ሊቢያ፤ የተረሳዉ ጦርነት | ዓለም | DW | 25.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሊቢያ፤ የተረሳዉ ጦርነት

ሊቢያ የስድስት ሚሊን የሚገመተዉ ሕዝቧ የነብስ ወከፍ ገቢ ከአስራ-አራት ሺሕ ዶላር በላይ ነበር።ከዘጠና በመቶ የሚበልጥ ሕዝቧ የተማረ ነበር። በነዳጅ ላይ የተመሠረተዉ ምጣኔ ሐብቷ በአመት በአማካይ 10,5 ከመቶ ያድግ ነበር።ዛሬ ሐብት ንብረት-የሕዝቧ ቅምጥል ኑሮ አይደለም አንድ ሐገርነቷም ያዉ ነበር ነዉ።

ሠፊ፤በነዳጅ ዘይት የበለፀገች፤የሐብታም ሕዝብ መኖሪያ አንድ ሐገር ነበረች-ሊቢያ የምንላት።ለአርባ ሁለት ዘመን የገዟት ፈላጭ-ቆራጭ፤ አምባገነን ግን አንድ ብሔረተኛ ገዢ ነበሯት።ሙዓመር ቃዛፊ የሚባሉ።የዓለም የሐያላን፤ ሐገራት መሪዎች ሕዝባዊ አመፅን አሳበዉ ያዘመቱት ምርጥ ጦር የሐብታሚቱን ሐገር ሐብታም ሕዝብ ከጨቋኙ ገዢ «ነፃ» ማዉጣቱን ከነገሩን ሰወስት ዓመት ሊደፍን ሳምንታት ቀሩት።«ነፃ» የወጣዉ ሕዝብ ግን ዛሬ ይተላለቃል።ሐብታሚቱ-አንዲቱ ሐገር በገቢር ዛዊያ፤ ቶብሩክ፤ሚስራታ፤ቤንጋዚ፤ትሪፖሊ እየተባለ ብዙ ሆናለች።ጨቋኙ ግን አንዱ ገዢ በአንድ ሺሕ ሰባት መቶ ትናንሽ ገዢዎች ተተክተዋል።«ነፃ» ያወጣት ዓለምም ዘንግቷታል።

መሥከረም 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከመጋቢት ጀምሮ ሊቢያን ካየር፤ ከባሕር የሚያነደዉ የዓለም ምርጥ ጦር ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን የመግደል ወይም የማስገደል ግዳጁን ገና አልፈፀመም።እንደ ሊቢያ ሕንፃዎች፤ መንግድ፤ ድልድዮች ሁሉ የሐገሪቱን ጦር ሐይል የማዉደም ተልዕኮዉ ግን ባብዛኛዉ ግብ መትቷል።

የአገዛዝ ጥርስ፤ጥፍራቸዉ የረገፈዉ ቃዛፊ ርዕሠ-ከተማ ትሪፖሊን ጥለዉ ትዉልድ ሐገራቸዉ ሲርጥ አካባቢ እየተሽሎኮሎኩ ነዉ።መጀመሪያ በተናጥል ኋላ በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የሚታዘዝ ጦር ያዘመቱት የፈረንሳይና የብሪታንያ መሪዎች ገድል-ድላቸዉን ለማወጅ የጠላታቸዉን እስከሬን ግዳይ እስኪጥሉ መታገስ አልቻሉም።

ፕሬዝዳንት ኔኮላይ ሳርኮዚ ከፓሪስ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካምሩን ከለንደን ተጠራሩና ቤንጋዚ ወረዱ።መስከረም 15 2011 አስፎከሩ፤ እስጨበጨቡ፤ አስፈነደቁ።አሉምም።

«ቤንጋዚ፤ ሊቢያ፤ ፈረንሳይ እንኳን ደስ አላችሁ።የሊቢያና የፈረንሳይ ወዳጅነት ለዘላለም ይኑር።ቪቫ።»

የያኔዉ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላይ ሳርኮዚ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንም ቀጠሉ።

«እዚሕ ነጻይቲ ቤንጋዚ እና ነፃይቱ ሊቢያ መገኘት ሲበዛ አስደሳች ነዉ።አምባገነን አስወግዳችሁ ነፃነትን ስትመርጡ ከተማችሁ ለዓለም አብነት ሆናለች።የብሪታንያ ሕዝብ ለጀግንነታችሁ አክብሮቱን ይገልፃል።የቤንጋዚ ፤የትሪፕሊ፤የዚሊታን፤ የብሬጋ፤ የሚስራታ ሕዝብ አምባገነን ገዢን አስወግዳችሁ ነፃነት መምረጣችሁን ለዓለም ሕዝብ አሳያችሁ።»

የሊቢያ ሕዝብ እንደማንኛዉም የዓለም ሕዝብ ከአምባገነናዊ ሥርዓት መላቀቅ መፈለጉን ማወቅ የሚፈልግ የለንደን-ፓሪስ ፖለቲከኞችን ምስክርነት ማድምጥ በርግጥ አስፈላጊዉ አይደለም።ከአምባ ገነን ገዢዉ ለመላቀቅ እንደ ቱኒዚያ እና እንደ ግብፅ አጎራባቾቹ ሁሉ ካሜሩን አብዮት ያሉትን ሠላማዊ ትግል ጀምሮም እንደ ነበር ግልፅ ነዉ።

ግልፅ ያልሆነዉ የሠላማዊዉ አደባባይ ሠልፍ ተቃዉሞ ገና ከመጀመሩ ነፍጥ ያነሱ አመፃያንን እርምጃ በመደገፍ ምዕራባዉያን መንግሥታት ጦር ለማዝመት የተጣደፉበትን ትክክለኛ -ምክንያት እስካሁን የሚናገር መሪ አለመገኘቱ ነዉ።ያም ሆኖ መጀመሪያ ከፓሪስ፤ለንድን ዋሽግን ግልፅ ቃል ነበር።

«ከአረብ አብዮት መማር ሥላለብን ጉዳይ ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር ሙሉ ሥምምነት አለን።ለምሳሌ ሊቢያን በተመለከተ አንድ አይነት አቋም አለን።አቶ ጋዳፊ መወገድ አለባቸዉ።»

ፕሬዝዳንት ሳርኮዚ ግንቦት 2011።እርግጥ ነዉ ምዕራባዉያን መንግሥታት ከሊቢያ ተቀናቃኝ ሐይላት አንዱን (አማፂያንን) ደግፎ በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት የሚያስወግድ ጦር ማዝመታቸዉን የተቃወሙ፤ የሊቢያ ተቀናቃኝ ወገኖች ልዩነታቸዉን በድርድር እንዲፈቱ የጠየቁ፤ የሞከሩም ነበሩ።ግንባር ቀደሙ ሊቢያ የሰሜን አፍሪቃ ሶማሊያ እንዳትሆንበት የሠጋዉ የአፍሪቃ ሕብረት ነበር።

ቃዛፊን ለማጥፋት የቆረጡት የፓሪስ፤ ለንደን፤ ዋሽንግተን መሪዎች የደሐ-ደካማይቱን አሐጉር ማሕበር ሥጋት፤ ሐሳብ፤ዕቅድ ለመቀበል አይደለም ለማድመጥም አልፈለጉም።እና ቃል ገቢር ሆነ።ቃዛፊ ተገደሉ።ጥቅምት 20 2011

«ዛሬ ሙዓመር ቃዛፊ መሞታቸዉን የሊቢያ መንግሥት አስታዉቋል።ይሕ ለሊቢያ ሕዝብ የረጅሙ እና የአሳማሚዉ ምዕራፍ ፍፃሜ ነዉ።ከእንግዲሕ በአዲሲቱ ዴሞክራሲያዊት ሊቢያ የራሳቸዉን ዕድል የመወሰን መብት አላቸዉ።የቃዛፊ ሥርዓት ሊቢያን ለአራት-አስርታት በብረት ጡጫ ገዝቷታል።መሠረታዊ ሠብአዊ መብቶች ታፍነዉ ነበር።ንፁሕ ሠላማዊ ሰዎች ታሥረዋል፤ተገርፈዋል፤ ተገድለዋልም።የሊቢያ ሐብት ተመዝብሯል።»

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማ።የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ሥርዓት በአርባ ሁለት ዘመን አገዛዙ የገደለ፤የገረፈ፤ ያሰረ፤ካገር ያሰደዳቸዉ ሊቢያዉን ቁጥር በዉል አይታወቅም,።አንዳድ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ግን የተገደሉት በመቶ፤ የታሠሩና የተሰደዱት በሺ ይቆጠራሉ።የኔቶ ጦር እና የያኔዎቹ አማፂያን ከቃዛፊ ሕይል ጋር በገጠሙት ዉጊያ ግን ከሃያ-አምስት ሺሕ እስከ ሰላሳ አምስት ሺሕ የሚገመት ሊቢያዊ አልቋል።

ጋዛፊ ከነሥርዓታቸዉ ከተወገዱ በኋላ በንፃነት በሠላም፤ዲሞክራሲ ሥርዓት እንደሚኖር የተነገረለት የሊቢያ ሕዝብ በየጎጡ በሠፈሩ ታጣቂዎች መዋረድ፤መዘረፍ፤ መታሰር፤ መደፈር፤መገደል፤ መሸማቀቅ ከነዚሕ ለማምለጥ መሰደድ የመዓለት ወሌት ኑሮዉ አካል ነዉ።

ዴቪድ ካሜሩን የአብዮቱ መዘዉሮች መገኛ በማለት የዘረዘሯቸዉ ትሪፖሊ፤ቤንጋዚ፤ ሚሥራታ፤ብሬጋ፤ ዛዊያሕ፤ ቶብሩክ እና ሌሎችም ከአቅማቸዉ በላይ እብዙ ሥፍራ የተከፋፈሉ ታጣቂዎች ታጭቀዉባቸዋታል።ሶማሊያ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከርስ በርስ ጦርነት ስትገባ አብዛኞቹ የጦር አበጋዞች ለሁለት ግፋ ቢል ለሰወስት አዛዦች ያደሩ ነበሩ።ሊቢያ ግን ሲፈልጋቸዉ አካባቢን፤ ሲያሰኛቸዉ ሐይማኖትን፤ ሲያሻቸዉ ፖለቲካን ሽፋን ያደረጉ አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ታጣቂ ቡድናት በየአካባቢያቸዉ ነግሠዉባታል።

የሶማሊያ የጦር አበጋዞች ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾን በተቆጣጠሩበት ዘመን የሐገሪቱ የሽግግር መንግሥት ኢትዮጵያ ድንበር አጠገብ በምትገኘዉ ባይዶዎ ከትሞ ነበር። የሊቢያ የጦር ሚሊሺዎች ርዕሠ-ከተማ ትሪፖሊም፤ ሁለተኛይቱ ከተማ ቤንጋዚ፤ ሰወስተኛይቱ ከተማ ሚስራታም መቀመጫ ያሳጡት የሊቢያ ብሔራዊ ምክር ቤት ግብፅ አጠገብ ወደምትገኝዉ ቶብሩክ መሰደድ ግድ ነዉ የሆነበት።

ጀርመናዊዉ የሊቢያ ጉዳይ አጥኚ አንድርያስ ዲትማን እንደሚሉት የምክር ቤቱ መሠደድ የሊቢያ ማዕከላዊ መንግሥት ምንያሕል ደካማ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነዉ።

«አነሰም በዛ በሕዝብ የተመረጠዉ ምክር ቤት በፀጥታ መታወክ ምክንያት ርዕሠ ከተማ ትሪፖሊ ዉስጥ መቀመጥ አለመቻሉና ወደ በረሐማይቱ ከተማ ለመዛወር መገደዱ መንግሥቱም፤ ሐገሪቱም ምን ያሕል ደከማ መሆናቸዉን አመልካች ነዉ።»

ሊቢያ ሰወስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ አምስት ፕሬዝዳንቶች፤ ሰባት ጠቅላይ ሚንስትሮች ተፈራርቀዉባታል።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትና የያኔዎቹ አማፂያን «የቃዛፊ ጦር » በማለት የሐገሪቱን ፀጥታ አስከባሪ ሐይል በማዉደማቸዉ ያሁኑ መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ፀጥታ አስከባሪ የለም። ወይም ካለ አይቆጠርም።ማዕከላዊ ባንክ፤አየር መንገድ፤ፍርድ ቤት፤ ብሎ ነገር የለም።የሊቢያ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነዉ የነዳጅ ዘይት ጉርጓዶችን፤ ማከማቻዎችንና ማሰራጪያዎችን በአብዛኛዉ የሚቆጣጠሩት የየአካባቢዉ ሚሊሺያዎች ናቸዉ።

ሐገራቸዉን ጥለዉ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እስከተሰደዱበት እስከ 1988 ድረስ የሊቢያ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍታር የሚመሩት ሚሊሺያ ተዋጊ ጄቶች ድረስ ታጥቋል።ባለፈዉ ቅዳሜ የጄኔራል ሐፍታርን ሚሊሺያ አሸንፎ የትሪፖሊ አዉሮፕላን ማረፊያን የተቆጣጠረዉ የሚስርታ ሚሊሺያ የተሰኘዉ ታጣቂ ቡድን ደግሞ ታንክ ያሽከረክራል።

አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት በዋሽንግተን፤ለንደን ፓሪሶች ጥቅሻ የግብፁ መሪ አብዱልፈታሕ አልሲሲ፤የባሕሬን ንጉስ ሐማድ ቢን ኢሳ አል ኸሊፋ እና የሌሎች የአረብና የአፍሪቃ መሪዎች ከሊቢያ ሚሊሻዎች ታማኞቻቸዉን በመደገፍ ሊቢያን እያነኮሩ ነዉ።የትሪፖሊን አዉሮፕላን ማረፊያ የተቆጣጠሩትን የሚስራታ ሚሊሺዎችን ይዞታና ትሪፖሊን ሰሞኑን የደበደቡት የግብፅና የባሕሬን የጦር አዉሮፕላኖች እንደሆኑ ተዘግቦም ነበር።

አልሲሲ ከሕዝባዊ አብዮት በሕዋላ በሕዝብ የተመረጡ ፕሬዝዳንትን አስወግደዉ ሥልጣን የያዙ ጄኔራል፤ኸሊፋ የተቃጣባቸዉን ሕዝባዊ አመፅ በታንክ የደፈለቁ ንጉስ ናቸዉ።

ይሁንና ባለፈዉ ባለፈዉ ቅዳሜ ትሪፖሊን እና አዉሮፕላን ማረፊያዋን የደበደቡት ጄኔራል ሐፍታር የሚያዙት ጦር ጄቶች መሆናቸዉን ጄኔራሉ አስታዉቀዋል።ሊቢያ መንግሥት ተብየዉ ግን እስካሁን ያለ፤ያደረገዉ የለም።ለነገሩ በፖለቲካ ተንታኝ ዲትማን ቋንቋ በማጣጣር ላይ የሚገኝ መንግሥት ምን ሊል-ሊደርግስ ይችላል።

«የሊቢያ መንግሥት እንደሚያጣጥር በሽተኛ ነዉ»

ቃዛፊን ለማስወገድ በተደረገዉ ዉጊያ የወደመዉን የሊቢያን የመሠረተ ልማት

አዉታር ወደነበረበት ለመለስ አስር ዓመት እንደሚያስፈልግ ብዙ ባለሙያዎች ገምተዉ ነበር።የምዕራባዉያን ሐገራት መሪዎችም በዳግም ግንባታዉ፤ ሠላም፤ ዴሞክራሲን በማስረፁ ሒደትም ከሊቢያ ሕዝብ ጎን እንደማይለዩ ቃል ገብተዉ ነበር።

«ዩናይትድ ስቴትስ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር በመሆን ለሊቢያ ሕዝብ ድጋፍ የመስጠት ሐላፊነት አለባት።አብዮታችሁ ለድል በቅቷል።አሁን ደግሞ ክብር፤ነፃነትና መልካም እድል የሚሰጥ ሥርዓት ለመገንባት በምታደርጉት ጥረት አጋራችሁ ነን።»

ቃል በርግጥ በኖ ቀርቷል።ሊቢያ ዓለም አቀፍ እርዳታ አጥብቃ በምትሽበት ወቅት ትሪፖሊ እገጭ እጓ ስትል ደግሞ የምዕራባዉያን ሐገራት ዲፕሎማቶችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ሊቢያንም የሚያጓጓ ሐብቷንም ጥለዉ እየተግተለተሉ ዉልቅ አሉ።ሊቢያ የስድስት ሚሊን የሚገመተዉ ሕዝቧ የነብስ ወከፍ ገቢ ከአስራ-አራት ሺሕ ዶላር በላይ ነበር።ከዘጠና በመቶ የሚበልጥ ሕዝቧ የተማረ ነበር።የሕዝቧ አኗኗር ከአፍሪቃ ብዙ ጊዜ ሁለተኛ አልፎ አልፎ አንደኛ ነበር። በነዳጅ ላይ የተመሠረተዉ ምጣኔ ሐብቷ በአመት በአማካይ 10,5 ከመቶ ያድግ ነበር።ዛሬ ሐብት ንብረት-የሕዝቧ ቅምጥል ኑሮ አይደለም አንድ ሐገርነቷም ያዉ ነበር ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic