ሊቢያ፣ ሌላኛዋ የዉክልና ጦርነት ሐገር | አፍሪቃ | DW | 16.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሊቢያ፣ ሌላኛዋ የዉክልና ጦርነት ሐገር

ዩናይትድ ስቴትስ፥የእስራኤል፣የአረብና የአዉሮጳ ተከታዮችዋን አስተባብራ ሶሪያን ለመቆጣጠር ከሩሲያ፣ ከኢራንና ደጋፊዎቻቸዉ ጋር ተቃርነዉ ሶሪያዎችን ያጫርሳሉ፣ ጥንታዊ፣ታሪካዊቱን ሐገር ያወድማሉ።ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ ከየደጋፊዎቻቸዉ ጋር ጎራ ለይተዉ የመኖችን ይገድላሉ-ያጋድላሉም።ሊቢያም የዉክልና ጦርነት በማስተናገድ ሶስተኛዋ አረባዊት ሐገር ሆናለች

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:22

ሶስተኛዋ የዉክልና ጦርነት አስተናጋጅ ሐገር

ሰሜን አፍሪቃዊቱ አረባዊት ሐገር ሊቢያ ከሰላማዊ፣ ጠንካራ፣ ሐብታም፣ ሌሎችን ረጂ ማዕከልነት ወደ ጦር አበጋዞች መፈልፈያነት፤የአሸባሪዎች መፈንጪያነት ከተሸነሸነች፣ የስደተኞች መገደያ፣ መደፈሪያ፣ መሰቃያ፣ መሸጪያ መለወጪያ ገበያነት ከዘቀጠች ለዘጠኝ ዓመት ወራት ቀሯት።ዘንድሮም ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍጣር እንደ 2011ዱ (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) ሙስጠፋ አብዱጀሊል ከቤንጋዚ፣ ፈይዝ አልሳራጅ እንደ ሙዓመር ቃዛፊ ከትሪፖሊ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ይዛዛታሉ።አል ሲሲ እና ኤርዶኻን በርግጥ የ2011ዶቹን ሳርኮዚ፣ ካሜሩን ወይም ኦባማን አይደሉም።ግን የተበተነችዉን ሊቢያን ይበልጥ ለማጥፋት ወይም ለመጠፋፋት ለሚዛዛቱት ኃይላት መጠፋፊያ ያቀብላሉ።ዛቻ-ዘመቻዉ መነሻ፣ ዳራዉ ማጣቃሸ እድምታዉ ድረሻችን ነዉ። 
                                     
ኒኮላ ሳርኮዚ ከፓሪስ፣ ዴቪድ ካሜሩን ከለንደን፣ ባራክ ኦባማ ከዋሽግተን ተባባሪ፣ደጋፊያቸዉን አስከትለዉ መጋቢት 2011 ሊቢያን ያስደበደቡት፣ የሊቢያን ሕዝብ ከሊቢያዊ ገዢዉ «ነፃ ለማዉጣት» ብለዉ ነበር። እነ ሳርኮዚ ያዘመቱት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር የሊቢያን የረጅም ጊዜ ገዢን፣ የልጅ-ቤተሰባቸዉን ሕይወት ከነሥርዓታቸዉ መግደል-ማስወገዱ እርግጥ ነዉ።
የፓሪስ-ለንደን-ዋሽግተን መሪዎች «ነፃ ያወጧት»ን ሐገር ለስደተኞች ቄራነት፣ ለአሸባሪዎች መፈልፈያ፣ ለጦር አበጋዞች መፈንጪያነት ማስረከባቸዉም ሐቅ ነዉ።የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማም 2011ዱ ጥፋት የአሜሪካን ዲፕሎማቶች ሕይወት ሊቢያ ዉስጥ እስኪያጠፋ ድረስ ዘገዩ እንጂ አልካዱትም።
                                    
«ይሕን ጣልቃ ገብነት የምናደርግ ከሆነ፣ ቃዛፊ ከተወገዱ በኋላ መደረግ የሚገባዉን ነገር እኛም አዉሮጶችም ብዙም አላሰብንበትም ነበር።«እሜሪካ እናመሰግናለን» የሚለዉ መልዕክት ሲያስደስተን፣ ጥሩ ስሜት ሲፈጥርብን፣ ያኔ፣ ማሕበረሰብ (ሐገር) ዳግም ለመገንባት ጥረት መደረግ ነበረበት»
ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ።2016።የእነ ኦባማ ስሕተት በይፋ ከመነገሩ ባለፍ የሊቢያ የጦር፣ ዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ መሪዎችን ሆነ የዉጪ ደጋፊዎቻቸዉን ያስተማረዉ ነገር አለመኖሩ ነዉ ዚቁ።መንበሩን ቶብሩክ-ምሥራቅ ሊቢያ ያደረገዉ፣ እንዳዴ የምስራቅ ሊቢያ ምክር ቤት ተብሎ የሚጠራዉ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብዱላሕ አ-ሳኒ በቀደም እንዳሉት ያቺ ሐብታም፣ሰፊ፣ስልታዊ ሐገር ዛሬ በከባድ እሳተ ጎሞራ እንደተናወጠ አካባቢ ናት።ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሚሉት ሊቢያን የገለባበጠዉ ነዉጥ የሚቆመዉ ግን በሌላ ነዉጥ ነዉ።ጦርነት።
«ሊቢያ ዉስጥ ባለፉት ዓመታት የሆነዉ ከባድ እሳተ ጎሞራ ነዉ።በ2014 እና 2013 ከነበረዉ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ፈጣሪ ምስጋና ይግባዉና እድሜ ለሊቢያ ብሔራዊ ጦር እና ለጠቅላይ አዛዡ ቤንጋዚ፣

ደራን እና ደቡባዊ አካባቢዎች ላይ ድል ተቀዳጅተዋል።አሁን ትሪፖሊ አጠገብ ናቸዉ።»  
ሊቢያ ዛሬ ከ50 ሺሕ የሚበልጡ በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ስደተኞች ይሰቃዩባታል።አ-ሳኒ የሚመሩትን እዉቅና የለሽ መንግስትን ጨምሮ ሶስት «ጠንካራ» ኃይላት፣ በየጎጡ የተደራጁ በመቶ የሚቆጠሩ የሚሊሺያ ቡድናትን አሰልፈዉ ይፋጁባታል።

ከአሳኒ-መንግሥት ሌላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሰረተዉ የሊቢያ የብሔራዊ ስምምነት መንግስት ትሪፖሊን ይቆጣጠራል።ከአሳኒ መንግስት ጋር ያበሩት እራሳቸዉን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ብለዉ የሰየሙት ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍጣር ቤንጋዚ ላይ ሆነዉ ትሪፖሊዎችን ለማጥፋት ይዝታሉ።ቱርክ-እና ግሪክ፣ ግብፅ ወይም ሳዑዲ አረቢያና-ቀጠር የቆየ ቂም በቀላቸዉን ማራገፊያ አድርገዋታልም።

ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ትሪፖሊ አካባቢ በሸመቁ ሚሊሺያዎች በሚደገፈዉ መንግሥት እና ሐፍጣር በሚያዙት ጦር መካከል ካለፈዉ ሚያዚያ እስካለፈዉ ሕዳር በተደረገዉ ዉጊያ ብቻ ከ1200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ሶስት መቶ ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ ተፈናቅሏል።በየስፍራዉ የተገደለ፣የታገተ፣አካሉን ያጣዉን ስደተኛ አፍሪቃዊ

እስካሁን በቅጡ የቆጠረዉ የለም።
በአ-ሳኒ ቃል እሳተ ጎሞራዉ ግን ቀጥሏል።ጄኔራል ሐፍጣር የ26 ዓመት ወጣት የጦር መኮንን በነበሩበት በ1969 ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የመሩት መፈንንቀለ መንግስት ተባባሪ ነበሩ።በ1987 ቻድ ዉስጥ በተደረገዉ ዉጊያ ተማረኩ።ከምርኮ እንደተለቀቁ በአሜሪካኖች ተመልምለዉ፣ የቀድሞ አለቃቸዉን ከስልጣን ለማስወገድ 350 ወታደሮችን አስከትለዉ ዉጊያ ከፈቱ።
ሲሸነፉ አሜሪካኖች፣ አሜሪካ አስገብተዉ ያኖሯቸዉ ያዙ።በቃዛፊ ዘመን የአሜሪካኖች ሰላይ መሆናቸዉ ይታመን ሥለነበር በሊቢያዎች ዘንድ ሲወገዙ፣ ሲወቀሱ የኖሩት ጄኔራል በቅርቡ ሊቢያን ከዘራፊዎችና ቀማኞች «ነፃ ለማዉጣት» የሚፋለሙ «ሐገር ወዳድ» ይባሉ ይዘዋል።ባለፈዉ ሚያዚያ ትሪፖሊን በዕለታት እድሜ ለመቆጣጠር ዝተዉ ነበር።እንደ ቻዱ ዉጊያ ከዛቻ አላለፈም።
ባለፈዉ ሳምንት እንደገና ፎከሩ።ጦራቸዉ ዓለም አቀፍ እዉቅና ያለዉን የጠቅላይ ሚንስትር ፈይዝ አል ሳራጅን መንግስት መነቃቅሮ ለመጣል የሰዓት እድሜ ነዉ የቀረዉ እያሉ።
 «ትሪፖሊ የወንጀለኞች መሸሸጊያ ሆናለች።ትሪፖሊ ባለስልጣናት ሕዝቡን በጠመንጃ ኃይል አስገድደዉ እየገዙት ነዉ።ትሪፖሊ የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን ተቆጣጥረዉ የሊቢያ ሕዝብን ሐብት በጠራራ ፀሐይ ይዘርፋሉ።ስለዚሕ ትሪፖሊን የቀፈደዳትን ሰንሰለት ለመበጠስ ዛሬ ወሳኝ ዉጊያ ለመክፈት መወሰናችንን አስታዉቃለሁ።ጥቃቱ፣ ለትሪፖሊ ሕዝብ ደስታ ለማጎናፀፍ፣ ከተማይቱን በታሪክ እንደምትታወቀዉ የስልጣኔ ርዕሠ-ከተማ ለማድረግ ያለመ ነዉ።»
ጠቅላይ ሚንስትር ፈይዝ አል-ሳራጅ ዓለም አቀፍ እዉቅና ይኑረዉ እንጂ ከትሪፖሊ ዉጪ የሚቆጣጠር አካባቢ ብዙም የለም።ይሁንና አል ሳራጅ የሐፍጣርን ዛቻ ለማጣጣል አልሰነፉም።«ቅዠታም» አሏቸዉ ጄኔራሉን።
  «ዉድ ነፃ ወገኖቼ ሆይ! የእኒያ ዉሸታሞችን ቅዠት እንዳትምኑ።ቃላትና አሉባልታዎቻቸዉን እንዳትቀበሉ።ለትሪፖሊ የመጨረሻ የሚባል ሰዓት የለም።ያለዉ ቅዠት ነዉ።ትሪፖሊን መቆጣጠርም ሆነ መዉረር ብሎ ነገር የለም።»
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በ2015 ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሰረት የሊቢያ ሕጋዊ መንግስት በአል-ሳራጅ የሚመራዉ የትሪፖሊ መንግስት ነዉ።ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በግልፅ የሚደግፉት ግን የአል-ሳራጅን መንግስት ለማፍረስ የሚዋጉትን ጠንካራዉን ጄኔራል ነዉ።
ፈረንሳይ እና ሩሲያም ወደ ጄኔራሉ

ያደላሉ ነዉ የሚባለዉ።የሞስኮ መንግስት እዉቅና ይኑራቸዉ አይኑራቸዉ አልተረጋገጠም እንጂ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ከሐፍጣር ጦር ጎን ሆነዉ እንደሚዋጉ የሐፍጣር ወታደሮችን እንደሚያማክሩም መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ ሚያዚያ ለጄኔራል ሐፍጣር ስልክ ደዉለዉ «በፀረ-ሽብር ዘመቻዉ የጋራ ጉዳይ ላይ» ከመነጋገራቸዉ ባለፍ ዩናይትድ ስቴትስ የምትደግፈዉን ኃይል በስም አልጠቀሰችም።ይሁንና ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ፕሬዝደንቱ ዓለም አቀፍ ቅዉቅና ያለዉን መንግስት መሪዎች አግልለዉ ጄኔራሉን ማነጋገራቸዉ ራሱ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለማን እንደቆመች መስካሪ ነዉ።
ከሳዑዲ አረቢያ እና ሳዑዲ አረቢያ ከምትመራቸዉ ግብፅና አረብ ኤምሬቶችን ከመሳሰሉ መንግስታት ጋር አይና ናጫ የሆነችዉ ትንሺቱ ሐብታም አረባዊት ሐገር ቀጠር የድሮ አቋሟን ቀይራ ድጋፏን ለትሪፖሊ መንግስት እየሰጠች ነዉ።
በሊቢያ ጉዳይ አድፍጣ የቆየችዉ ቱርክ በቅርቡ ከትሪፖሊዉ መንግሥት ጋር የባሕር ኃይል የጋራ መከላከያ ስምምነት በተፈራረመች ማግስት፣የቱርክ ፕሬዝዴንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን እንዳሉት የትሪፖሊን መንግስት ከጥቃት የሚከላከል ጦር ያዘምታሉ።
«ሊቢያ የኛን ድጋፍ ከጠየቀች፣ በተለይ በቅርቡ ወታደራዊ ስምምነት ከተፈራረምን ወዲሕ፣ ሊቢያ የምትፈልገዉን ያሕል ወታደራዊ ኃይል እናዘምትላታለን።ወታደራዊ ስምምነት በማድረጋችን ምንም ዓይነት እንቅፋት የለብንም።»
እንቅፋት።እንቅፋቱ የሕግ ወይም የስምነት ጉዳይ እንዳልሆነ ፕሬዝደንቱ በርግጥ አላጡትም።አልቀረምም።የሐፍጣር ዛቻ የተሰማዉ ኤርዶኻን ያሉትን ባሉ በሁለተኛዉ ቀን ነበር።የሐፍጣር ዛቻ በተሰማ በሳልስቱ ደግሞ የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታሕ አል-ሲሲ የአንካራ-ትሪፖሊን ዉል ወረቀት ላይ ለማስቀረት እንደሚያሰሩ

በተዘዋዋሪ ግን ቴሊቪዥን ካሜራ ፊት አረጋገጡ።
«ባለፉት ዓመታት ሊቢያ ዉስጥ የሚሆነዉ እና የሐገሪቱ መንግስት ትሪፖሊ ዉስጥ እንኳን በነፃነት የማይንቀሳቀሰዉ የሚሊሺያዎችና የአሸባሪዎች ታጋች በመሆኑ ነዉ።»
የቱርክ እና የትሪፖሊ መንግስታት ስምምነት እንደተሰማ የቱርክ የረጅም ጊዜ ባላንጣ ግሪክም ተንደርድራ ከተልዕኮዉ ጦርነት ተመስጋለች።ቱርክና ግሪክ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባላት ናቸዉ።ግን ግሪክ ከቱርክ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ከ1832 ወዲሕ ጠላቶች ናቸዉ።ግብፅ፣ሳዑዲ አረቢያና ቀጠር የዓረብ ሊግ አባላት ናቸዉ።ከ2015 ወዲሕ ግን ጠላቶች ናቸዉ።
ዩናይትድ ስቴትስ፥ የእስራኤል፣ የአረብና የአዉሮጳ ተከታዮችዋን አስተባብራ ሶሪያን ለመቆጣጠር ከሩሲያ፣ ከኢራንና ደጋፊዎቻቸዉ ጋር ተቃርነዉ ሶሪያዎችን ያጫርሳሉ፣ ጥንታዊ፣ታሪካዊቱን ሐገር ያወድማሉ።ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ ከየደጋፊዎቻቸዉ ጋር ጎራ ለይተዉ የመኖችን ይገድላሉ-ያጋድላሉም።ሊቢያም የዉክልና ጦርነት በማስተናገድ ሶስተኛዋ አረባዊት ሐገር ሆናለች። ቸር ያሰማን። 

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic