ልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘር ግብይት | ኤኮኖሚ | DW | 07.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ ልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘር ግብይት ልትፈቅድ ዝግጅት ላይ ነች

ልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘር ግብይት

ኢትዮጵያ በዘረ-መል ምኅንድስና የተዘጋጀ የጥጥ ዘር ግብይትን ለመፍቀድ እየተዘጋጀች ነው። የአካባቢ ተቆርቋሪዎች እና የሸማቾች መብት ተሟጋቾች ግን አገሪቱ አሁንም ልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘር ለመጠቀም ዝግጁ አይደለችም ሲሉ ይሞግታሉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:18
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:18 ደቂቃ

ኢትዮጵያ ልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘር ግብይት ልትፈቅድ ዝግጅት ላይ ነች

ኢትዮጵያ ከበርካታ ከአመታት ክርክር በኋላ በዘረ-መል ምኅንድስና የተለወጠ (Biotechnologically modified) የጥጥ ዘር ለገበያ እንዲቀርብ ልትፈቅድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ጥብቅ የነበረውን የደኅንነት ሕይወት አዋጅ ያሻሻለችው ኢትዮጵያ በታቀበ ወይም በተከለለ ማሳ ላይ የልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘር ሙከራ ስታካሒድ ከርማለች። ሙከራው ግን ሱዳን እና ሕንድን በመሳሰሉ አገሮች በሰፊው ለተሰራጨው ዘር ማረጋገጫ ከመፈለግ የዘለለ አይደለም። ዶ/ር ፈንታሁን መንግስቱ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ኃላፊ ናቸው።ኃላፊው የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ማዕከል በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ቢቲ ከተን ተብሎ የሚታወቀውን የልውጠ ኅያዋን ጥጥ ለሙከራ አገር ውስጥ ማስገባቱን ተናግረዋል። የሚመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት አካል ከውጤቱ በመነሳት ዝርያዎቹ ለገበያ የሚቀርቡበትን ሒደት እንደሚወስንም ገልጠዋል።  

የኢትዮጵያ አመታዊ የጥጥ ምርት አገሪቱ ተስፋ የጣለችበትን የጨርቃ ጨርቃ ማምረቻ ዘርፍ በአግባቡ መመገብ የቻለ አይመስልም። አብዛኞቹ ማሳዎች  በአዋሽ ሸለቆ እና በአማራ ብሔራዊ ክልል ምዕራባዊ ክፍል ቢገኙም ስድስት የኢትዮጵያ ክልሎች ጥጥ ያመርታሉ። ወደ 65 ከመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ጥጥ በመካከለኛ እና ከፍተኛ ሜካናይዝ የእርሻ ማሳዎች ይመረታል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ አገራት የግብርና ቢሮ ከሶስት ወራት ባወጣው የሐተታ ጥናት በጎርጎሮሳዊው 2016/17 የበጀት አመት የኢትዮጵያ የጥጥ ግብዓት ፍላጎት ወደ 62,000 ሜትሪክ ቶን እንደሚያሻቅብ አትቷል።  ይህ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃጸር በ12,000 ሜትሪክ ቶን ጭማሪ አለው። ፍላጎቱ አገሪቱ ከምታመርተውም ሆነ ከውጭ ከምታስገባው ጋር ፈፅሞ 
እንደማይመጣጠንም የቢሮው የዳሰሳ ጥናት ይጠቁማል። የጥሬ እቃ ፍላጎቱ መጨመር በአገሪቱ የተስፋፉት የጨርቃ ጨርቅ እና ተጓዳኝ አምራቾች ስራ እስከ ማስተጓጎልም ደርሷል። ዶ/ር ፈንታሁን መንግሥቱ እንደሚሉ የኢትዮጵያ የግብዓት ፍላጎት መጨመር የልውጠ ኅያዋን የጥጥ ዘርን መጠቀምን አስፈላጊ ከሚያደርጉት ገፊ ምክንያቶች አንዱ ነው። «በጣም በርካታ ኩባንያዎች ተገፍተዋል።» የሚሉት ዶ/ር ፈንታሁን ወደ 60 የሚጠጉ ፋብሪካዎች ፍላጎትን የሚያሟላ ምርት መታጣቱን ገልጠው የጥጥ ምርት እየቀነሰ እንደሆነም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 


በከባቢ አየር ለውጥ፤ የዝናብ እጥረት እና የአፈር ለምነት መመናመን የዜጎቻቸውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ለተሳናቸው ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ልውጠ ኅያዋን ዘር ሁነኛ መፍትሔ ነው የሚል ክርክር ይደመጣል። አፍሪቃ ቴክኖሎጂውን እንድትቀበል የሚደግፉ ወገኖች ጥናቶች እያጣቀሱ አመታዊ የግብርና ምርትን እንደሚያሳድግ ይወተውታሉ። የቡርኪና ፋሶ፤ ደቡብ አፍሪቃ እና ግብፅ ገበሬዎች የጥጥ እና በቆሎን ጨምሮ የተለያዩ የልውጠ ኅያዋን ዘሮችን በመጠቀም ከአፍሪቃ ቀዳሚ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የአካባቢ ተቆርቋሪዎች እና የሸማቾች መብት ጥበቃ ተሟጋቾች በዘረ-መል ምኅንድስና የተዘጋጁ ሰብሎች በሰው ልጆች ጤናና እና በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን አሉታዊ ጫና እየነቀሱ ሲሞግቱ ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ገብረመድኅን ቢረጋ ናቸው። «ኢትዮጵያ ውስጥ የዘረ-መል ምኅንድስና ምርቶችን እና ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ  የሚያስችል ጥንቃቄ እና ቅድመ-ዝግጅት አጥጋቢ ነው ብለን አናምንም።» የሚሉት አቶ ገብረመድኅን «በባለሙያም ሆነ በቴክኖሎጂ ረገድ በጣም ብዙ ይቀረናል።» ሲሉ አክለዋል። አቶ ገብረመድኅን ከጥጡ ባሻገር ከፍሬው የምግብ ዘይት ተመርቶ ለገበያ ቢቀርብ ለጤና ጠንቅ ይሆናል የሚል ሥጋትም አላቸው።
ዶ/ር ፈንታሁን መንግስቱ ቢቲ ከተን ተብሎ ከሚታወቀው ልውጠ ኅያዋን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ማዕከል ቆየት ባሉት ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ዶ/ር ፈንታሁን ይኸን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሕንድ እና የሱዳን የጥጥ ገበሬዎች የጥጥ ምርታቸውን እስከ ሶስት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸውንም ተናግረዋል። ልውጠ ኅያዋን ዘር የጥጥ ሰብልን የሚያጠቃውን ቦልወርም የተሰኘ ትል ለመከላከል ያስችላሉ የሚሉት ዶ/ር ፈንታሁን  የኢትዮጵያ የጥጥ አምራቾች የትሉን ጥቃት እስከ አስራ አራት ጊዜ መድሐኒት ይረጫሉ ሲሉ ተናግረዋል። 

አቶ ገብረመድኅን ቢረጋ ልውጠ ኅያዋን ፦አገር በቀል የጥጥ ዝርያዎችን እንዳይበክሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ይናገራሉ። በአመራረት ሒደት አንዳቸው ሌላውን ሳይበክሉ መኖር ስለማይችሉ ኢትዮጵያ ቢቲ ከተንን መጠቀሟ ካልቀረ በተራራቀ ቦታ ሊዘሩ እንደሚገባም ጨምረው ተናግረዋል። አቶ ገብረመድኅን የዘረ መል ምኅንድስናን ከሚቃወሙባቸው ምክንያቶች መካከል የጥገኝነት እና አዲስ መጤ የሰብል በሽታ ሥጋት ይገኙበታል። 
የልውጥ ዘር አምራች ኩባንያዎች የዓለምን ዘር ቀስ በቀስ በቁጥጥራቸው ሥር እያዋሉ ነው የሚል ወቀሳ ከአካባቢ ተቆርቋሪዎች ይደመጣል።  እንደ ሕንድ እና ቡርኪናፋሲ በመሳሰሉ አገሮች የቢቲ ከተንን ዘሮችን ከምዕራቡ ዓለም ኩባንያዎች ገዝተው የዘሩ ገበሬዎች ብድራቸውን መክፈል ተስኗቸው ኤኮኖሚያዊ እና ማሕበረሰባዊ ቀውስ ውስጥ ሲገቡም ተስተውሏል።  የጥገኝነት ሥጋት እንዳለ የሚስማሙት ዶ/ር ፈንታሁን መንግሥቱ  ኢትዮጵያ ዝርያዎቹን ለመጠቀም ስትወስን ከጥገኝነቱ ለመላቀቅ የወጠነችው እቅድ እንዳለ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic