ሊቢያ፤ ድርድርና ዉጊያ | ዓለም | DW | 15.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሊቢያ፤ ድርድርና ዉጊያ

ዘመቻዉ ለአፍሪቃ ዳግማዊት ሶማሊያን፤ ለአረብ ዳግማዊት ኢራቅን በሚያስከትል ዉጤት ሊያሳርግ እንደሚችል በተለይ አፍሪቃዉያን ተናግረዉ፤ አስጠንቅቀዉ፤ ተማጽነዉም ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:07
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:07 ደቂቃ

ሊቢያ፤ ድርድርና ዉጊያ

ሮብ-በርሊን። የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የሊቢያ ተፋላሚ ሐይላትን መከሩ-እንዲሕ እያሉ።«ዛሬ እዚሕ የሚደራደሩት ወገኖች ካልተስማሙ፤ አንዳቸዉም አይጠቀሙም።የሚጠቀሙት ሌሎች ፅንፈኛ ቡድናት ናቸዉ።ISIS»

ማክሰኞ፤ሞሮኮ፤ የሊቢያ ተፋላሚ ሐይላት ተወካዮችን ያሳፈረዉ አዉሮፕላን ወደ ጀርመን ሲበር ISIS ሚስራታሕን መቆጣጠሩን አስታወቀ።ሐሙስ፤ የበርሊኑ ድርድር አበቃ።አርብ ቶብሩክ የሚገኘዉ መንግሥት ተባባሪ ጦር አዛዥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሠላም ዕቅድ እንደማይቀበሉ በድጋሚ አስታወቁ። ቅዳሜ፤- ዩናይትድ ስቴትስ ከሊቢያ ሚሊሻዮች ያንዱን መሪ በአዉሮፕላን ቦምብ መግደሏ ታወጀ።አራት ቀን።አራት ክስተት። የምስቅልቅሊቱ ሐገር ምስቅልቅል ዕዉነት።

ትሪፖሊ።እንደ ብዙ ሰላዮች ስማቸዉን መናገር አይፈልጉም። ፎቷቸዉ በጋዜጣ መታተሙን ግን አይቃወሙም። በቴሌቪዥን መታየት መናገሩንም እንዲሁ።«እያንዳዱን መንገድ፤ እያንዳዱን ቀጣና አዉቀዋለሁ።» የተወለዱ፤ያደጉ፤ የሠሩባት ሚያዉቋት ከተማ የማያዉቋትን ያክል ወድማለች።ትሪፖሊ።

ሰዉዬዉ ሲያድጉ፤ ሲማሩ፤ ሲሰሩባት በሕንፃ- መንገድ፤በገበያ አዳራሽ-መደብሮች የተንቆጠቆጠች ዉብ፤ ዘመናይ፤ የሐብታሞች ሞቃት ከተማ ነበረች። በወር 1,5 ሚሊዮን የዉጪ ሐገር ጎብኚ፤ ነጋዴ፤ ደላላ፤ ባለኩባንያ የሚርመሰመስባት ደማቅ ከተማ። ትሪፖሊ። ዛሬ ይኽ ሁሉ ትዝታ ነዉ-ለሰዉዬዉ።ሕዝቧም።

«ምናልባት እዚሕ ርዕሰ-ከተማይቱ ዉስጥ ከሚኖረዉ ግማሽኑን ሕዝብ አዉቀዋለሁ።እነሱም ያዉቁኛል።» ቀጠሉ ሰዉዬዉ።ከሚያዉቁት ከሚያዉቃቸዉ ሕዝብ ገሚሱ ተገድሏል፤ ሌላዉ ሸሽቷል፤ ወጣቱ ሊዋጋ ዘምቷል።የተቀረዉ በየሕንፃዉ ፍርስራሽ ሥር ተወሽቋል።

የቀድሞዉ የሊቢያ የሥለላ ድርጅት ባልደረባ የኮሌኔል ሙዓመር ቃዛፊን መንግሥት ከድተዉ የያኔዎቹን አማፂያን የተቀላቀሉት የተሻለ ፖለቲካዊ ሥርዓት ይመሠረታል ብለዉ ነበር።ቃዛፊ በተገደሉ ማግሥት የተመሠረተዉ የሊቢያ የሽግግር መንግሥት ዳግም ያደራጀዉ የስለላ ድርጅት አባል ሆኑም።የሽግግር መንግሥቱ ፈርሶ ሊቢያ ባለ ሁለት መንግሥት ስትሆን ያለ አዛዥ-አለቃ ብቻቸዉን ቀሩ።ግን ይሰራሉ።ሕገ-ወጥ የሚሏቸዉን ስደተኞች እያደኑ ይይዛሉ።በሕግ አልባዋ ሐገር-ሕግ ማስከበር።

«ሊቢያን ሠላም ለማድረግ ሐላፊነታችንን ከመወጣት የሚያግደን ሐይል የለም።መሥራታችንን እንቀጥላለን። አዲሲቱን ሊቢያ ማደራጀት አለብን።አያንዳዱ ሰዉ ሥፍራ ካላገኘ ሊቢያ አትጠገንም።የሐገር ወዳዶች ምግባር እያከናወንን ነዉ።ለልጆቻችን የምናወርሰዉ ይሕንን ነዉ።»

በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቤርናርዲኒኖ ሌዮን በየአጋጣሚዉ የሚሉትም ይሕንኑ ነዉ።ድርጅታቸዉ ሁሉም ሊቢያዊ የሚወከልበት ተጣማሪ መንግሥት እንደሚሠረት ይፈልጋል።ዤኔቭ-ዘንድሮ ጥር።

«ዛሬ የቀጠልነዉ-ባለፈዉ ሳምንት የጀመርነዉን ሥራ ነዉ።አንዳዶቹን ነጥቦት ከልሰናል።በመነጋገሪያ አርዕስቱ ላይ በተለይ ሥለ ተዓማኒ መንግሥት ምሥረታ ተስማምተናል።መልካም ምግባር ነዉ።በሁሉም ተሳታፊዎች መካካል የሐሠብ ልዉዉጥ ተደርጓል።እንደሚመስለኝ ጥሩ እመርታ እያሳየን ነዉ።»

ጥር ላይ ታየ የተባለዉ እምርታ እስከ ዛሬ-በርግጥ የለም።ዓለም አቀፉ ድርጅት እስከ ጥርስ የትነበር?

የምዕራባዉያን መንግሥታት ጦር የያኔዎቹን የሊቢያ አማፂያንን ደግፎ ያቺን ሐብታም፤አዳጊ፤ በረሐማ ሐገር በቦምብ-ሚሳዬል ካወደመበት ከ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ሊቢያ ሠላምም፤ ማዕከላዊ መንግሥትም፤ ፀጥታ አስከባሪም ኖሯት አያዉቅም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሳካለትም -አልተሳካለት ተፋላሚዎችን ለመሸምገል አራት ዓመት የጠበቀበት ምክንያት ያጠያይቃል።

መንግሥት አይደለም መንደር ማስተባባር የማይችሉትን የነሙስጠፋ አብዱል ጀሊልን ቡድን በመደገፍ ኒኮላ ሳርኮዚ-ከፓሪስ፤ ዴቪድ ካሜሩን-ከለንደን ፤ ባራክ ኦባማ ከዋሽግተን ሊያቢያን ያወደመዉን ዘመቻ ሲያዙ፤ ዘመቻዉ ለአፍሪቃ ዳግማዊት ሶማሊያን፤ ለአረብ ዳግማዊት ኢራቅን በሚያስከትል ዉጤት ሊያሳርግ እንደሚችል በተለይ አፍሪቃዉያን ተናግረዉ፤ አስጠንቅቀዉ፤ ተማጽነዉም ነበር።

ዓለም አቀፍ የሚባለዉ ድርጅት የሐያላኑን ሐሳብ አፀደቀ እንጂ የተቀሩ አባላቱን ሐሳብ ለማስተናገድ አቅምም፤ ፍላጎትም አልነበረዉም።ከመጋቢት-ጀምሮ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ እስከተገደሉበት እስከ ጥቅምት 2011 በዘለቀዉ የምዕራባዉያን ጦር ድብደባ እና በሊቢያ ተፋላሚ ሐይላት ዉጊያ ብዙዎች እንደገመቱት፤ ከሠላሺ በላይ ሊቢያዊ አልቋል።በመቶ ሺህ የሚቆጠር ቆሰሏል።ተፈናቅሏል።ተሰድዷልም።በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት-ንብረት ወድሟል።

ሳርኮዚና ካሜሩንን ቤንጋዚ ድረስ አጉዞ ባደባባይ ያስጨፈረዉ ድል፤ ከዋሽግተን የተንቆረቆረው የሠላም፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተስፋ ከበነነ አራት ዓመት ተቆጠረ።ሊቢያ ዛሬ በ1990ዎቹ አጋማሽ ከነበረችዉ ሶማሊያ፤ ከ2003 ወረራ በኋላ ከምናዉቃት ኢራቅም ብሳለች።በሕንፃ ፍርስራሽ፤ በነዳጅ ክሳይ፤ በቦምብ-ጥይት ቀለሕ የተሞላችዉ ሐገር ከአልቃኢዳ ደጋፊዎች እስከ ISIS ተዋጋዊዎች፤ ከጎሳ ታጣቂዎች፤ ጄት፤ ታንክ፤ መድፍ እስከሚያዙ ሚሊሺያዎች ይፈነጩባታል።

ስምንት ትላልቅ ታጣቂ ቡድናት፤ ወደ ሰወስት መቶ የሚጠጉ የጎጥ ታጣቂዎች ይርመሰመሱባትል።ሁለት መንግሥት፤ ሁለት ምክር ቤት (ፓርላማ)፤ ሁለት ጠቅላይ ሚንስትሮች አሏት።

እርግጥ ነዉ ሐያላኑ መንግሥታት እና በነሱ የሚዘወረዉ የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት ከድሮ-እስከ ዘንድሮ ከእስራኤል-አረቦች፤ እስከ ሩዋንዳ፤ ከቀድሞዋ ይጎዝላቪያ እስከ ሶሪያ፤ ከኮንጎ እስከ ዩክሬን፤ ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ደቡብ ሱዳን፤ ሠላም ለማዉረድ ያደረጉት ጥረት ለአስተማማኝ ዉጤት አልበቃም።

ኢትዮያዉናንን ጨምሮ የዉጪ ስደተኞች የሚታረዱ፤ የሚደፈሩ፤ በዘፈቀደ የሚታሰሩ፤ የሚሰቃዩባት ሊቢያን-ሐገር ለማድረግ ከመሸ የተጀመረዉ ጥረትም እስካሁን ያመጣዉ ዉጤት የለም።የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቤርናርዲኒዮ ሌዮን ባለፈዉ ጥር ዤኔቭ ላይ የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮችን ከሰበሰቡ በኋላ እዚያዉ ዤኔቭ፤ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ ዉስጥ የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮችን በጋራና በተናጥል አነጋግረዋል።

በስድት ወራት ዉስጥ አራት ጉባኤዎች ተደርገዋል። ሌዮን ጥር ላይ የሰጡት ተስፋ-ገቢር የመሆን ፍንጭ ግን አልታየበትም።እና ሌላ-ጉባኤ። በርሊን።ሮብ።

«ግጭቱ በሚቀጥልበት በያንዳዱ ዕለት፤ የISIS ነቀርሳም ሊቢያ ዉስጥ እየተሰራጨ ነዉ። ለዚሕም ነዉ በሚቀጥሉት ቀናትና ሳምንታት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት የሚመሠረትበት መንገድ ካልተገኘ (አደገኛ ነገር እንደሚከተል) ለሊቢያ ተፋላሚ ሐይላት የምናሳስበዉ።መግባባት ላይ ከልተደረሰ እዚሕ ለድርድር ከተቀመጡት አንዳቸዉም ተጠቃሚ አይሆኑም።ሌሎች ፅንፈኛ ሐይላት ISIS እንጂ።»

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይን ማየር።ሽታይን ማየር ባስተናገዱት ጉባኤ ላይ 23 ተፋላሚ ሐይላትን የወከሉ መልዕክተኞች ተገኝተዉ ነበር።ጉባኤዉ መቀመጫቸዉን ትሪፖሊና ቶብሩክ ያደረጉት የሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊትለፊት የተቀመጡበት፤ በፀጥታዉ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ የአምስቱ መንግሥታት እና የአዉሮጳ ሕብረት ተወካዮች የተገኙበት ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተፋላሚ ሐይላትን ማደራደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመደራደሪያ ነጥቦቹን አራቴ ቀያይሯል ወይም በድርጅቱ ዲፕሎማቶች ቋንቋ አሻሽሏል።በርሊን ላይ የተነሳዉ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ምሥረታ የመጨረሻዉ እና አግባቢዉ ነዉ ተብሏል።ባለፈዉ ጥር ሊቢያ ዉስጥ ሠላም ለማዉረድ ጥሩ እመርታ ታይቷል ብለዉ የነበሩት የድርጅቱ ልዩ መልዕክተኛ ቤርናርዲኖ ሌዮን በርሊን ላይ ደግሞ ጊዜ የለም አሉ።

«ሊቢያ የቀራት ጊዜ የለም።ይሕ የመጀመሪያ መልዕክቴ ነዉ።ሊቢያ ሆነዉ የሚያዳምጡን ይሕንን መገንዘብ፤ ተጨባጭ ርምጃ መዉሰድና ጊዜዉ ደርሷል፤ በቃ፤ በቃ ነዉ ማለት አለባቸዉ።»

እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ወይም ዳአሽ ብሎ የሚጠራዉ ፅንፈኛ ቡድን ታጣቂዎችም እንደ አብዛኛዉ ሊቢያዊ ሁሉ የልዩ መልዕክተኛ ሌዮንን ወይም የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሽታይን ማየርን መልዕክት ሰምተዉት ይሆናል።ያዉም ሚስራታሕ-ሊቢያ ሆነዉ።

የፅንፈኛዉ ቡድን ታጣቂዎች የሊቢያዋን ሰወስተኛ ትልቅ ከተማ ሚስራታሕን በከፊል መቆጣጠራቸዉን ያስታወቁት የበርሊኑ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ነበር።

ISIS ሚስራታሕን መቆጣጠሩን ከማወጁ ጥቂት ቀደም ብሎ ቶብሮክ የሚገኘዉ ምክር ቤት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እንዲመሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቀረበዉን የመደራደሪያ ሐሳብ ዉድቅ አድርጎት ነበር።እራሳቸዉን እንደ ሰወስተኛ መንግሥት የሚዩት ግን የቶብሩኩን መንግሥት የሚደግፉት ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍታርም ከትሪፖሊ መንግሥት ጋር ተጣማሪ መንግሥት ይመስረት የሚለዉን ሐሳብ ዉድቅ አድርገዉታል።

በግብፅና በባሕሬን የሚደገፉት ጄኔራል ሐፍታር የጦር ጄቶችን ጨምሮ አብዛኛዉን የቀድሞ የሊቢያ ጦርንና ጦር መሳሪያን ይቆጣጠራሉ።ዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማትዋን እንደ አደራዳሪ ወደ በርሊን ስትልክ-ወደ ሊቢያ ያዘመቻቸዉ የጦር ጄቶችዋ ቅዳሜ ግዳይ መጣላቸዉ ተነገረ።የአሜሪካ የጦር ጄቶች በጣሉት ቦምብ አል ሙራብታን የተሰኘዉ ሚሊሺያ ቡድን መሪንና ተባባሪዎቻቸዉን መግደላቸዉን ቶብሩክ የሚገኘዉ መንግሥት ቃል አቀባይ አስታዉቋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ጦር ዛዦች መንግሥታቸዉ በአሸባሪነት የሚወነጅላቸዉ ሙክታር ቤልሙክታርን ያሉበትን አካባቢ ጄቶቻቸዉ መደብደባቸዉን አልካዱም።ሰዉዬዉ መገደል-አለመገደላቸዉን ለማረጋገጥ ግን ጊዜ-ያስፈልጋል ብለዋል።የልዩ መልዕክተኛዉ ሁለተኛ መልዕክት

«ከሁሉም ወገኖች ከሁሉም የሊቢያ ከተሞች የደረሱን መልዕክቶች ረመዳንን በሠላም ማክበር እንፈልጋለን የሚል ነዉ።»

ሠላም- አደፍራሹ ማን ይሆን? ገዳይ አስገዳዩስ? ሁለት ነገር ግን በርግጥ እዉነት ነዉ።ጉባኤተኞች ወደ በርሊን መጡ፤አወሩ፤ ከበርሊን ሔዱ።ሊቢያም ካየርም ከምድርም ቦምብ፤ጥይት ይወርድባታል።በነዳጅ በርሊን ምትክ አስከሬን ትቆጥራለች።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic