ሊቢያ እና የኒዠር ወቀሳ | አፍሪቃ | DW | 30.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሊቢያ እና የኒዠር ወቀሳ

በሰሜናዊ ኒዠር ባለፈው ሣምንት በአጋዳዝ ከተማ አጠገብ በሚገኝ አንድ የጦር ሠፈር እና አርሊት በተባለችዉ ከተማ በሚገኘው አንድ የፈረንሳይ ኩባንያ የዩሬንየም ማውጫ ማዕድን ላይ ጥቃት የጣሉት አጥፍቶ ጠፊዎች ከሊቢያ የሄዱ ናቸው ስትል ኒዠር ወቀሳ ሰነዘረች።

default

የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ

የኒዠር ፕሬዚደንት ወቀሳውን የሰነዘሩት ጥቃቱ የተጣለበትን አካባቢ ከአንድ ቀን በፊት በጎበኙበት ጊዜ ነበር። ብዙ ሕይወት የጠፋበትን ጥቃት ተከትሎ ኒዠር ከሊቢያ ጋ በሚያዋስናት ድንበሯ ላይ ቁጥጥሯን አጠናክራለች።

በሰሜናዊ ኒዠር በሚገኘው የአጋዴዝ የጦር ሠፈር እና በአርሊት ባለው የሶሜር ማዕድን ላይ ባለፈው ሐሙስ ጥንዱን ጥቃት የጣሉት ፅንፈኞች ከደቡባዊ ሊቢያ ወደ ኒዠር መግባታቸውን የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ አስታውቀዋል። በጥቃቱ ሀያ አራት ወታደሮች እና በርካታ ሲቭሎች ሲገደሉ፣ የፈረንሣው ኩባንያ ማዕድኑን ዩሬንየም የሚያወጣበት የሶሜር ማዕድን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

«የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው በሊቢያ የታየውን ቀውስ ተከትሎ ነው። ከማሊ ጊዚያዊ ሁኔታ የተያያዘ አይደለም። ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ሊቢያን ለማረጋጋት ከጀመረው ተግባሩ ለማዘናጋት አትሞክሩ። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የሳህልን አካባቢ መረጋጋት የማደፍረስ ትልቅ ሥጋት ደቅናለች። »

Ali Seidan Ministerpräsident Libyen

የሊቢያ ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ዜይዳን

የምዕራብ አፍሪቃ የአንድነት እና የጂሀድ ንቅናቄ የተባለ እና አንድ ሌላ የፅንፈኞች ቡድኖች ለጥቃቱ ኃላፊነቱን በመውሰድ፣ ፈረንሣይ ባለፈው ጥር ወር በሰሜናዊ ማሊ በሚንቀሳቀሱ ሙሥሊም አክራሪዎች አንፃር ለጀመረች የጦር ዘመቻ ኒዠር ለሰጠችው ድጋፍ አፀፋ ርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል። የኒዠርን ጥቃት የጣሉት ፅንፈኞች መጡበት የተባለውን ደቡባዊ ሊቢያን በዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች የአሸባሪዎች መሸሸጊያ እና ለአሸባሪዎችም በሕገ ወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ ማቀበያ ቦታ አድርገው ይመለከቱታል። የሊቢያ ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ዜይዳን ግን የኒዠር ፕሬዚደንት ፅንፈኞች ከደቡባዊ ሊቢያ ወደ ኒዠር ገቡ ያሉበተን ወቅሳ እና የፖለቲካ ታዛቢዎች የሰነዘሩትን አስተያየት መሠረተ ቢስ ሲሉ አስተባበለዋል።

አዲሱ የሊቢያ መንግሥሥት ሽብርተኝነትን በቸልታ እንደማያልፍ በመግለጽ፣ የቀድሞ የሀገሪቱን መሪ ሞአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ለማውረድ ባደረገው ትግሉ የረዱትን በረካታ ቡደኖች አሁን የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለማስፈታት አየሰራ መሆኑን ዜይዳን አመልክተዋል። መንግሥታቸው ከያዘው ከዚሁ ሙከራ ጎን የሊቢያ ብሔራዊ ምክር ቤት የግጭት ቀጣና ብሎ ያወጀውን ደቡባዊውን የሀገሩን ከፊል እና ከማሊ ጋ የሚያዋስነውን ድንበሩን ቁጥጥር ማጠናከሩን የሊቢያ ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ዜይዳን ገልጸዋል። ባለፈው ሐሙስ በኒዠር የተጣለው ጥቃት ፈረንሣይ በሰሜናዊ ማሊ ዘመቻ ከጀመረች ከአምስት ወራትም በኋላ ሊቢያ አሁንም ጠቅላላው አካባቢው እንዳይረጋጋ ሥጋት መደቀንዋን ያሳየ መሆኑን ፕሬዚደንት ማሃማዱ ዬሱፉ አስታውቀዋል። በዚህም የተነሳ የኒዠር ፀጥታ ኃይላት የሀገራቸውን ፀጥታ ጥበቃ እንዲያጠናክሩ ትዕዛዝ መተላለፉን በአጋዴዝ የሚገኘው የራድዮ ኖማድ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢዝማዜል ኢግላላ አስረድተዋል።« ፀጥታ የማስጠበቁ ርምጃ አየተወሰደ ነው። ምክንያቱም የድንበሩ አካባቢ ጠንካራ ቁጥጥር የተጓደለው ነው። በዚህም የተነሳ የጠቅላላውን ግዛት ብሔራዊ ፀጥታ ተጠናክሮ እንዲጠበቅ ትዕዛዝ ተላልፎዋል። »የኒዠር ፕሬዚደንት ማሃማዱ ዬሱፉ አሸባሪዎቸ ጎረቤት ቻድን ቀጣይዋ ዒላማ ለማድረግ ማቀዳቸውን በመገለጽ ማስጠንቀቂያ አሰምተዋል።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic