ሊቢያ፣ ሌላ ተኩስ አቁም፣ሌላ ቀዉስ | ዓለም | DW | 24.08.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሊቢያ፣ ሌላ ተኩስ አቁም፣ሌላ ቀዉስ

የተባበሩት መንግስት ድርጅትና ተፋላሚ ኃይላትን የሚደግፉ ሌሎች መንግስታትም ተኩስ አቁሙን መቀበላቸዉን በተከታታይ አስታዉቀዋል።ሊቢያዊ-አሜሪካዊዉ የቀድሞ ኮሎኔል ኸሊፋ ሕፍጣር ግን ተራዉ ሊቢያዊ የጓጓ፣የናፈቀ፣ ተስፋ የጣለበትን፣ ደጋፊ፣ አደራጅ፣ አስታጣቂዎቻቸዉን የተቀበሉትን፣ የተቀረዉ ዓለም የደገፈዉን ተኩስ አቁም ዉድቅ አደረጉት።ዕሁድ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:26

ሊቢያ፣ ሌላ ተኩስ አቁም፣ የሌላ ጦርነት ጥሪ

240820
ያቺ ሰፊ-በረሐማ፣ ግን ቱጃር-ስልታዊት ሐገር እንደ ስፋት፣ሐብት፣ ስልታዊነቷ ሁሉ አብዛኛ ሕዝቧ አንድ ዘር-የሚጠራ-አረብ፣ አንድ ቋንቋ የሚናገር-አረብኛ፣ የአንድ እምነት ተካታይ የሙስሊም ሕዝብ ሐገር ናት።ሊቢያ።የየዘመኑን ሑነቷን ያጠኑ እንደሚሉት የጥንት፣የድሮ ታሪኳ እንደ ብዙዉ ዓለም ሁሉ ብዙዎችን የሚያጣቅስ፣ የብዙዎች ስብጥር ዉጤት ነዉ።በ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኃያላን ዘምተዉባት ከትቢያ ከቀየጧት ወዲሕ ግን የዚያች ሐገር ፖለቲከኞች አንድ ቋንቋ እያወሩ፣አንድ ዕምነት እየተከተሉ አንድ ሕዝባቸዉን ብዙ ቦታ ከፋፋለዉ፣ እየፈጁ፣እያስፈጁ፣ እያፋጁትም ነዉ።ባለፈዉ ሐሙስ ከወደ ትሪፖሊ የተሰማዉ አዋጅ የዕልቂት-ፍጅት የጥፋት ዉድመት ጉዞዉን ለመግታት ደብዛዛም ቢሆን ተስፋ ሰጪ መስሎ ነበር።ትናንት ዕሁድን አለመሻገሩ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ።ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።
የጀርመንዋ መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ባለፈዉ ሐሙስ ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ጋር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ሊቢያን እንደ ሐገር ለመቅረፅ ሶስተኛ ወገን «ጣልቃ» መግባት ያለበት አይመስለኝም አሉ።
«ለእኛ አስፈላጊዉ ነገር፣ የሊቢያዉያንን ስልታዊ እንቅስቃሴ ለመገንዘብ ሊቢያ ሶስተኛ ወገን እንደማያስፈልጋት (መረዳት) ነዉ።ሊቢያን ቅጥ መያዝ የሚገባት በራሳቸዉ በሊቢያዉያን ነዉ።ከዚያ ግብ እንድትደረስ ግን ጀርመንና ፈረንሳይ በጋራ ይጥራሉ።»
ፈረንሳዊዉ Bernard-Henri Lévy (BHL ባጭሩ) በካይሮ-ግብፅ አድርጎ ቤንጋዚ-ሊቢያ በገባ ማግስት ከያኔዎቹ የሊቢያ አማፂ መሪዎች ጋር ተነጋገረ።መጋቢት 5 2011።ሰዉዬዉ ሲሻዉ ፈላስፋ፣ ሲያሰኘዉ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ሲፈልገዉ ፊልም አዘጋጅ ወይም ደራሲ፣ደግሞ ሲፈልገዉ አማካሪ፣ ብቻ ምናልባት አንዱንም

ያልሆነ ግን ሁሉንም መሆን የሚመኝ ዓይነት ሰዉ ነዉ።የዚያን ቀን አማካሪ መሆን አማረዉ።የግራ የፖለቲካ ፍልስፍናን ያቀነቅናል ነዉ የሚባለዉ።የዚያን ቀን አማካሪ ሆነ። የያኔዉ የ62 ዓመት አዛዉንት በኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ላይ ያመፁትን ሙስጠፋ አብዱል ጀሊልንና ሌሎች የቀድሞ የቃዛፊ ባለስልጣናትን ካነጋገረ በኋላ ከዚያዉ ከቤንጋዚ ስልክ የደወለዉ ለፖለቲካ እምነቱ ተቃራኒ ለቀኝ ፖለቲከኛዉ ለፕሬዝደንት ኒኮላ ሳርኮዚ ነዉ።ደዉለ። ሳርኮዚ አማፂያኑን በጦር ኃይል እንዲረዱ ምክር ብጤ ለገሰም።
ሳርኮዚ የሰዉዬዉን  ምክር መቀበላቸዉ ከተረጋገጠ ከሰዓታት በኋላ ሙስጠፋ አብዱል ጀሊልና ተባባሪዎቻቸዉ የሊቢያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ያሉትን የአማፂያን ድርጅት መሠረቱ።ሳርኮዚም መጀመሪያ የብሪታንያዉን ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንን፣ ቀጥለዉ የዩናይትድ ስቴትሱን አቻቸዉን ባራክ ኦባማን አሳምኑ።
በኃያላኑ ፍላጎት እና ፍቃድ ሁሉም የሚዘወረዉ የኒዮርኩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ለእነ ሳርኮዚ እብሪት ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ሁለት ሳምንት አልፈጀበትም።መጋቢት 19 2011። መጀመሪያ የፈረንሳይ፣ ቀጥሎ የብሪታንያ አሰልሶ መላዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር የሊቢያ መንግስትን ታንክ፣መድፍ፣ጄት ወታደርን ካየር-ከባሕር በቦምብ ሚሳዬል ያቀልጠዉ ገባ።
እርግጥ ነዉ (ኔቶ) የያኔዎቹን የሊቢያ አማፂያንን ደግፎ የሐገሪቱን መንግስት እንዲወጋ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መወሰኑን ከምዕራባዉን መንግስታት የታቀወሙት እንደ ሐገር-ጀርመን፣ እንደ ዲፕሎማት  ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ጊዶ ቬስተር ቬሌ ብቻ ነበሩ።ተቃዉሟቸዉ ያኔ ለትችት ወቀሳ፣ ለመገናኛ ዘዴዎች ፍጆታ፣ ኋላ ለታሪክ ዝክር ከመቀመጡ ግን ባለፍ የጦር ኃይል ወረራዉን አላስቀረም።
በዘጠነኛ ዓመቱ ዘንድሮ ሜርክል ለሊቢያ የሰወስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም ሲሉ ምናልባት እነቱርክ-ግብፅን ከመዉቀስ፣ ወይም ከፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ የአንገት በላይ ሽንጋለ ባለፍ ያንጀት መሆኑ ሲበዛ ያጠራጥራል። 

የሊቢያ የብሔራዊ ስምምነት መንግስት (GNA በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ)ን የመሠረተዉ ራሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነዉ።
እና ጣልቃ ገብነት ቦርማ ነዉ ፈንዝማ? 
GNA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉን የትሪፖሊ ጊዚያዊ መንግሥት የጥንቷ ሊቢያ ገዢ ቱርክ፣ የቀድሞዋ ሊቢያ ቅኝ ገዢ ኢጣሊያ እና ትንሺቱ ግን ቱጃሪቱ ቀጠር ይረዳሉ።ጊዚያዊ መንግስቱን የሚወጋዉ በጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣር የሚታዘዘዉን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር (LNA በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የተባለዉን ስብስብ የሊቢያ ጎረቤት፣ የቀጠርና የቱርክ ጠላት ግብፅ፣ የግብፅ ወዳጅና እንደግብፅ ሁሉ

የቱርክና የቀጠር ጠላት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሩሲያ እና በተዘዋዋሪም ቢሆን ፈረንሳይ ይደግፉታል።
ሐፍጣር፣ በ2017 ለጊዚያዊ መንግስቱ እዉቅና ነፍጎ መንበሩን ከትሪፖሊ ወደ ምሥራቃይቱ የሊቢያ ከተማ ቶብሩክ ያዞረዉ የሊቢያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር ሚንስትር ናቸዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሠረተዉ የትሪፖሊ መንግስት ባለፈዉ አርብ ተኩስ አቁም አወጀ።ተኩስ አቁሙን የቶብሩኩ ምክር ቤት ደገፈዉ።የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ አብዱላሕ ብላሂክ ለሊቢያ ሰላም የመጀመሪያዉ ርምጃ አሉትም።
«መጀመሪያ ተኩስ አቁሙን በመደገፍ፣ ቀጥሎ ሊቢያ የገቡ የዉጪ ቅጥረኛ (ወታደሮችን) በማስወጣት እና የነዳጅ ዘይት ምርትን በመጀመር የሊቢያ ፖለቲካዊ ቀዉስ መወገድ አለበት።ከነዳጅ ዘይት የሚገኘዉ ገቢ ፍትሐዊና ግልፅነት በተመላበት መንገድ መከፋፈል አለበት።»
እራሳቸዉን ፊልድ ማርሻል ብለዉ ለሚጠሩት ለጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣር ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጡት የግብፁ መሪ አብዱል ፈታሕ አልሲሲ ባለፈዉ ሐሙስ በትዊተር ባሠራጩት መልዕክትም ተኩስ አቁሙን ደግፈዉታል።
                                       
«የሊቢያ ፕሬዝደንታዊ ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጁትን ተኩስ አቁም እና በመላዉ ሊቢያ የሚደረገዉን ወታደራዊ ዘመቻዎች ለማቆም መወሰናቸዉን ተቀብዬዋለሁ።ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማግኘት ለሚደረገዉ ጉዞ፣ የሊቢያ ሕዝብ ዳግም መረጋጋት፣ ሰላምና ብልፅግና እንዲሰፍንለት ላለዉ ጉጉትም ጠቃሚ እርምጃ ነዉ።»
በርግጥ ተኩስ አቁሙ ለፖለቲከኞቹ የስልጣን ጥማት ጠብ፣ ዉዝግብ፣ ነዳጁን ለመቀራመት ለሚራኮቱት ለዉጪ ኃይላት ሽኩቻ፣ ሕይወት፣ አካል ኑሮ ሐብት ንብረቱን ለሚገብረዉ ሊቢያዊ ትልቅ ተስፋ ነዉ።የቶብሩኩ የፖለቲካ አዋቂ አላዕ ፋዚይ እንደሚሉት ደግሞ ትንሽም ቢሆኑ የሊቢያ የፖለቲካ መሪዎኞች ለሕዝብ ማሰብ፣ መብሰላቸዉንም ጠቋሚ ነዉ።
«ይሕ ፖለቲካዊ እርምጃ የሊቢያ የፖለቲካ መድረክን ከያዙት ፖለቲከኞች የተወሰኑት መብሰላቸዉን አመልካች ነዉ።እርግጥ ነዉ ርምጃዉ በጣም ዘግይቷል።ይሁንና ፈጣሪ ይመስገን አንዳድ ሰዎች ስለሰላም ማሰብ የመጀመራቸዉ ምልክት ነዉ።ወታደራዊ ዉጊያ ጥሩ መፍትሄ እንደማያመጣ የተገነዘቡ፣ ለመላዉ የሊቢያ ዜጋ እንደማይጠቅም፣ ሌላዉ ቀርቶ ለጎረቤት ሐገራትም እንደማይበጅ የተረዱ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነዉ።»
 የተባበሩት መንግስት ድርጅትና ተፋላሚ ኃይላትን የሚደግፉ ሌሎች መንግስታትም ተኩስ አቁሙን መቀበላቸዉን በተከታታይ አስታዉቀዋል።ሊቢያዊ-አሜሪካዊዉ የቀድሞ ኮሎኔል ኸሊፋ ሕፍጣር ግን ተራዉ ሊቢያዊ የጓጓ፣የናፈቀ፣ ተስፋ የጣለበትን፣ ደጋፊ፣ አደራጅ፣ አስታጣቂዎቻቸዉን የተቀበሉትን፣ የተቀረዉ ዓለም የደገፈዉን ተኩስ አቁም ዉድቅ አደረጉት።ዕሁድ።
ምክንያት? የሐፍጣር ቃል አቀባይ አሕመድ አል ሞስማሪ ትናንት  እንዳሉት የትሪፖሊዉ መንግሥት ተኩስ አቁም  ያወጀዉ ሥልታዊቱን የሲርት ከተማ ለመቆጣጠር እንዲመቸዉ ነዉ።«በዕይን ዉስጥ አሸዋ

ለመሞጀር» ያለመ-እንደቃል አቀባዩ።
ሊቢያዎች በርግጥ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸዉ።ፖለቲካጋ ሲደርሱ ግን ባንድ ቋንቋ እያወሩ፣ አንዱን ሕዝብ እየከፋፈሉ፣ ጥቅም በሚያጋጫቸዉ የዉጪ ኃይላት እየተነዱ ሕዝባቸዉን ቁልቁል እንደደፈቋት ነዉi።
ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ከወጣችበት ከ1951 ጀምሮ የገዟት ንጉስ መሐመድ ኢድሪስ ቢን መሐመድ አል መሕዲ አል ሱኔሲ  የያኔዋ ደሐ፣ ሰፊይቱን ሐገር ነፃነት እንደሳቸዉ የሚያስከብር፣ የ3 (ያኔ) ሚሊዮን ሕዝቧን ፍላጎት የሚያሟላ መሪ አይገኝም ባይ ነበሩ።የኢድሪሷ «ዉብ» ሊቢያ የሕዝቧ መሰቃያ የሆነችባቸዉ የ28 ዓመቱ ጎረምሳ ሻለቃ ሙዓመር ቃዛፊ ንጉሱን አሽቀንጥረዉ ጣሏቸዉ።1969።
ቃዛፊ በመጨረሻዉ የስልጣን ዘመናቸዉ በሰጡት መግለጫ የሳቸዉ ሊቢያ ለሊቢያዉያን «ጀነት ነች» ብለዉ ነበር።ሰዉ ግን «ጀነትንም ያማርራል» አከሉ።እነ  ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል ከቤንጋዚ «ጀሐነብ ነች» አሏቸዉ።የፓሪስ፣ለንደን፣ ዋሽግተን መሪዎችም እነ ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል የሚሉትን ብለዉ፣ ዓላማ ፍላጎታቸዉን ደግፈዉ «ጀሐነቧን» ሊቢያ «ሊያቀዘቅዙ» እሳት አወረዱባት።
በኔቶ ጦር ከመዉደሟ ከብዙ ዓመታት በፊት በረሐዋ ከ48 ቢሊዮን በርሚል በላይ ነዳጅ ዘይት መቋጠሩ ተረጋግጧል።ቃዛፊ እስከተገደሉ እስከ 2011 ድረስ በየቀኑ 1.65 ቢሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ይዛቅበት ነበር።የነዳጁ ዶላር ከ6 ሚሊዮን የማይበልጠዉን ሕዝብ ከግመል-ፍየል እረኝነት ወደ ዘመናይ መኪና አሽከርካሪነት፣ ከደሳ ጎጆ ነዋሪነት ወደ ሕንፃ ባለቤትነት፤ ከማይምነት ወደ ዘመናዊ ትምሕርት አዋቂነት ቀይሮት ነበር።
ዛሬ ግን የራሷ ዜጋ የሚሰቃይ፣ ሲከፋ የሚገደል፣ የዉጪ ስደተኛዋም የሚያልቁ-የሚሸጡባት ሐገር ናት።ሐብቷ ይወድማል።ይዘረፋል። ይባክናልም።የሊቢያ ብሔራዊ የነዳጅ ድርጅት እንዳስታወቀዉ የኸሊፋ ሐፍጣር ጦር በተለይ ሲርትና አካባቢዉ የሚገኙ የነዳጅ ማምረቻና ማስተላለፊያዎችን ባለፈዉ ጥር ከዘጋበት

እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ  ብቻ ሐገሪቱ ከ8.36 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች።በወር ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነዉ።
ከሞት፣ ስደት፣ የተረፈዉ ሕዝቧም፣ ሲርት አጠገብ የሚኖረዉ አብዱል መሐመድ እንዳለዉ ነገን በጭንቀት ይጠቅብቃል።«የሲርት ከተማ ነዋሪ አይደለሁም።ሕዝቡ ግን ሁሌም እንደተጨነቀ ነዉ።እንዴት እንደምገልፀዉ አላዉቅም።(ለብዙ ዓመታት) ጦርነት፣ፖለቲካዊ ቀዉስ፣ ዉዝግብ ያየ ሕዝብ ነዉ።ይፈራል።ስለሚመጣዉ ነገር ሁሌም እንደተጨነቀ ነዉ።»
የትሪፖሊ፣የቤንጋዚ፣ የቶብሩክ፣ የሚስራታ ነዋሪዎችም ሕይወት ከሲርቶች የተለየ ዓይደለም።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic