ላይቤርያና የዋሽንግተን ጉባዔ | አፍሪቃ | DW | 15.02.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ላይቤርያና የዋሽንግተን ጉባዔ

በላይቤርያ የርስበርሱ ጦርነት ካበቃ ዛሬ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላም፡ ሀገሪቱ ራስዋን ችላ ለመቆም ትችል ዘንድ ገና ብዙ ዓለም አቀፍ ርዳታ ያስፈልጋታል።

ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና ፖል ዎልፎዊትስ

ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና ፖል ዎልፎዊትስ

ይህችው አፍሪቃዊት ሀገር ከተደቀነባት ችግር መካከል ትልቁ የተሸከመችው ሦስት ነጥብ ሰባት ሚልያርድ ዶላር የውጭ ዕዳ ነው። ይህንኑ ችግር ለማቃለልና ለላይቤርያም ብሩሕ የወደፊት ዕድል ለመክፈት ስለሚቻልበት ጉዳይ ለመምከር ሀያ ሁለት ሀገሮችና ወደ ስድሳ የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በዋሽንግተን የሁለት ቀናት ስብሰባ አካሂደዋል።

ላይቤሪያ ለጀርመን መክፈል ያለባት የውጭ ዕዳ ሦስት መቶ ሚልዮን ዶላር ይደርሳል፤ ይኸው የአፍሪቃዊቱ ሀገር ዕዳ ሊሰረዝ እንደሚገባው በጉባዔው ወቅት ተገልፆዋል፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን፡ ላይቤሪያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት፡ አይ ኤም ኤፍና ከዓለም ባንክና ከአፍሪቃ የልማት ባንክ የተበደረችውን ገንዘብ ቀስ በቀስ ከፍላ መጨረስ እንደሚኖርባት የዓለም ባንክ ወስኖዋል። ሦስቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የላይቤርያን ዕዳ ይሰርዙ ዘንድ ካለፉት ወራት ወዲህ ጥረት ሲካሄድ መቆየቱን በዋሽንግተኑ ስብሰባ የጀርመናውያኑን የልዑካን ቡድን የመሩት ብርጊተ ዩሰን አስታውቀዋል።
« ዩኤስ አሜሪካ ለላይቤርያ ተጨማሪ ርዳታ እንዲገኝ ጥረት ጀምራለች። ጥረትዋ ከተሳካላት፡ ሌሎች ለጋሽ ሀገሮች ድርሻ ይተባበሩና ድርሻ ያበረክቱ ዘንድ ይቀላቸዋል፡ በሚቀጥሉት ሣምንታት፡ ወራት ለዚሁ ጉዳይ መፍትሄ እንደሚገኝ ተስፋ እናደርጋለን። »
ላይቤርያ የአይ ኤም ኤፍ ዕዳዋን ትከፍል ዘንድ ዩኤስ አሜሪካ 185 ሚልዮን ዶላር እንዲዘጋጅ ለሀገርዋ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ማመልከቻ አቅርባለች። ብሪታንያም ላይቤሪያ ከአፍሪቃ የልማት ባንክ ከተበደረችው ዕዳ መካከል አሥር ከመቶውን ለማቅረብ ዝግጁነትዋን ገልፃለች። ዩሰን እንዳስረዱት፡ የዋሽንግተኑ ጉባዔ ለላይቤሪያ የውጭ ዕዳ በቅርቡ መፍትሄ ያስገኛል።
«መፍትሄው ገና አልተገኘም፡ ጠበብት በሚቀጥሉት ቀናትም መደራደር ይኖርባቸዋል። ይህ ከሆነ በኋላ በሁለት ሀገሮች መካከል ያለው ዕዳ የሚሰረዝበት ጥሩ ዕድል ሊፈጠር ይችላል፡ በተለይ፡ ላይቤርያ ለልማቱ ተግባር በአስቸኳይ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ እንደገና የምታገኝበት ዕድል ይከፍትላታል። »
ላይቤሪያ በቅርቡ ከዓለም አቀፍ ዕዳ ነፃ እንደምትሆንና የዓለም ባንክ ያዘጋጀው የአነስተኛ ብድር መርህን የምታሟላ ሀገር እንደምትሆን የላይቤርያ ገንዘብ ሚንስትር አንቶንየታ ሳየህ ተስፋ ገልፀዋል። ምክንያቱም፡ ያኔ የዕዳ ክፍያው በሀገሪቱ በጀት ላይ ጫና እንደማያሳርፍ ነው ሳየህ ያመለከቱት።
« ስብሰባው ለኛ ጥሩ ነበር። እርግጥ፡ ገና ብዙ መፈፀም ያለበት ጉዳይ አለ። ከኛም ብዙ ይጠበቃል። ይህንንም ለማሟላት ዕቅድ አለን። ግን፡ አንድ ትልቅ ርምጃ ወደፊት መራመዳችን የማይካድ ነው። »
እንደ ላይቤሪያዊቱ ሚንስትር አስተያየት፡ ጀርመን የላይቤርያን ዕዳ ለመሰረዝ ያሳለፈችው ውሳኔ ለላይቤርያ እና ለሕዝብዋ ወሳኝ ሆኖ አግኝተውታል።
« ጀርመናውያኑ ዘንድሮ የቡድን ስምንት እና የአውሮጳ ኅብረት የሚንስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚደንትነትን ሥልጣን ይዘዋል። ጀርመን የላይቤርያን ዕዳ ለመሰረዝ ባሳየችው ዝግጁነት ሌሎቹ የቡድኑ አባል መንግሥታትም ተመሳሳዩን ርምጃ እንዲወስዱና ላይቤርያም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተበደረችውን ዕዳ ቀስ በቀስ በምትከፍልበት ሂደት ላይ ሁነኛ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጠንካራውን ምልክት ልኮዋል። »
የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ተጠሪ ኬት ራይትም ጉባዔው የላይቤርያ ሕፃናት ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ዕቅድ በማውጣቱ ተግባር ላይ ሰፊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አስረድተዋል። የዓለም ባንክም በሚቀጥሉት አሥራ ስምንት ወራት ለላይቤርያ ስድሳ ሚልዮን ዶላር ርዳታ ለመስጠት ዕቅድ እንዳለው በዋሽንግተኑኑ ጉባዔ ውጤት የረኩት የዓለም ባንክ ባለሥልጣን ክላርሰን ገልፀዋል። በጉባዔው ለተገኘው ውጤት ላይቤርያ ፕሬዚደንትዋን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ማመስገን ይገባታል። የቀድሞዋ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሰርሊፍ ባላቸው ተሞክሮና ግንኙነት የተነሳ፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በሀገራቸው ፈጣን መሻሻል አስገኝተዋል፤ ምንም እንኳን አንዳንድ የሀገራቸው ዜጎች የመሻሻሉን ሂደት ፈጣን ሆኖ እንዳላገኙት ፕሬዚደንትዋ ቢያስታውቁም። ሰርሊፍ በጉባዔው ላይ የሀገራቸውን መነግሥት ስህተቶች ሳይደባብቁ ያቀረቡበት ድርጊታቸው ከተሳታፊዎጭ በኩል አድናቆት አትርፎላቸዋል። የዋሽንእግትን ቀጣይ ጉባዔ ከአንድ ዓመት በኋላ በላይቤሪያ መዲና ሞንሮቪያ የሚደረግ ሲሆን፡ ስብሰባው ዘንድሮ የተገቡ ቃሎችና የወጡ ዕቅዶች ተግባራዊ መሆናቸውን ይገመግማል።

ተዛማጅ ዘገባዎች