ሊቢያ እና የእርዳታ ድርጅቶች መርከቦች | ዓለም | DW | 18.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሊቢያ እና የእርዳታ ድርጅቶች መርከቦች

ሊቢያ የእርዳታ ድርጅቶች መርከቦች ስደተኞችን ይስባሉ ትላለች ። እነርሱ ባይኖሩ ማንም ወደዚያ ዝር አይልም ነበር ይላሉ ባለሥልጣናትዋ። በዓለም አቀፍ የውኃ ክልል ላይ በባህር ኃይል ጀልባዎችዋ የህይወት አድን ሥራን ለማጠናከር የምትፈልገው ሊቢያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ መርከቦች በዚህ የውኃ ክልል እንዳይሰማሩ በጥብቅ ከልክላለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:35 ደቂቃ

ሊቢያ እና የህይወት አድን መርከቦች

የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሜዴትራንያን ባህር ላይ በሕይወት አድን ሥራ በተሰማሩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መርከቦች ላይ ጫና እያደረጉ ነው። መርከቦቹ ወደ ሊቢያ የባህር ክልል እንዳይጠጉ እንደሚከለከሉ አንዳንዴም ጥቃት እና የጥቃት ዛቻ እንደሚሰነዝርባቸው ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ ይናገራሉ። የሊቢያ ባህር ጠረፍ ጠባቂዎቹ የሕይወት አድን መርከቦቹ የሚያከናውኑት ሥራ ያደንቃሉ። ይሁንና ሥራውን ከነርሱ ጋር ተባብረው እንዲያከናውኑ እና የሀገሪቱንም ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ ይጠይቃሉ።
የአውሮጳ ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት በምህፃሩ ፍሮንቴክስ እንዳስታወቀው ባለፈው ሐምሌ ከሊቢያ ተነስተው በሜዲቴራንያን ባህር በኩል በጀልባ ኢጣልያ የደረሱ ስደተኞች ቁጥር በቀደመው ወር ከገቡት በግማሽ ያነሰ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ኢጣልያ የገቡት ቁጥር ወደ 10 ሺህ ይጠጋል። ኢጣልያ መድረስ የቻሉት ስደተኞች ቁጥር ከቀድሞው የቀነሰው የሊቢያ የባህር ጠረፍ

ጠባቂዎች ቁጥጥር በመጠናከሩ ነው ይላሉ የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት በምህጻሩ አይ.ኦ.ኤም ባልደረባ ጆኤል ሚልማን ፤
«የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ካለፈው ዓመት በበለጠ ተጠናክረው እየተንቀሳቀሱ ነው። ባለፉት ሰባት ወራት 11ሺህ ስደተኞች ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ከመነሳታቸው በፊት ነው የመለሷቸው።»
በያዝነው ነሐሴ ወር ከሊቢያ ወደ ኢጣልያ የሚጓዙት ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። የሕይወት አድን መርከቦች በሜዴትራንያን ባህር ላይ ስደተኞችን እንዳይታደግ ገደቦች ተጥለውባቸዋል። ሁኔታው ያላማራቸው የእርዳታ ድርጅቶች ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው። በነርሱ አስተያየት የአውሮጳ እና የሊቢያ ትብብር የስደተኞችን ሞት ያባብሳል ብለው ይሰጋሉ። 
በእጅ ስልክ የተቀረፀ አንድ ቪድዮ አንድ የሊቢያ ባህር ኃይል የጠረፍ ተቆጣጣሪ ጀልባ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ለሕይወት አድን ሥራ የተሰማራ «ፕሮአክቲቫ» ወደ ተባለ የስፓኝ የእርዳታ ድርጅት መርከብ ተጠግተው ሲተኩሱ ያሳያል። ይህ ከአንድ ሳምንት በፊት ነው የሆነው። ያኔ ምን እንደተፈጠረ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ባልደረባ ናስር አልካሙዲ ያስረዳሉ። 
«የባህር ዘባችን በድንገት የሕይወት አድን መርከቧን ያያል፣ የመርከቧን ሠራተኞች የሊቢያን የባህር ክልል ለቀው እንዲወጡ ስንጠይቃቸው እንቢ ስላሉ ለማስጠንቀቂያ ነው የተኮስነው።»

የሊብያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች እስከ እስካሁን ዘመናዊ የድንበር መቆጣጠሪያ መርከቦች የሏቸውም። የጠረፍ ጠባቂዎቹ ባልደረባ ኮሎኔል አሽራፍ አል ባዳሪ እንደሚሉት መርከቦቻቸው በማታ የሚያሳዩ መሣሪያዎች ወይም ካሜራዎች የሏቸውም።  ቢበዛ 5 ማይል መጓዝ ሲገባቸው አብዛኛውን ጊዜ ግን 35 ማይል ይሄዳሉ። ይህ አሁን ሊቀየር ይችላል። አውሮጳውያን ሊቢያ ስደተኞችን እንድታስቆምላቸው ድጋፍ እንደሚሰጧት ቃል ገብተውላታል። 
በተለይ ኢጣልያ ድጋፏን አጠናክራለች።  አንድ የመርከብ መለዋወጫዎች የያዘ የኢጣልያ የባህር ኃይል ጀልባ በቅርቡ ሊቢያ ገብቷል። በአሁኑ ጊዜም የጀልባው ሠራተኞች የሊቢያን መርከብ እየጠገኑ ነው። አዩብ ቃሲም የሊቢያ የባህር ጠረፍ ተቆጣጣሪ ባልደረባ እርዳታው አስፈላጊ ነው ይላሉ።
«የኢጣልያ ባህር ኃይል የውኃ ክልላችንን በመጠበቅ ይረዳናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ደግሞ ያለ ሊቢያ መርከብ ሊሆን የሚችል አይደለም።»
በአዩብ እምነት የእርዳታ ድርጅቶች መርከቦች ስደተኞችን ይስባሉ። ርሳቸው እንደሚሉት የግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ መርከቦች ባይኖሩ ማንም ወደዚያ ዝር አይልም ነበር። በዚህም የተነሳ ሊቢያ በዓለም አቀፍ የውኃ ክልል ላይ በባህር ኃይል ጀልባዎችዋ የህይወት አድን እና የፍለጋውን ሥራ ለማጠናከር ትፈልጋለች። ሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ መርከቦች በዚህ የውኃ ክልል እንዳይሰማሩ በጥብቅ ከልክላለች። እንደገና  አዩብ፤ 
«የሊቢያን ሉዓላዊነት ማክበር አለባቸው። የአውሮጳ ባለሥልጣናት ከሊቢያ መንግሥት ጋር እንጂ ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር መተባበር የለናቸውም»

 ዩርገን ሲራክ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች