ሊዮኔል ሜሲ ታሪክ ሰርቷል | ስፖርት | DW | 24.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ሊዮኔል ሜሲ ታሪክ ሰርቷል

ሊዮኔል ሜሲ ታሪክ ሰርቷል። በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ 37,000 ሰዎች መሳተፋቸው ተገልጧል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪዎች አቅም እየከዳቸው ይመስላል። አርሰናልና ሊቨርፑል ዳገቱ ከብዷቸው 8ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ እየኳተኑ ነው። ቸልሲ ዘንድሮም ጥንካሬ አልተለየውም፤ ማንቸስተር ሲቲና ማንቸስተር ዩናይትድን በቅርብ ርቀት አስከትሎ

ሆኖም በነጥብ ልቆ በአንደኛነት እየገሰገሰ ነው።በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ፥ ኃያሉ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ16ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ትንንሾቹን ቡድኖች ሽቅብ ለመመልከት ተገዷል።ባየርን ሙንሽን ዛሬም ያው ባየርን ሙንሽን ነው። አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የፍፃሜ ውድድር ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ለእንግሊዛዊው ሊዊስ ሀሚልተን እጁን ሰጥቷል።

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንት ጨዋታ ቀዳሚውን ግብ በአጥቂው ሪኪ ላምበርት ያስቆጠረው ሊቨርፑል ዳግም ሽንፈት ተከናንቧል፤ ሊቨርፑል በክሪስታል ፓላስ 3 ለ1 ተቀጥቷል። ሊቨርፑሎች በሻምፒዮንስ ሊግም ኹለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀራቸው ከምድባቸው ዝቅተኛ ነጥብ ይዘው በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ምናልባት አንፊልድ በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ የስዊዘርላንዱ ባዝል ነጥብ ከጣለላቸው ወደ ኹለተኛ ደረጃ ይሸጋገሩ ይሆናል። ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ግን አልተሳካለትም፥ የሜርሲሳይዱ ሊቨርፑል በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ለሽንፈት ተዳርጓል። ለተከታታይ ሽንፈቶቹ አሠልጣኙ ብሬንዳን ሮጀርስ ተጠያቂ ናቸው ተብሏል።

የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ከልጃቸው ጋር

የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ከልጃቸው ጋር

ትናንት ቶትንሐም ከሁል ሲቲ ጋር ተጋጥሞ 2 ለ1 ረትቷል። ከትናንት በስትያ በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ስዋንሲን 2 ለ1፣ ኒውካስትል ኪው ፒ አርን 1 ለ ምንም እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ የዘመናት ተቀናቃኙ አርሰናልን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ቸልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ዌስት ብሮሚችን አስተናግዶ 2 ለ ዜሮ አሰናብቷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዡን ቸልሲ በ32 ነጥቦች ይመራል። ሳውዝሐምተን 25 ነጥቦች ይዞ ይከተለዋል። ማንቸስተር ሲቲ በ24 ነጥብ ሦስተኛ፣ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ በ19 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ኪው ፒ አር፣ በርንሌይ እና ላይስተር ሲቲ ከታች ወደላይ ከ20ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ላይ በመገኘት ወራጅ ቃጣና ውስጥ ናቸው። ሁሉም ቡድኖች 12 ጨዋታዎችን አከናውነዋል።

ጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ ቡድናቸውን ደግፈው ያቀኑት የብሬመን ደጋፊዎች አንገት ሲደፉ፤ ሐምቡርጎች በደስታ ጮቤ ሲረግጡ አምሽተዋል። ትናንት ሐምቡርግ ቬርደር ብሬመንን 2 ለባዶ በማሸነፉ ከወራጅ ቃጣናው ለመውጣት ችሏል። በምትኩ ቦሩስያ ዶርትሙን፣ ቬርደር ብሬመን እና ሽቱትጋርት ከ16ኛ እስከ መጨረሻው የ18ኛ ደረጃ በቅደም ተከተል ይገኛሉ። አውስቡርግ ሽቱትጋርትን 1 ለዜሮ አሸንፏል።

ሐምቡርጎች በትናንትናው ወሳኝ ጨዋታ ገና ከመጀመሪያው ንቁ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ነበር። ለሐምቡርጎች በ84ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው አርትዮምስ ሩድኔቭስ ነበር። መደበኛ የጨዋታው ክፍለ-ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው 3ኛ ደቂቃ ላይ ራፋኤል ቮልፍ ኹለተኛውን ግብ በገዛ መረቡ ላይ አሳርፏል። ሐምቡርግን ከወራጅ ቀጣናው ከፍ እንዲል ያስቻለው የትናንቱ ጨዋታ ወሳኝ እንደነበር የክንፍ ተመላላሹ ኒኮላይ ሙይለር ጠቅሷል።

ሐምቡርግ ከቬርደር ብሬመን ጋር ሲጋጠም

ሐምቡርግ ከቬርደር ብሬመን ጋር ሲጋጠም

«በጣም ወሳኝ ጨዋታ ነበር። ያ ጨዋታ ወሳኝ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል። በዚያ ላይ የጨዋታው ፍጥነት፤ ከእዛ ደግሞ የደረጃ ሠንጠረዡ፥ እጅግ በጣም ወሳኝ ጨዋታ ነበር»

ሐምቡርጎች ነጥብ ላለመጣል እንዲያ ቆርጠው ሲገቡ፥ እንግዳው የብሬመን ቡድን ይኽ ነው የተባለ ጥረት ሳያደርግ በመከላከል የመልሶ ማጥቃት ስልት ላይ ነበር ያተኮረው። ሐምቡርጎች በእርግጥም አሸንፈው ሦስት ነጥቦች ለመሰብሰብ መቁረጣቸውን ያመላከተ ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በሞሐመድ ጎዋይዳ አደረጉ፤ ግብ ለመሆን ግን አልቻለችም። በኹለተኛው አጋማሽ ግን ብሬመኖች ባይሳካላቸውም አይለው ነበር። የብሬመን አማካይ ፊን ባርቴል።

«እዚህ መሸነፍ አይገባንም ነበር። ሐምቡርጎች ምን አይነት ዕድል ገጥሟቸው ነበር፥ አላውቅም። ምናልባት በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ የግብ ዕድል ገጥሟቸው ነበር፤ ከእዚያ ውጪ ግን ምንም አላደረጉም። ውጤቱ ምናልባት 0 ለ0 መሆን ነበረበት። ግን ደግሞ እዚህ በደንብ ተጫውተን ማሸነፍ ነበር የሚጠበቅብን። ግን 2 ለ ባዶ ነው የተረታነው፤ ለምን? እንጃ!»

ከትናንት በስትያ ሔርታ ቤርሊን ኮሎኝን 2 ለ1 አሸንፏል። ኃያሉ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለቡንደስ ሊጋው አዲስ ከሆነው ፓዴርቦርን ጋር 2 ለ 2 አቻ መውጣቱ ብዙዎችን አስደምሟል። ፍራይቡርግ ማይንትስን ገጥሞ በተመሳሳይ ኹለት እኩል ወጥቷል። ሌቨርኩሰን ሐኖቨርን እንዲሁም ሞይንሽንግላድባኽ ሐኖቨርን 3 ለ1 ረትተዋል። ሻልካ ዎልፍስቡርግን 3 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ግዙፉ ባየርን ሙይንሽን ሆፈንሀይምን 4 ለዜሮ አንኮታክቷል። በእዚህም መሠረት ባየርን በ12 ጨዋታዎች 30 ነጥብ ይዞ ቀዳሚውን ስፍራ ተቆናጧል። 23 ነጥብ ለመሰብሰብ የቻለው ዎልፍስቡርግ በሦስት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ግላድባኽን አስከትሎ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የባየር ሙይንሽኑ አማካይ አርያን ሮበን በቡድኑ በተመሳሳይ በአማካይ የሚሰለፈው ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ከጉዳት አገግሞ ወደ ሜዳ መግባቱን በተመለከተ እንዲህ ብሏል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከፓዴርቦርን

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከፓዴርቦርን

«ወሳኙ ተጫዋች ተመልሷል። ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ብዙ ችግሮች ነበሩበት፥ እናም መጀመሪያ አካባቢ ድጋፍ ልናደርግለት ግድ ነበር። ግን እሱም ቢሆን መጀመሪያ ላይ ነበር፥ ከእዛ ቀስ እያለ ወደ ጨዋታው ስልት ሲመለስ መመልከት በእውነት በጣም ደስ ይላል። በጣም ድንቅ ነበር።»

የሩጫ ውድድር

ወደ 40 000 ሯጮች ይካፈሉበታል ተብሎ በተጠበቀው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትናንት በወንዶች የሩጫ ውድድር አዝመራው በቀለ አሸናፊ መሆኑ ተዘግቧል። በሴቶች ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር ውዴ አየለው 10 ኪሎ ሜትሩን በ34 ደቂቃ ከ03:04 በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች። አዝመራው በቀለ በአሸናፊነት ያስመዘገበው ሠዓት 30 ደቂቃ ከ11:01 ሠከንድ መሆኑም ተጠቅሷል። በኃይሌ ገብረስላሴ አዘጋጅነት ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መካሄድ የጀመረው ውድድር ለ14ኛ ጊዜ ሲከናወን 37,000 ሰዎች እንደተሳተፉበት ተገልጿል።

የፎርሙላ 1 አሸናፊ ሌዊስ ሐሚልተን

የፎርሙላ 1 አሸናፊ ሌዊስ ሐሚልተን

የመኪና ሽቅድምድም

ትናንት አቡዳቢ ውስጥ በተካሄደው የፎርሙላ አንድ የፍፃሜ ውድድር እንግሊዛዊው ሌዊስ ሐሚልተን ለኹለተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። የ29 ዓመቱ እንግሊዛዊ በመርሴዲስ ተሽከርካሪው ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ የሆነው እጎአ በ2008 ነበር። የትናንትናውን ድል አስመልክቶ ሌዊስ ሐሚልተን ሲናገር፦ «በዓለም ላይ ከምንም በላይ የሆነ ስሜት ነው። ሕይወቴን በመላ የኖርኩት ለእዛ ነው። ከእንቅልፌ ስነሳ፥ ስለማመድ፦ ያ የአሽከርካሪዎች ሁሉ ምኞት ነው። ከመርሴዲስ ጋር ከ13 ዓመቴ አንስቶ ይኸው አለሁ፤ በቃ የእኔ ቦታ እዚህ ነው።»

የሜዳ ቴኒስ

በዓለም አቀፍ የሜዳ ቴኒስ ውድድር ኃያልነቱን በተደጋጋሚ ያስመሰከረው ስዊትዘርላንዳዊው ሮጀር ፌዴሬር ትናንት ፈረንሳይ ውስጥ የተካሄደውን የዳቪ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ለማሸነፍ ችሏል። ሮጀር ፌዴሬር ትናንት ከፈረንሳዊው ሪቻርድ ጋስኬን ጋር ተከታታይ ዙር ጨዋታዎች አከናውኖ 3 ለ1 በመርታት በሜዳ ቴኒስ ጨዋታ አይበገሬነቱን አስመስክሯል። ሮጀር የትናንቱን የዳቪ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ለማሸነፍ 16 ዓመታት ግድም ለመጠበቅ ግድ ሳይለው አልቀረም፤ ሆኖም የተለያዩ የሜዳ ቴኒስ የፍፃሜ ውድድሮችን በአጠቃላይ በሚባል መልኩ ለማሸነፍ የቻለ ብርቱ ተወዳዳሪ መሆኑን አስመስክሯል።

ታሪክ ያስመዘገበው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ

ታሪክ ያስመዘገበው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ

አርጀንቲናዊው የባርሴሎና ግብ አዳኝ ሊዮኔል ሜሲ በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ታሪካዊ ግብ አስቆጥሯል። ሊዮኔል ሜሲ በራውል ጎንዛሌዝ ተይዞ የቆየውን 71 የሻምፒዮንስ ሊግ ግብ ክብረወሰን በሻምፒዮንስ ሊግ የነገው ጨዋታ ሊያሻሽል እንደሚችል ተገምቷል። ባርሴሎና አያክስን የዛሬ 15 ቀን 2 ለዜሮ ባሸነፈበት ዕለት ሊዮኔል ሜሲ ከራውል ጎንዛሌዝ ጋር እኩል የምታደርገውን 71ኛ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማድሪድ ቆይታው ከመረብ ያሳረፋቸው ግቦች 70 ነበሩ። ሜሲ ከትናንት በስትያ ቡድኑ ባርሴሎና ሴቪላን 5 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማስቆጠር ሐትሪክ ሰርቷል። በእዛም ብቻ አልተወሰነም፥ በቴልሞ ዛራ ተይዞ የቆየውን የስፔን ላ ሊጋ 251 ግቦች ለቡድኑ 253 በማግባት አሻሽሎ ታሪክ ሰርቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic