ልዑል ሉዊ ዋጋሶሬ፤ የንጉሥ ልጅ የዲሞክራሲ ታጋይ | አፍሪቃ | DW | 19.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ልዑል ሉዊ ዋጋሶሬ፤ የንጉሥ ልጅ የዲሞክራሲ ታጋይ

ሀገራቸው ነፃነቷን ከመቀዳጀቷ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነበር የተገደሉት። ቡሩንዲ ሠላማዊ በኾነ ሽግግር ነጻነቷን እንድታውጅ የልዑል ሉዊ ዋጋሶሬ ተግባር ልዩ ሥፍራ ይሰጠዋል። ምንም እንኳ የንጉሥ ልጅ ቢኾኑም ስለ ዲሞክራሲ በመስበክ፤ የሀገሪቱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንሥትርም መኾን ችለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:18

የቡሩንዲው ልዑል ሉዊ ዋጋሶሬ

የአፍሪቃ ብሔርተኞቹ የኮንጎው ፓትሪስ ሉሙምባ፣ የታንዛኒያው ዡሊዬስ ኒዬሬሬ እና የጋናው ክዋሜ እንኩርማህ ወዳጅ ልዑል ሉዊ ዋጋሶሬ በሀገራቸው የተከበሩ ጀግና ናቸው። 

ወቅቱ ቡሩንዲ ከቤልጂግ ነጻነቷን ለመቀዳጀት ነጋሪት የምትጎስምበት የጎርጎሪዮሱ 1961 ነው። ሀገሪቱ በቀጣዩ ዓመት 1962 ለምታውጀው ነጻነቷ ለመዘጋጀት ምርጫ አከናውናለች። አዲስ የተመረጡት ጠቅላይ ሚንሥትር ሉዊ ዋጋሶሬ መጻኢውን የሚመለከቱት በልበ-ሙሉነት ነው።
   
«ራሳችንን ማዘጋጀት፤ ነገሮችንም በእጃችን ማስገባት ይገባናል። ያለማጋነን ያን ለማድረግ ከአምስት እስከ ሰባት ወራት ይወስድብናል። ነገሮች ጥሩ እንዲኾኑ በመልካም ኹናቴም እንዲሠሩ እንሻለን።»

ኾኖም ዋጋሶሬ የቡሩንዲ ነፃነትን ለማየት አልታደደሉም። የ29 ዓመቱ ወጣት ልዑል ፓርቲያቸው ዩፒሮና (UPRONA ) በሀገር አቀፍ ምርጫው አስተማማኝ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ከጀርባቸው በጥይት ተመትተው ተገደሉ። ሉዊ ዋጋሶሬ በሀገሪቱ የነፃነት ንቅናቄ እውነተኛ ጀግና ተደርገው ይታያሉ። የዩፒሮና ፓርቲ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቦዪ አታናሴ፤ ሉዊ ዋጋሶሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከቱ የ14 ዓመት ታዳጊ ነበሩ።  

DW Videostill Projekt African Roots | Louis Rwagasore, Burundi

የንጉሥ ልጅ፤ የዲሞክራሲ ታጋዩ፤ የቡሩንዲ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚንሥትር፤ ልዑል ሉዊ ዋጋሶሬ

ቀኑ ኅዳር 13 በ1959 ነበር... ደመ-ግቡ፣ እጅግ ሳቢ፣ አብዝቶ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ወጣት ነበር። ግርማ ሞገሱ እና ለዓለም የነበረው ግልጽነትም ከተለያዩ ታላላቅ መሪዎች ጋር ወዳጅነት እንዲመሰርት አስችሎታል፤ በተለይ ከዡሊየስ ኒዬሬሬ፣ ከፓትሪስ ሉሙምባ እና ከክዋሜ እንክሩማህ ጋር...

የሉዊ ዋጋሶሬ ተወዳጅነት ሕዝቡ ከመንደር ፖለቲካ እና ከጎሠኛ አስተሳሰብ ተላቆ አንድ እንዲኾን ማድረግ አስችሏቸዋል። ዩፒሮና የተሰኘው ፓርቲያቸውም ሠፊ ቅንጅት ነበር፣ ይኽ ሊሠመርበት ይገባል ይላሉ በቡሩንዲ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ኤሚሌ ምዎሮሃ። ጥምረቱ በጎረቤት ሩዋንዳ የነበረው ብርቱ ኹከት በሀገራቸው እንዳይከሰት አስተዋጽዖ አድርጓል።     

ሉዊ ዋጋሶሬ በዚህ ተሳክቶላቸዋል፤ ምክንያቱም ቡሩንዲ ወደ ነፃነት የተሸጋገረችው ያለአንዳች ውጥረት ነበር ማለት ይቻላል። ፓርቲያቸው ዩፒሮና ለሁቱዎችም ኾነ ለቱትሲዎች አለያም ለጋንዋዎች እኩል ነበር።    

ቢኾንም ቅሉ ሉዊ ዋጋሶሬ በበርካታ ደመኞች የተከበቡ ነበሩ። ከጠላቶቻቸው መካከል እኚኽን፦ የንጉሣዊ ቤተሰብ ደም ያላቸው ወጣት ልዑል ፈጽሞ ያልጠረጠሩት የቅኝ ግዛት አስተዳዳሪዎች ይገኙበታል። የቤልጂግ ባለሥልጣናት ወጣቱ ልዑል አውሮጳ ተጉዘው ብራስልስ ከተማ ውስጥ ሳይቀር እንዲማሩም ፈቅደውላቸዋል። ልዑሉ ታዲያ እዚያ ከመላዋ አፍሪቃ ከተሰባሰቡ ተማሪዎች ጋር መገናኘት ችለዋል፤ ያ ለእሳቸው ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። የቡሩንዲ የምጣኔ ሐብት ጉዳይ ያንገበግባቸው የነበሩት ሉዊ ዋጋሶሬ ሀገራቸው ነፃ እንደምትወጣ ሙሉ እምነት በመሰነቅ በ1956 ወደ ቡጁምቡራ ተመለሱ። ሉዊ ዋጋሶሬ በጠቅላይ ሚንሥትርነት ከመመረጣቸው ቀደም ብሎ የምጣኔ ሐብት ነፃነትን ለመቀዳጀት ይቻል ዘንድ በሀገር ውስጥ ትብብሩ እንዲጠናከር ይተጉ እንደነበር ፕሮፌሰር ምዎሮሃ ይናገራሉ። ነፃዪቱ ቡሩንዲን ለማየት ሩቅ አልመዋል። ሀገራቸው እንድትበለጽግ ይመኙ ስለነበረም ቅንጅት እንዲፈጠር አድርገዋል። ከቡና እርሻ ባሻገር ቡሩንዲ ገና ያላደገች በአብዛኛው ገጠራማ ሀገር ነበረች። ሉዊ ዋጋሶሬ ቡሩንዲያውያንን ሊያስተባብር የሚችል ዘመናዊ ምጣኔ-ሐብት እንዲዳብር መሠረት ጥለዋል።  

DW Videostill Projekt African Roots | Louis Rwagasore, Burundi

የጋንዋው ሰው ሉዊ ዋጋሶሬ የጎሣ ውጥረትን ለማርገብ በሚል በትዳር የተሳሰሩት ከሑቱ ሴት ጋር ነበር

ይኽ ቅንጅት ግን በአስተዳዳሪዎቹ በመታገዱ ከሽፏል። የሉዊ ዋጋሶሬ ሠላማዊ ሽግግርም አብሮ ተሰናክሏል። ከሳቸው መገደል በኋላ የፖለቲካ ፍጥጫ እና የጎሣ ባላንጣነት ቡሩንዲን ከአንዱ የግጭት ጥግ ወደ ሌላኛው አላትሟታል። የሉዊ ዋጋሶሬ እጣ ፈንታ በዚያ መልኩ ቢደመደምም፤ የቡሩንዲ ነዋሪዎች ግን ወጣቱ ልዑል ትንሽ በሕይወት ቢቆዩ ኖሮ ሀገራችን ምን መልክ ይኖራት ነበር ሲሉ ዛሬም ድረስ ይጠይቃሉ።   

  

ታማራ ዋከርናግል/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

Audios and videos on the topic