ሊቢያ የለዉጥ ጅምር አንደኛ አመት | ዓለም | DW | 20.02.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሊቢያ የለዉጥ ጅምር አንደኛ አመት

የያኔዉ እስረኛ-ያሁኑ ሚንስትር፥ ከያኔዉ ሚንስትር፥ ካሁኑ እስረኛ ጋር ሲነጋገሩ የተርቤልን ፅሑፍ ያነበበዉ፥ መታሰራቸዉን የሰማዉ አምስት መቶ ያሕል የቤንጋዚ ሕዝብ ፖሊስ ጣቢያዉን ከበቦ ይዘመር ፥ይፈክር ገባ። «ከዉጪ ጩኸት ሰማሁ።»

Karte Libyen Provinzen Tripolitania, Cyrenaica, Fezzan DW-Grafik: Olof Pock Libyen.jpg

200212

የአንድ ሐገር ዜጋ ናቸዉ።ሊቢያዊ።ግን ለአንድ ሐገር-ሕዝባቸዉ የሚያልሙ፣ የሚያደርጉት ያቃረናቸዉ፣ የሥልጣን ሙያ ጠልቅ ልዩነት ያራራቃቸዉ ሁለት ሰዎች።የዚያን ቀን ሲገናኙም የዓላማ-ምግባራቸዉ ቅራኔ የማይታረቅነቱን በማወቅና መጪዉን እኩል ባለማሳወቅም አንድ ነበሩ።የስለላዉ የበላይ አብዱላሕ ሴኑሲ ለብዙ ዘመን ብዙ ጊዜ ያደረጉትን መድገማቸዉን እንጂ፣ የመሪያቸዉን ሞት የሥርዓታቸዉን ዉድቀት ማፅደቃቸዉ መሆኑን አላወቁም።ወንጀለኛ ያሏቸዉን የመብት ተሟጋች ፈትሒ ተረቤል እንዲታሰሩ ፈረሙ።ተረቤል መጪዉን አላወቁም።ከዚያ በፊት እንደሚያዉቁት የሚደርስባቸዉን ሥቃይ የሚገደሉበትን ዕለት መቼነት እያሰላሰሉ እስር ቤት ተወረወሩ።ሮብ አመት ደፈነ።አርብ የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ አንደኛ አመቱ ተከበረ፣ የአመፁ አንደኛ አመት፥ የሁለቱ ሊቢያዉን አብነት፣ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መገደል በዉጤቱም የአርባ አንድ ዘመን አምባገናዊ ሥርዓታቸዉ መገርሰስ ከያኔዉ የሊቢያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል የበላይ ከመሐመድ ጀብሪል እኩል፣ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ለኒኮላ ሳርኮዚ፣ ለብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዴቪድ ካሜሩን ታላቅ ድል ነበር።

ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ለባራክ ኦባማ ደግሞ እራሳቸዉ ኦባማ ያኔ እንዳሉት ከመሐመድ ጅብሪል፥ ከሳርኮዚ፥ ከካሜሩን የድል ስሜት በለጥ፥ ካሁኑ የሊቢያ መሪ ከሙስጠፋ አብዱል ጀሊልም ደስታ አለፍ ያለ ዓይነት ነበር።አለምን የመምራት ብልሐት፥ ብቃታቸዉ ማረጋገጪያ፥ በዓለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት አል-ቃኢዳ ላይ የተቀዳጁት ድል ማጠናከሪያ ነበር።

ከሁሉም በላይ ኦባማ እንደተናገሩት የቃዛፊ መገደል መስተዳድራቸዉ የኢራቅና አፍቃኒስታኑን ጦርነት በድል አድራጊነት የማጠናቀቁ ዋቢ አድርገዉት ወይም መስሏቸዉ ነበር።ጥቅምት ሃያ፥ ሁለት ሺሕ አስራ አንድ (ዘመኑ በሙሉ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ከዋሽንግተን።

«ይሕ (የጋዛፊ መገደል) የሆነዉ የአሜሪካ አመራር በመላዉ ዓለም በተጠናከረበት ወቅት ነዉ።የአል ቃኢዳ መሪዎችን አስወግደናል፥በዉድቀት ጎዳና እንዲጓዙ አድርገናቸዋል።የኢራቁን ጦርነት እያጠናቀቅን ነዉ።የአፍቃኒስታንን ሽግግር ጀምረናል።አሁን ደግሞ ሊቢያ ዉስጥ ከወዳጆቻችንና አጋሮቻችን ጋር ያከናወነዉ ምግባር በሃያ-አንደኛዉ ምዕተ-ዓመት የጋራ እርምጃ ሊያከናዉነዉ የሚችለዉን አሳይተናል።»

የቃዛፊ መገደል፥ የሥርዓታቸዉ ዉድቀት፥ ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል እንደ ፖለቲከኛ፣ እንደ ሐገር ሽማግሌ፣ እንደ ሕግ አዋቂም የመሩት፣ የተቃዋሚ ስብስብ ድል የማድረጉ ዋቢ፣ እነ አብዱ ጀሊልን ለሥልጣን የማብቃቱ ማረጋገጪያ፣ ወይም እነሱ እንዳሉት የሊቢያን ሕዝብ ከጭቆና ብዝበዛ የመላቀቁ ዋስትና ብቻ አይደለም።በቃዛፊ ዘመን ብዙም ያልተጠቀመዉ የአዲሶቹ መሪዎች ጎሳ ፥ ተወላጆች የፖለቲካዉን ሥልጣንም የደለበዉን ሐብትም የአምበሳ ድርሻ ተጋሪ የመሆናቸዉ መሠረት ነዉ።

ለአብዛኛዉ ሊቢያ ደግሞ ያኔ ኦባማ እንዳሉት ከረጅም ዘመን አምባገነናዊ አገዛዝ የመላቀቅ ምኞቱ ስኬት፥የሰላም ነፃነቱ ተስፋ ብርቀት ነበር።

«እርግጥ ነዉ፥ከሁሉም በላይ የዛሬዉ ዕለት የሊቢያ ሕዝብ ነዉ።ዕለቱ ቃዛፊ ያሰቃያቸዉ እና ያጠፋቸዉ ወገኖቻቸዉን የሚያስታውሱበት እና የአዲስ ዘመን ቃል የሚያማትሩበት ነዉ።»

በርግጥም የሊቢያ ሕዝብ ከዚያ ቀን ለመድረስ ወዶም ሆነ ተገዶ፥ አዉቆም ሆነ-ሳያዉቅ ስምንት ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ በትንሽ ግምት ከሰላሳ ሺ በላይ ወገኖቹን ሕይወት ለቃዛፊ ጦር ታንክ፥ መድፍ አረር፥ ለሸሰማቂዎች መትረየስ ጥይት፥ ለኔቶ ጦር የአዉሮፕላን መርከብ ቦምብ-ሚሳዬል መገበር ነበረበት።ከሐምሳ ሺሕ የሚበልጡ ወገኖችን አካል የሰወስቱ ወገኖች ቦምብ-ሚሳዬል ጥይት-አረር ማብረጃ ማድረግ ነበረበት።

ከሞት፥ ቁስለት የዳነዉ ሊቢያዊዉ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት የሐብታም ሐገሩ ሐብት ንብረት፥ ሕንፃ፥ የመሠረተ-ልማት አዉታር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ሲለወጥ፥ ከትቢያ ሲቀየጥ ማየት ነበረበት።ሌላዉ ቀርቶ የየሐገሩ ፖለቲካ፥ ምጣኔ ሐብታዊ ሥርዓት አስመርሮት የተሻለ ኑሮ ነፃነት ፍለጋ የተሰደደ በሺ የሚቆጠር አፍሪቃዊ የባሕር ዉስጥ አዉሬ ሲሳይ መሆን ነበረበት።

ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከነልጆቻቸዉ፥ ከነልጅ ልጆቻቸዉ፥ ከነታማኝ አገልጋዮቻቸዉ ላጠፋዉ፥ የአርባ አንድ ዘመን ሥርዓታቸዉን ለገረሰሰዉ ጦርነት መለኮስ ሰበብ-የሆነዉ የቤንጋዚ ሕዝብ ተቃዉሞ ነበር።ተቃዉሞዉ የተጀመረበት አንደኛ አመት ባለፈዉ አርብ ሲከበር አንዲት የቤንጋዚ ወጣት ተማሪ እንዳለችዉ ቢያንስ ቤንጋዚ ብዙ ተቀይራለች።

«ፍፁም የተለየ ነዉ።አሁን መናገር እንችላለን።ሰዎች ሐሳባቸዉን በግልፅ ይለዋወጣሉ።ብዙ ለዉጥ አለ።»

ሻለቃ ሙዓመር ቃዛፊ የመሯቸዉ የጦር መኮንኖች ንጉስ ኢድሪስን ከሥልጣን ካስወገዱበት ከ1969 ጀምሮ በቃዛፊ ሥርዓት እንዳኮረፈ ጋዛፊና የቅርብ ባለሟሎቻቸዉ በወጡበት ጎሳ ላይ እንዳቄመ ከአርባ-አመት በላይ የቆየዉ የንጉሱ ዉልድና ጎሳ፥ የቤንጋዛ ከተማ ነዋሪም፥ ወገኖቹን ለትሪፖሊ ቤተ-መንግሥት ባበቃዉ አዲስ ለዉጥ የማይደሰት፥የማይፈነደቅበት ምክንያት የለም።

Libysche Übergangsregierung steht

የሽግግሩ መሪየቃዛፊ ሥርዓት ዉድቀት በመላዋ ሊቢያ የሠላም፥ እኩልነት መሠረት፥ የዲሞክራሲያዊ ነፃነት፥ የብልፅግና መደላድል ፈንጥቋል ማለት ግን ሲበዛ ያጠራጥራል።ባለፈዉ አርብ ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ቢሮ የወጣዉ መግለጫም ፕሬዝዳንቱ ባለፈዉ ጥቅምት ካሉት ጋር አይጣጣምም።

የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የመገናኛ ዘዴዎች ጉዳይ ሐላፊ ጄይ ካርኔይ ያወጡት መግለጫ አዲሶቹ የሊቢያ መሪዎች ሥለ ዉሳኔዎቻቸዉ ይበልጥ ግልፅ እንዲሆኑና የሁሉንም ሊቢያዊ መብት እንዲያከብሩ ያሳብባል።በዓለም አቀፉ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የሊቢያ ጉዳይ አጥኚ ካርስተን ዩርገንሰን እንዳሉት ደግሞ ሊቢያ ዛሬም ሥልጣን የያዘ፥ ወይም የታጠቀ ዘር፥ እየቆጠረ ወገን እየመረጠ ሰዉ የሚያሰቃይ-የሚገድልባት ሐገር ናት።

«ካለፈዉ ጥር አጋማሽ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሊቢያ ነበርን።ትሪፖሊ፥ ሚስራታና በየአካካቢያቸዉ የሚገኙ በርካታ እርስ ቤቶችን ጎብኝተናል።በነዚሕ እስር ቤቶች ያየነዉ ዘግናኝ ነበር።እስረኞቹ ተሰቃይተዋል።በሁሉም አይነት መሳሪያ ይደበደባሉ።እንደነገሩን በኤሌክትሪክ ንዝረት የተሰቃዩም አሉ።እኛ ከመድረሳችን ከአንድ ሰዓት በፊት እንኳን የተገረፉ እንደነበሩ ነግረዉናል።እኛም አዳዲስ ቁስል ያለባቸዉን ሰዎች አይተናል።አንዱ ባልደረባችን እንዲያዉም እዚያዉ በቆመበት እስረኞች ሲገረፉ አይቷል።በድብደባና ግርፋት ብዛት በየእስር ቤቱ ወዳጅ-ዘመዶቻቸዉ የሞቱባቸዉን ሰዎች አነጋግረናል።የግርፋት ቁስልና ጠባሳ የነበሩባቸዉ ሰዎች አስከሬኖች ተገኝተዋል።የእነዚሕ ሰዎች ቤተ-ሰቦች እስር ቤት ዉስጥ እንደሚሰቃዩት ሁሉ ፍትሕን ይጠይቃሉ።»

የመብት ተሟጋቹ ድርጅት አጥኚ ሊቢያ እስር ቤቶች ሥላዩ-ሥላጠኑት ከለንደን ሲናገሩ በቀደም አርብ፥ የሊቢያዉ የወጣቶች እና የስፖርት ሚንስትር ፈትሒ ተረቤል የአምና ይኼኔ ትዝታ፥ ሁኔታቸዉን ይተርኩ ነበር።ማክሰኞ ነበር የካቲት አስራ-አምስት።«አስቆሙኝና ከመኪዬ እንድወርድ አዘዙኝ።»

የሕግ ባለሙያዉ ከመያዛቸዉ ከሁለት ቀን በፊት የሊቢያ ሕዝብ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አገዛዝን በመቃወም አደባባይ እንዲወጣ የሚጠይቅ ፅሁፍ በኢንተርኔት አሰራጭተዉ ነበር።በተለይ በዚያ አመት ሐሙስ በሚዉለዉ የካቲት አስራ-ሰባት ሕዝቡ «የቁጣ ዕለት» ብሎ ብሶቱን ባደባባይ እንዲገልፅ ተርቤል ይጠይቃሉ።

የካቲት አስራ-ሰባት ለቤንጋዚዎች የቆየ በደል-የተፈፀበት ዕለትም ነዉ።ዴምንማርካዊዉ የካርቱን ሳዓይ የሳሉት ነብዩ መሐድን የሚያንቋሽሽ ካርቱን በየጋዜታዉ መታተሙንና የምዕራባዉያኑን አቋም የቤንጋዚ ነዋሪዎች ከኢጣሊያ ቆንስላ አጠገብ አደባባይ ወጥተዉ አዉግዘዉ ነበር።የካቲት አስራ-ሰባት ሁለት ሺሕ ስድስት።ለወትሮዉ ምዕራባዉያኑን የሚያወግዙ፥ የሚወነጅሉት ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከዚያ ጊዜ ጥቂት ቀደም ብሎ ከነ-ቡሽ፥ ከነ ብሌር፥ በዚያ ሰሞን ደግሞ ከነሳርኮዚ፥ ከነ ቤርሎስኪኒ የጀመሩትን ወዳጅነት ለመጠበቅ ሲሉ ሰልፈኛዉ እንዲበተን ያዛሉ።

ቤንጋዚዎች ቃዛፊን ተገደዉ እንጂ እሺ ብለዉ አያውቁም።ፀጥታ አስከባሪዎች ተኩስ ከፍቱ። አስራ-አራት ሰዉ ተገደለ።የቤንጋዚ ነዋሪ በተለይም ኢንተርኔት የሚያገኘዉ ወጣት የቱኒዚያ-ግብፆችን አመፅ ጀግንነት-ዉጤቱንም እየቀላወጠ፥ የካቲት አስራ-ሰባት ሲጠብቅ ነዉ-የሕግ ባለሙያዉን ፅሁፍ ያነበበዉ።

መልዕክቱ የቱኒዝ-ካይሮ የዘመናት ፖለቲካዊ ሥርዓትን የገለባበጠዉን ሕዝባዊ አብዮት በጥሞና ለሚከታተሉት፥ አብዮቱ ድንበር ተሻግሮ ወደ ደቡብ ዝቅ ቢል-የሚያከሽፉበትን ሥልት ለሚያብሰለስሉት ለትሪፖሊ ሹማምንት ልዩ ትርጉም ነበረዉ።እና መልዕክቱ እንደበተነ ወደ ቤንጋዚ የገቡት የሰለላዉ ድርጅት የበላይ አብዱላሕ አል-ሴኑሲ ፀሐፊዉ እንዲታሰሩ ወሰኑ።ፈረሙም።

French President Nicolas Sarkozy, right, gestures towards Libyan Transitional National Council chairman Mustafa Abdel Jalil, center, and Libyan Transitional National Council Prime Minister Mahmoud Jibri during the final press conference at the Elysee Palace in Paris, Thursday, Sept.1, 2011. World leaders and top international envoys started talks Thursday with Libya's rebel government about how to keep the country together and build a new democracy, after months of civil war and decades of dictatorship under Moammar Gadhafi. (AP Photo/Michel Euler)

የአዲሶቹ የሊቢያ መሪዎች አጋሮች

የሴኑሲን የትዕዛዝ ወረቀት የያዙት ነጭ ለባሾች ተርቤልን ከመኪናቸዉ አዉርደዉ ቤንጋዚ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ወረወሯቸዉ።«አለቀልኝ ብዬ ነበር።» አሉ በቀደም የዛሬዉ ሚንስትር።አካላቴ በጥይት ሲበጣጠስ ይታየኝ ነበር።» አከሉ። የዚያኑ ቀን ማታ ሴኑሲ ተርቤልን አስጠርተዉ ለሁለት ሰአታት ያሕል አነጋገሯቸዉ።

«አንዳዴ ያስፈራራኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ አድቤ እንድቀመጥ ይመክረኝ ነበር።»

የያኔዉ እስረኛ-ያሁኑ ሚንስትር፥ ከያኔዉ ሚንስትር፥ ካሁኑ እስረኛ ጋር ሲነጋገሩ የተርቤልን ፅሑፍ ያነበበዉ፥ መታሰራቸዉን የሰማዉ አምስት መቶ ያሕል የቤንጋዚ ሕዝብ ፖሊስ ጣቢያዉን ከበቦ ይዘመር ፥ይፈክር ገባ።
«ከዉጪ ጩኸት ሰማሁ።እና የመጨረሻዉ መጀመሪያ ይሆናል ብዬ አሰብኩ።» አሉ ተረቤል።

በዚያች ማታ ቤንጋዚ የተጀመረዉ ሕዝባዊ አመፅ የአርባ አንድ ዘመኑ-ሥርዓት የፍፃሜ መጀመሪያ መሆኑ አላነጋገረም።ሕዝባዊ አመፅ ግን እንደ ሊቢያ ጎረቤቶች በሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ተጀመረ-እንጂ በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ፥ በአደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ አልቀጠለም።ደም ባራጨ ዉጊያ ጦርነት አዝግሞ በብቀላ-ቂም ቁርቁስ ነዉ ያበቃዉ።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናሉ አጥኚ እንዳሉት ደግሞ የድሕረ-ቃዛፊዉ ሥርዓተ-አልበኝነት ከእስካሁኑም እንዳይብስ ነዉ ያሁኑ ሥጋት።

«ችግሩ ደግሞ እነዚሕ ሰዎች እስረኞቹን የሚቆጣጠሩት ሚሊሺያዎች ከሕግ በላይ መሆናቸዉ ነዉ።ያነጋገርናቸዉ ሕግ አስከባሪዎች በግልፅ እንደነገሩን ሚሊሺያዎቹ ማንም የሚቆጣጠራቸዉ የለም።እና አሁን ያለዉ ሥጋት የሊቢያ ሁኔታ ከእስካሁኑም ይበላሻል የሚለዉ ነዉ።»
ነጋሽ መሐመድ ነኝ ።ቸር ያሰማን

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic