜሪካዊት ሴሬና ዊሊያምስ ለሰባተኛ ጊዜ አሸናፊ ኾናለች። ሴሬና ትናንት ያሸነፈችው ጀርመናዊቷ አንጄሊክ ክሬበርን ነው። የብሪታንያው አንዲ ሙራይም በበኩሉ በዌምብልደን ለሁለተኛ ጊዜ አሸንፏል። አንዲ ሙራይ ትናንት ለድል የበቃው ካናዲያዊው ሚሎ ራኖይችን በማሸነፍ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰAudios and videos on the topic