ልዩ ባትሪ ድንጋይ እንደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 29.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ልዩ ባትሪ ድንጋይ እንደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ

ለተንቀሳቃሽ ወይም የእጅ ስልኮች (ሴልስ፤ ሞባይልስ) መልሶ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሞላ «AKU»(አኩሙሌተር) የተለመደ መሣሪያ ነው ። የኤልክትሪክ አውቶሞቢሎች ከጸሐይ ኃይል የሚገኝ ኤልክትሪክ ጉልበት እጅግ ያስፈልጋቸዋል ፤ ዋጋው ደግሞ ተስማሚ ነው።

የኅይል ምንጭ መጋቢዎች ጉዳይ(World Of Energy Solutions) የተሰኘ ዓለም አቀፍ ዐውደ ርእይ ፣ ሽቱትጋርት ጀርመን ውስጥ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለህዝብ እይታ ቀርቦ ነበር። በሌላም አጠራር «ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ነጻ የሆነ የኃይል ምንጭ ትርዒት » ተብሏል። ሠሪዎቹ ለዚህ የኃይል ምንጭ ዘርፍ ብሩሕ ዕድል አለ ባዮች ናቸው። እንዴት?

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና ማከማቸት የሚቻልበት አሠራር፣ በተለይ ደግሞ ከቦታ -ቦታ እንቅሥቃሴ በተስፋፋበት ዘመን ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣና ወደፊት የላቀ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑ ፣ እዚህ ጀርመን ውስጥ በባደን ቩርተምበርግ ፌደራል ክፍለ ሀገር ርእሰ ከተማ፣ ሽቱትጋርት በቅርቡ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የባትሪ ድንጋይና ሃይድሮጅን ዐውደ-ርእይ ላይ ተገልጿል። የሳይንስ ጠበብትና የኢንዱስትሪ ባለሙያዎችም ይህን በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተደረገውን ትልም እንደሚስማሙበት ነው የተመለከተው።

የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫና ማከማቻ እንዲሁም ማሠራጫ ተግባሮች፣ ፣ እዚህም ላይ ባትሪ ድንጋይን በተመለከተ፣ ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ስልቶች ዐቢይ ግምት ነው የተሰጣቸው። በተለይ ከ «ሊትየም» የሚገኙ ባትሪዎች ፤ ተመራማሪዎችንና ተጠቃሚዎችን ማማለላቸውም ነው የተገለጠው። በድቡባዊቷ ከተማ በ ዑልም፤ የፀሐይ ኅይል ምንጭና የሃይድሮጂን ምርምር ማእከል፣ የኤሌክትሪክ ና ቅመማ -ነክ የኃይል ምንጭ ሥነ-ቴክኒክ ንግድ ነክ ሥራ መሪ፣ ፕሮፌሰር ቬርነር ቲልሜትስዝ፣ ይህን ነበረ ያሉት።

«ትርፉን በዩውሮም ሆነ በዶላር ስያስቡት ፤ አሁን 15 ቢሊዮን ነው። በዓለም ገበያ! እ ጎ አ በ 2020 የሊትየም ባትሪ ድንጋዮች 30 ቢሊዮን ዩውሮ ወይም ዶላር ትርፍ የሚያስገኙ ይሆናሉ።»

የባትሪ ድንጋይ ገበያ የደራ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠው በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ረገድ የመዝናኛ ጉዳይ የሙዚቃ መሳሪያዎች ናቸው። ከሊትየም የሚሠሩ ባትሪዎች ለእጅ ስልኮችና «ላፕቶፕ» ኮምፒዩተሮች 3 እጥፍ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ እንደገና እስኪሞሉ ድረስ ማለት ነው!እንደገና ኃይል የሚያጠራቅሙ ባትሪ ድንጋዮ ች በብዛት ይመረታሉ። ታላላቅ የባትሪ ፋብሪካዎች፤ በተለይ በጃፓን ቻይናና ኮሪያ ልዩ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

«ከሊትየም የሚሠሩ ባትሪዎች ገበያ በአሁኑ ጊዜ በአስያ የደራ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የሊትየም ባትሪዎች ሥነ-ቴክኒክ በመጀመሪያ ጃፓን ውስጥ በ SONY በኩል ለሙዚቃ የኤሌክርሮኒክ መሣሪያዎች እንዲያገለግል ከተሠራ ወዲህ ነው። »

ለመዝናኛ የሚሆኑ የሙዚቃ ኤልክትሮኒክ መሣሪያዎች ኩባንያዎች ዋና ማዕከላቸው፣ እስያ፣ በተለይ ጃፓን ፣ ቻይናና ኮሪያ ሲሆን፣ በዚያ የሚገኙት ኩባንያዎችም፣ ከ 10 እና 15 ዓመatት ገደማ በፊት በዓለም ገበያ ሰፊ ተቀባይነት የሚኖራቸው ጥሩ ባትሪ ሲያቀርቡ መሆኑን መገንዘባቸው አልቀረም።

እ ጎ አ በ 1990ዎቹ ዓመታት የመጀመሪያዎቹ የእጅ ስልኮች ሁለት ሰዓት ከሠሩ በኋላ ባትሪአቸው ቀጥ ይል እንደነበረ የምናስታውሰው ነው። ስለሆነም፣ በሊትየም ባትሪ ከ ሁለት ሰዓት በላይ፣ ስድስት ሰዓት መገልገል የሚቻልበት ሁኔታ እንደ ትልቅ እመርታ ነበረ የታየው። ታዲያ የሊትየም የባትሪ ሥነ ቴክኒክ እስያ ውስጥ የተስፋፋበትና የዓለምን ገበያ ያጥለቀቀለቀበት ምክንያቱ ይህ ነበር»።

የባትሪ ድንጋይ ሥነ ቴክኒክ ሰፊ ተቀባይነትም ሆነ ትኩረት ያገኘው በኤሌክትሪክ ተንቀሳቃሽ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ፣ ከቦታ -ቦታ የመዘዋወር ተፈላጊነት የጎላ በመሆኑ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ባቻ በዓለም ዙሪያ 500,000 ያህል በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ተሠርተዋል።

ዓለም አቀፉ ንፁሕ የማጓጓዣ አገልግሎት ም/ቤት(International Council on Clean Transpotation) እ ጎ አ ከ 2020 አንስቶ በያመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች መሸጥ እንደሚችሉ ነው የሚገልጸው።ከየአሥራ አንዱ ተሽከርካሪ አንዱ ባለኤሌክትሪክ ሞተር ያለው ይሆናል።

በ2030 ከየሦስቱ አውቶሞቢል አንዱ ባለኤሌክትሪክ ሞተር መሆኑ እንደማይቀርም ነውየሚገመተው።ጠበብትእንደሚሉት፤የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የሽቦ መሥመሮች ላልተዘረጉላቸው አካባቢዎች የኃይል ምንጭ ማጠራቀሚያ ትልቅ ባትሪ ተፈላጊነት የጎላ ይሆናል።በነፋስ ኃይልና በፀሐይ ኃይል፤ ከሚገኝ የኅይል ምንጭ ጎን ለጎን ኢንዱስትሪዎችና መኖሪያ ቤቶችም በባትሪዎች የኅይል ምንጭ አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራር ይበልጥ ተስማሚ እንደሚሆን ነው የሚታሰበው።ታዲያ፣ጥቅሙ የታወቀለት የሊትየም ባትሪ ዋጋ ከመናር ይበልጥ እንዲቀንስ አንድ በካሊፎርኒያ፤ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ፣ ቴስላ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ሥራ ከ«ፓናሶኒክ» ኩባንያ ጋር በመተባበር በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ በኔቫዳ በረሃ አንድ ግዙፍ የባትሪ ድንጋይ ፋብሪካ ለመትከል አቅዷል። ባትሪዎች ፤ እ ጎ አ በ 2010 ከነበራቸው ደረጃ ጋር ሲነጻጸር ዋጋቸው ከእንግዲህ 80 ከመቶ ቀንሶ ሊገኝ እንደሚችልም ነው በመነገር ላይ ያለው።

ፕሮፌሰር ቬርነር ቲልሜትስዝ፣ በአዳጊ አጋሮች ከኃይል ምንጭ አኳያ ስላለው ችግርና አማራጭ ስለሆነው መፍትኄ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በሌሎች አገሮች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በተለይም በአዳጊ አገሮች፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአመዛኙ ስለተጓደለበት ሁኔታ ስነገር ነው የምንሰማው። ይህም ማለት፤ ቋሚ የኤልክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ማስተላለፊያ ሽቦዎችን መዘርጋቱ እጅግ ውድ ነው እየተባለ ነው የሚነገረው። በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስወጣልና! ከዚህ ነጻ ለመሆን፤ በረጅሙ ከሚዘረጋ ሽቦ ውጭ ፤ እንበል በአንዲት መንደር ፤ በሚሰጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ወይም ለአንድ መኖሪያ ቤት ብቻ በሚያገልግል መጠቀሙ፤ በዋጋ ወይም ወጪ ይበልጥ ረከስ ያለ ነው የሚሆነው»።

ጀርመንና የባትሪ ኢንዱስትሪ

የጀርመን የማሺንና ፋብሪያ ሥራ ማሕበርም ፣ የባትሪ ሥነ ቴክኒክ ወደፊት የሚያዋጣ መሆኑን በማገናዘብ ጥበቡን ፤ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ከማቅረቡ ተመክሮ ጋር በማጣመር ፣ በጀርመን እጅግ ዘመናዊ የባትሪ ፋብሪካዎች ሊቋቋሙ እንደሚችሉ ጠቁሞአል። በታዋቂው የ SIEMENS ኢንዱስትሪ ኩባንያ የባትሪ ምርት ጉዳይ ሥራ መሪ ፔተር ሃን ፣

«በሰፊው አቅድ ባለው መልኩ አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤት ማለትም ትልልቅ ባትሪዎችን ከሊትየም እየሠራን በማቅረብ ላይ እንገኛለን። ይህ ደግሞ ፤ በኤሌክትሪክ ለሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችና ለመሳሰሉት ፣ በአንድ ቋሚ ቦታ ልዩ ልዩ ተግባራትን ለሚያከናውኑም አስፈላጊነቱ ግንዛቤ ያገኘ ነው»። ማሕበሩ ፣ ፔተር ሃን ጨምረው እንዳብራሩት፤ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ኤልክትሪክ አመንጪ መሣሪያዎች ማምረቱ፣ ለዋጋ እጅግ መቀነስ አርአያነት ያለው ሆኗል።

« ጠበብት እንደሚያሰላስሉት፣ የሊትየም ባትሪዎች ዋጋ እጅግ ዝቅ ይላል። ትልልቆቹ ባትሪዎች፤ በሰዓት የኪሎዋት ዋጋ እ ጎ በ 2010 1000 ዩውሮ ነበ።ር። በ 2020፣ 200 ዩውሮ ቢሆን እንጂ ከዚያ ምንም ያህል አይጨምርም። በ 2020 እንግዲህ እንደተተነበየው፤ ለአያንዳንዱ የኪሎዋት ሰዓት ኃይል ለማጠራቀም 10 የዩውሮ ሴንት ይሆናል ዋጋው። ከ2020 በኋላ ደግሞ ዋጋው ይበልጥ እየቀነሰ ነው የሚሄደው።

ባትሪ ወይስ ሃይድሮጂን

በእሽቱትጋርት ከተካሄደው የትልልቅ ባትሪዎች ዐውደ ርእይ ጎን -ለጎን፤ ከውሃ በኤሌክትሪክ ርዳታ የሃይድሮጂንን ኃይል በማጥመድ በሰፊው ማጠራቀም እንደሚቻል ለማሳየት ተችሏል። የባትሪ ድንጋይ ጉዳዮች ባለሙያ ቲልሜትስዝ እንደሚሉት ሃይድሮጂን በሚንቀሳቀስ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ረገድ አጋዥ ቴክኖሎጂ ነው።

«ለተለመዱ የከተማ አውቶሞቢሎች፤ በባትሪ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እጅጉን የሚመረጡ ናቸው። ይሁን እንጂ በየዕለቱ ፣ ወደገጠር፣ ከሞላ ጎደል ፣ ራቅ ብሎ በተሽከርካሪ ለመጓዝ፣ ተለቅ ያለ መኪና ያሻል። እናም በሃይድሮጂን የሚሠራ ይበልጥ ይመረጣል። ስለዚህም የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሆኑት በሁለቱም ማለት በባትሪና በታመቀ ሃይድሮጂን እያፈራረቁ መጠቀሙ ፋይዳ ያለው ነው። »

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic