ሊቢያ እና ምክር ቤታዊው ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 09.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሊቢያ እና ምክር ቤታዊው ምርጫ

ሊቢያውያን ሀገሪቱን ለአርባ ሁለት ዓመታት የገዙት የቀድሞው መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊ በሕዝብ ዓመፅ ከተወገዱ ወዲህ ባለፈው ቅዳሜ የብሔራዊ ምክር ቤት እንደራሴዎቻቸውን የመረጡ ሲሆን ፡ ሀገሪቱ ወደዴሞክራሲያዊው ሥርዓት ለመሸጋገር በያዘችው ሂደት ላይ ይህ የመጀመሪያው ርምጃ ሆኖ አግኝተውታል፤

ይሁንና፡ ይኸው የመጀመሪያ ነፃ የምርጫ ሂደት በሀገሪቱ በቀጠለው የጎሳ ግጭትና ሕዝብ ከምርጫ እንዲርቅ በቀረበ ጥሪ ጥላ አጥሎበታል። ለሞአመር በአርባ ዓመቱ የጋዳፊ አመራር ዘመን ምክር ቤትም ሆነ ሕገ መንግሥት አልነበረም። የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታምም ሆነ አባልነት በሞት ያስቀጣም ነበር። ዎች ጋዳፊ ከተገደሉ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሊቢያውያን ድምፃቸውን እንዲሰጡ መጠራታቸውን እንደ አዲስ ክስተት ነው የተመለከቱት። የመምረጥ መብት ያላቸው 2,8 ሚልየን ሊቢያውያን ሁለት መቶ መንበሮች ለሚኖሩት ምክር ቤት በተፎካካሪነት ከቀረቡ 3,800 ዕጩዎች እና ከ 140 ፓርቲዎች መካከል መምረጥ ይችላሉ። ግን በሀገሪቱ ዴሞክራሲያው ባህል ባለመኖሩ፡ ለብዙ መራጮች ድምፅ በሚሰጡበት ውሳኔአቸው ላይ ተወዳዳሪ ዕጩዎች ከየትኛው አካባቢ ወይም ጎሳ መጡ የሚለው ጉዳይ እንጂ የሚከተሉት የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ትርጉም እንደሌለው የሊቢያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል።


አዲስ የሚመረጠው ብሔራዊ ምክር ቤት ሀገሪቱን በጊዚያዊነት የሚያስተዳድር የሽግግር መንግሥት ያቋቁማል፤ ሕገ መንግሥታዊውን ምክር ቤትም ይሠይማል። ከዚያ መራጩ ሕዝብ ወደፊት በሚካሄደው ሁለተኛ ምርጫ በሚረቀቀው ሕገ መንግሥት ላይ ድምፁን ይሰጣል ። በነዳጅ ዘይት የተፈጥሮ ሀብት ለታደለችውና በአምባገነን ሥርዓት ሥር ለቆየችው ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር ልትወጣው የምትገባ ትልቅ ፈታኝ ሁኔታ ነው። ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተቀናቃኝ ቡድኖች፡ ባማፅያን ሚሊሺያዎችና በጎሳዎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች አሁንም አሳሳቢ ችግር የተደቀነባት ሲሆን፡ በምሥራቃዊው የሀገሪቱ ከፊል የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ኃይላት ሕዝቡ በዛሬው የብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫ እንዳይሳተፍ የተጠናከረ ጥሪ ሲያስተላልፉ ነው የቆዩት። ሊቢያን በወቅቱ የሚያስተዳድረው የሽግግሩ ምክር ቤት የፀጥታው ጥበቃ ከቁጥጥር እንዳይወጣ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ቢገኝም፡ በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች አሁንም ከባድ ውጊያ እንዳለ ነው የሚሰማው፤ በተለይ ብዙ የጦር መሣሪያ የሚዘዋወርበት ድርጊት ሁኔታውን አዳጋች አድርጎታል።
አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን