ሌላ ቦምብ፤ ሌላ ስጋት | ዓለም | DW | 04.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሌላ ቦምብ፤ ሌላ ስጋት

ኪም ዴ-ጁንግ--- የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን እንደያዙ ካወጇቸዉ መርሆቻቸዉ፤ ከሰሜን ኮሪያዎች ጋር የሚደራደሩበት መርሕ ዋናዉ ነበር።ኪም «የፀሐይ ነፀብራቅ» ያሉት መርሕ በያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በቢል ክሊንተን በመደገፉ ከ1950 ጀምሮ በኮሪያ ልሳነ-ምድር የፀናዉን የዉጊያ-የለም፤  ሠላምም የለም ዉጥረትን አርግቦት ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:40
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:40 ደቂቃ

ሌላ ቦምብ፣ ሌላ ስጋት

ሱንግ ጆንግ-ሔኦን የ27 ዓመት ወጣት ነዉ።ደቡብ ኮሪያዊ።«ሑለቱም ያዉ ናቸዉ አለ» ትናንት በተሰላቸ ስሜት።«ኪም ጆንግ ኡንም (ዶናልድ) ትራምፕም የሚያደርጉትን መገመት አይቻልም።አዉነቱን ለመናገር ጦርነት ቢጫር ብዙ አይገርመም።መቼ እንደሚነሳ ማንም አያዉቅም።የኮሪያ ሕዝብ ሥለ ሁኔታዉ በትክክል የሚያዉቀዉ ነገር የለም።»

የሚታወቀዉ ሠላም አለመኖሩ ነዉ።የሚታወቀዉ የኑኬሌር ጦርነት ደመና ማንዣበቡ ነዉ።የሚታወቀዉ መሪዎቹ የሚሉና የሚያደርጉት አለመታወቁ ነዉ። የሚታወቀዉን እየጠቀሰን የማይታወቀዉን እንጠየቅ።                            

የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ገዢዎች ያደርሱባቸዉ የነበረዉን ግፍ፤ እስራት፤ የግድያ ሙከራ ተቋቁመዉ ለረጅም ጊዜ በመታገላቸዉ ሰበብ «የሩቅ ምሥራቁ ማንዴላ» ይባሉ የነበሩት ኪም ዴ-ጁንግ በ1998 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን እንደያዙ ካወጇቸዉ መርሆቻቸዉ፤ ከሰሜን

ኮሪያዎች ጋር የሚደራደሩበት መርሕ ዋናዉ ነበር።ኪም «የፀሐይ ነፀብራቅ» ያሉት መርሕ በያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በቢል ክሊንተን በመደገፉ ከ1950 ጀምሮ በኮሪያ ልሳነ-ምድር የፀናዉን የዉጊያ-የለም፤  ሠላምም የለም ዉጥረትን አርግቦት ነበር።

ፕሬዝደንት ኪም ዴ-ጁንግን እና የሰሜን ኮሪያዉን መሪ ኪም ጆንግ ኢልን፤ ኪም ጆንግ ኢልን ከዩናትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማድሊን ኦል ብራይት ጋር ፒዮንግያንግ ዉስጥ ያደራደረዉ፤ የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተንን ከሰሜን ኮሪያዉ ምክትል መሪ  ከማርሻል ጆ ምዮንግሮክ ጋር ዋሽግተን ዉስጥ ፊት ለፊት ያነጋገረዉ ጥረት፤ ሠላም ለሚፈልጋት እሩቅ እንዳልሆነች ለድፍን ዓለም አስመስክሮ ነበር።

ኪም ዴ-ጁንግ ያስተዋወቁት መርሕ በአሜሪካኖች ተቀባይነት በማግኘቱ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ለማቆም ተስማምታ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎችም የኑክሌር መርሐ-ግብሯን እንዲቆጣጠሩ ፈቅዳ ነበር።በ2001 ፕሬደንት ቢል ክሊንተን በፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ ተተኩ።አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሥልጣን በያዙ ባመቱ እንዲሕ አሉ

                                        

«ሰሜን ኮሪያ ሕዝቡ እየተራበ ሚሳዬልና ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ የሚታጠቅ ሥርዓት ነዉ ያላት።ኢራን ይሕን መሳሪያ ለማግኘት አጥብቃ እየጣረች ነዉ።የኢራን ሕዝብ ለነፃነት ያለዉን ተስፋ ያልተመረጡ ጥቂቶች የሚደፈሉቁባት፤ ሽብርንም ወደ ዉጪ የምታዛምት ናት።ኢራቅ በፀረ አሜሪካ አቋሟ ፀንታለች፤ አሸባሪነትን መደገፏን ቀጥላለች።----እንዲሕ ዓይነት መንግስታት እና ተባባሪዎቻቸዉ አሸባሪዎች የዓለምን ሰላም ለማወክ የሚታጠቁ የሰይጣን ዛቢያ ናቸዉ።»

ቡሽ በሰይጣን

ዛቢያነት ከወነጀሏቸዉ ሰወስት ሐገራት በጣም ደካማዋን ኢራቅን ምንቅርቅሯን ሲያወጡ «የፀሐይ ነፀብራቁ» መርሕ አራማጅ ኪም ዴ-ጁንግ በአክራሪዉ ፖለቲከኛ በሮሕ ሙሕዩን ተተኩ።2003።ከብዙ ጥረት፤ከተከታታይ ድርድር፤ የስድስት ሐገራትን ዲፕሎማቶች ካባተለ ዉይይት በኋላ ኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ብልጭ ብሎ የነበረዉ የሰላም ተስፋም ተዳፈነ።

ሰሜን ኮሪያ እንደ ሐገር ከታወቀችበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ አምባ ገነን ቤተሰብ የምትገዛ ዝግ ሐገር ናት።ፍትሕ፤ሰብአዊ መብት፤ነፃነት ጨርሶ የማይታወቅባት ሐገር ናት። ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በሰይጣንነት እስከወነጀሏት ድረስ ግን አንድም የኑክሌር ቦምብ አልሞከረችም።የመጀመሪያዉን የአዉቶሚክ ቦምብ የሞከረችዉ ኢራቅን የወረረዉ የአሜሪካ ጦር ድል ቢያደርግ ኖሮ እንደማይምራት በሰጋችበት ዘመን ነበር።ጥቅምት 2006።በሰወስተኛ ዓመቷ ሁለተኛዉን ደገመች።2009።

ኪም ዴ-ጁንግ የ2000ዉን ኖቤል የሠላም ሽልማት ያሰጣቸዉን የድርድር መርሐቸዉን «የፀሐይ ነፀብራቅ» ያሉበትን ምክንያት ሲጠየቁ ስያሜዉ የግሪኮች ጥንታዊ አፈታሪክ፤ ይዘቱ ግን የኮሪያዎች ይትባሐል እንደሆነ አስታዉቀዉ ነበር።

ኮሪያዎች «ጠላትሕ አደጋ እንዳያደርስብሕ ቅረበዉ፤ የሚያረካዉ ነገር ስጠዉም» የሚል ነባር ልምድ አላቸዉ አሉ።ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ባፈነዳች ወይም ሚሳዬል ባወነጨፈች ቁጥር ሶል ላይ የሚደረገዉ አንድም አፀፋ ዛቻ፤ አለያም የጦር  ልምምድ፤ ዝግጅት እንጂ ኪም ዴ-ጁንግ ወደ ፖለቲካ የቀየሩት ነባሩ ልምድ አይደለም።የዋሽግተን እና የቶኪዮ ዛቻ ፉከራ ደግሞ ከሶሎችም የባሰ ነዉ።

የዓለምን ሠላም ለማስከበር የቆመ የሚባለዉ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትም  ከዋሽግተን የሚረቀቅለትን የማዕቀብ ርምጃ «ወደ ሰላም ድርድሩ ተመለሱ» ከሚል አረፍተ-ነገር ጋር ከማፅደቅ አልፎ ሠላምን የሚያስከብር ሁነኛ አቋም ይዞ አያዉቅም።

ሰሜን ኮሪያ ትናንት የሞከረችዉ ስደስተኛዉ ቦምብ ሐድሮጂን ይባላል። ከዚሕ በፊት ከሞከረቻቸዉ ሁሉ እጅግ የላቀ ነዉ።50 ኪሎቶን ይመዝናል።ባለሙያዎች እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ማብቂያ በጃፓን ከተሞች ላይ ከጣለቻቸዉ ቦምቦች ከአስር ጊዜ በላይ ጥፋት የሚያደርስ ነዉ።ቦምቡን የሚያወነጭፍ

አሐጉር አቋራጭ ሚሳዬልም አላት።

ወጣቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እንደ እድሜ አቻዎቻቸዉ ጨዋታና ፌዝ አምሯቸዉ ወይም ሞቅ ብሏቸዉ የጦር አዛዣቸዉን ቀጥል ካሏቸዉ የደቡብ ኮሪያ የትኛዉም ከተማ፤ የጃፓን ማንኛዉም ደሴት፤ የዩናይትድ ስቴትስ ሎስአንጀለስ፤ ዴንቨር፤ቺካጎ፤ ቦስተን እና  ኒዮርክ ባፍታ ወደ ክሳይ አመድ ክምርነት ይለወጣሉ።

የቻይና፤የሩሲያ፤የፈረንሳይ መሪዎች የሰሜን ኮሪያን እርምጃ አዉግዘዉ በጦር የሚዛዛቱት መንግሥታት የጥፋት ሥጋቱን በድርድር እንዲፈቱት አደራ ብለዋል።የጀርመንዋ መራሒተ-መንግስት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክልም በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ጠቡን በድርድር ለመፍታት መጣር እንዳለባት አሳስበዋል።

                                  

«ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካን እንደ ሰላም ኃይል እንፈልጋታለን፤ ለዚህም አስላጊዉ ሁሉ  መደረግ ይኖርበታል።  እናም ለዚህ ግጭት ወታደራዊ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ብቻ ነዉ የሚያስፈልገዉ። ይህን ለማረጋገጥም አስፈላጊዉን ሁሉ አደርጋለሁ። ከአሜሪካኑ ፕሬዝደንት ጋር ከፍተኛ ልዩነት ቢኖረንም በሌላ ወገን ደግሞ ልንተባበርበት የሚገባ ጉዳይም አለ፤»

የደቡብ ኮሪያ አፀፋ ግን ሶሎች ነባር ባሕላቸዉን፤የቀዳሚዎቻቸዉን መርሕ፤ሰላማዊ መፍትሔ የሚሉ ደጋፊዎቻቸን ጥሪም አለማክበራቸዉን መስካሪ ነዉ።ፕሬዝደንት ሙን ጄ-ኢን እንዳሉት ሰሜን ኮሪያ ጠካንካራ እና አሳማሚ እርምጃ  ይወሰድባታል።

                                 

«ሰሜን ኮሪያ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ይበልጥ የሚያገልላትን ግራ-አጋቢ እርምጃ ዳግም ወስዳለች።ደሕና አድርጎ የሚያሳምም እርምጃ ለመዉሰድ እንዘጋጃለን።ሰሜን ኮሪያ የኑክሌርና የሚሳዬል መርሐ-ግብሯን እርግፍ አድርጋ የሚያስተዋት እርምጃ ከመወስድ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም።»

የፕሬዝደንት ሙን ማስጠንቀቂያ እስካሁን ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ የምታመርተዉ በደቡቦች ፈቃድና ይሁንታ ነበር ማለት ይሆን ያሰኛል።የደቡብ ኮሪያ ጦር ዛሬ የወሰደዉ እርምጃ የፕሬዝደንቱ ማስጠንቀቂያ አካል መሆን አለመሆኑ በርግጥ ግልፅ አይደለም።ግልፅ የሆነዉ ጦሩ የመካከለኛ ርቀት ተመዝግዛጊ ሚሳዬል ሲያወነጭፍ መዋሉ ነዉ።ሰሜኖችን ለማስፈራራት።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር

ሺንዞ አቤ አፀፋ ከደቡብ ኮሪያዉ መሪ ለስለስ ያለ ነዉ።ከሰወስት ሳምንት በፊት በሰሜን ኮሪያ ላይ ዓለም አይቶት የማያዉቀዉ እቶንና መዓት ለማዝነብ የዛቱት ፕሬዝደንት ትራምፕ ትናት ቀዝቀዝ ብለዋል።ከሩቅ ያያቸዉ  ጋዜጠኛ ጠየቃቸዉ «ሰሜን ኮሪያን ይወጋሉ» ብሎ።«እናያለን» መለሱ ፕሬዝደንቱ።መከላከያ ሚንስትራቸዉ ጂም ማቲያስ ግን ከሚንስትርነት ይልቅ ጄኔራልነቸዉ ደምቆ ነበር።

                              

«ብዙ ወታደራዊ አማራጮች አሉን።ፕሬዝደንቱ ሥለ እያንዳዱ አማራጭ ማብራሪያ እንዲሰጣቸዉ ይፈልጋሉ።እራሳችንን፤ተባባሪዎቻችንን ደቡብ ኮሪያንና ጃፓንን ከጥቃት የመከላከል ችሎታ እንዳለን ግልፅ አድርገናል።ለተባባሪዎቻችንን ከጥቃት የመከላከል ቃላችን በብረት የተለሰነ ነዉ።በዩናይትድ ስቴትስ፤ጉዋምን ጨምሮ በግዛቶችዋ ወይም በተባባሪዎቻችን ላይ የሚደርስ ጥቃት ገደብ የለሽ ወታደራዊ አፀፋ ይገጥመዋል።ዉጤታማ እና ድባቅ የሚያስገባ አፀፋ።»

ኢትዮጵያ የምትመራዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ማምሻዉን በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረ ነዉ።ምክር ቤቱ ከ1950 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ላይ 21 የወረራ፤የማዕቀብ፤ የዉግዘት ወይም የማስጠንቀቂያ ዉሳኔዎችን አሳልፏል።ምናልባት 22ኛዉ ዛሬ ይቀጥል ይሆናል። ከእስከዛሬዉ ዉሳኔ አንዱም  ሰላም አላወረደም። ሰላም አዋኪዉ ማለነዉ? 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic