ሊቢያና የየአገራቱ ተቃዉሞ | ዓለም | DW | 23.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሊቢያና የየአገራቱ ተቃዉሞ

የተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት የሊቢያ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ማዋከቡን አዉግዞ፤ ጥቃት እንዲያቆም ጠየቀ።

default

የሊቢያዉ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ግን ደጋፊዎቻቸዉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ኃይል እንዲጠቀሙ በማበረታታት ስልጣን እንደማይለቁ ትናንት አስታዉቀዋል። እንዲያም ሆኖ አንድ ምስራቃዊ የአገሪቱ ግዛት ከጋዳፊ መንግስት ቁጥጥር ስር ነፃ መሆኑ ሲገለፅ አንዳንድ ባለስልጣናትም ተቃዋሚዎች ላይ የሚወሰደዉን የኃይል ርምጃ በመቃወም ስራቸዉን ለቀዋል። የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸዉን ከሊቢያ ማስወጣቱን ተያይዘዉታል። ወቅታዊዉን የሊቢያን ሁኔታ የሚመለከቱ ዜናዎችን ሸዋዬ ለገሠ አሰባስባለች።

ከአርባ ዓመታት በላይ ስልጣን ላይ በመክረም የዝንተዓለም ገዢ ለመሆን የቆረጡት ሙአመር ጋዳፊ ወትሮም አብዮተኛ እንጂ ፕሬዝደንት አልነበርኩም ሲሉ፤ ከአገር ወጥተዋል የሚለዉን ጭምጭታ ባንኳሰሰዉ ንግግራቸዉ ፎክረዋል። አያይዘዉም እሳቸዉና ባልደረቦቻቸዉ ስልጣን ለሕዝቡ ካስተላለፉ አራት አስትር ዓመታት መቆጠራቸዉን በመጠቆም፤ ኃላፊነቱን በአቅባቡ ያልተወጣዉ ወገን ተጠያቂ እንደሚሆን አመልክተዋል።

«እኔና ነፃ መኮንን ባልደረቦቼ ስልጣኑን በ1977 ለሕዝብ አስረክበናል፤ ከዚህ በኋላ ስልጣንም ሆነ ኃይል የለንም። ስልጣንና ኃይላችንን ለሕዝቡና ለሕዝቡ መማክርት ሰጥተናል። እነሱ ኃላፊነታቸዉን በትክክል መወጣት አለመወጣታቸዉን የሚወስነዉ ሕዝቡ ነዉ። ከ197ጀምሮ ስልጣን ለመያዝ የሚደረገዉ ሽኩቻ አብቅቷል። ከዚያ ወዲህ እኔና ጓደቼ ሊቢያ ለምታደርገዉ ትግል ብቻ ነዉ ተጠያቂነታችን።»

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የጋዳፊ ንግግር ፍርሃት ያዘለ ነዉ ብለዉታል። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለም የጋዳፊ ርምጃ በሊቢያ ካልተስተካከለ አገራቸዉ ማዕቀብ ልትጥል ትችላለች ሲሉ አስጠንቀዋል። ምንም እንኳን ጋዳፊ ባለስልጣኖቻቸዉ ከጎናቸዉ እንደቆሙ ቢናገሩም የአገር ዉስጥ ሚኒስትራቸዉ አብዱል ፋታህ ዩኑስ ከተቃዋሚዉ ጎራ መሰለፋቸዉን ይፋ አድርገዋል። በፕሬዝንቱ ደጋፊዎች የመግደል ሙከራ እንደተደረገባቸዉ ያስታወቁት ፋታህ ዩኑስ ከእንግዲህ ሚኒስትር ሳይሆኑ ሕዝቡን የሚያገለግል ወታደር እንደሆኑ አመልክተዋል። ቀደም ሲል የእኝህኑ ሰዉ ሞት ጋዳፊ ማወጃቸዉን የጀርመኑ የዜና ወኪል DPA ዘግቧል። ጋዳፊ የገዛ ሕዝባቸዉ ላይ መዝመታቸዉ ሌሎች ባለስልጣናቶቻቸዉንም አሳጥቷቸዋል። በተመድ የሊቢያ ተወካይ አምባሳደር ኢብራሂም ዳባሺ በሊቢያ ሕዝብ ላይ እልቂት አዉጀዋል ላሏቸዉ ጋዳፊ መላዉ ዓለም መሸሸጊያ እንዲነፍግ አሳስበዋል፤

«ድርጊቱ በሊቢያ ሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነዉ ከሚል ድምዳሜ ደርሰናል። ከጥር 7ቀን ጀምሮ የጋዳፊ ገዢ ቡድን የሊቢያን ሕዝብ ዘር በመፍጀት ላይ ነዉ። በዓለም የሚገኙ አገሮች ጋዳፊ በግዛታቸዉ እንዲሰወሩ እንዳይፈቅዱ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤ በተጨማሪም ከሊቢያ ሊወጣ የሚችል የትኛዉንም የገንዘብ መጠን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ አሳስባለሁ።»

ከእሳቸዉ በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ የሊቢያ አምባሳደር አሊ አድጃሊም እንዲሁ ጋዳፊ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል። በህንድና ባንግላዲሽ የሊቢያ አምባሰደሮችም ሕዝቡ ላይ ጦርነት ከፍቷል ያሉትን የጋዳፊን መንግስት እንደማይወክሉ በመጠቆም ሥራቸዉን ለቀዋል። ኦስትሪያ የሚገኘዉ የሊቢያ ኤምባሲ በበኩሉ ድርጊቱን ተቃዉሞ ሰላማዊዉን ህዝብ የሚከላከል ርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል።

Libyen Innenminister Abdulfattah Junis schließt sich Aufstand an

የሊቢያ የአገር ዉስጥ ሚኒስትር

ዛሬ ደግሞ የጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ከፍተኛ ረዳት የሆኑት ዩሱፍ ሳዋኒ የመንግስታቸዉን ርምጃ በመቃወም ከኃላፊነታቸዉ መነሳታቸዉን ለሮይተር በላኩት መልዕክት አስታዉቀዋል። ሊቢያ ዉስጥ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ለጊዜዉ በትክክል መግለፅ ባይቻልም ወደአንድ ሺ እንደሚደርሱ የጣሊያን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንኮ ፍራቲኒ አመልክተዋል። ፍራቲኒ ትሪፖሊ የሚገኘዉን ኤምባሲያቸዉን በመጥቀስም የሊቢያ ምስራቃዊ ግዛት ከጋዳፊ መንግስት ቁጥጥር ዉጭ መሆኗን ገልጸዋል።     

የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን አገራቸዉ የሊቢያን ጉዳይ በተጠንቀቅ እየተከታተለች መሆኗን አመልክተዋል፤

«ዩናይትድ ስቴትስ የሊቢያን ሁኔታ በተጠንቀቅ መከታተሏን ትቀጥላለች። ሃሳባችንና ጸሎታችን ህይወታቸዉን ካጡትና ከወዳጆቻቸዉን ጋ ነዉ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ መገደላቸዉንና በርካቶችም መጎዳታቸዉን የሚያመለክት መረጃ ስለሚደርሰን ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ጥቃቱን አስመልክቶ በሚያሳልፈዉ ጠንካራ ዉግዘት ተባባሪ ነን። ይህ ደም መፋሰስ ፍፁም ተቀባይነት የለዉም። የሕዝቡን ሃሳቡን በነፃ የመግለፅና የመሰብሰብ ነፃነትን ጨምሮ ዓለም ዓቀፍ መብቶችን ማክበር የሊቢያ መንግስት ኃላፊነት ነዉ።»

የኢራን ፕሬዝደንት ሙሃመድ አህመዲነጃድ በሊቢያ ተቃዋሚዎች መገደላቸዉን በመቃወም የአገሪቱ መሪዎች የህዝቡን ፍላጎት እንዲያከብሩ ጠይቀዋል። አህመዲነጃድ በመካከለኛዉ ምስራቅ የተፋፋመዉ ህዝባዊ አመጽ ወደአዉሮፓና ወደሰሜን አሜሪካም ሊዛመት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የጋዳፊ ልጅ ሚስትና ሌሎች የገዢዉ ወገን ቤተሰቦችን የጫነ ጀት ቤይሩት አዉሮፕላን ማረፊያ ማረፍ መከልከሉን የሊባኖስ ድምፅ ራዲዮ መዘገቡን የጀርመን የዜና ወኪል ዘግቧል። የዜና ምንጮቹን የጠቀሰዉ ዘገባ እንዳመለከተዉም የአዉሮፕላን ማረፊያዉ ባለስልጣናት ከሊቢያ የተነሳዉ የግል ጀት ያሳፈራቸዉን የአስር መንገደኞች ማንነት ለመግለፅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ማረፍ ከልክለዉታል። አሜካንን ጨምሮም የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸዉን ከሊቢያ እያወጡ ነዉ። ቱርክ ወደአምስት ሺ ገደማ ዜጎቿን ማዉጣቷን ስትገልፅ አንድ ዜጋዋ መሞቱን አመልክታለች።

Unruhen in Libyen

የጋዳፊ ደጋፊዎች

ሮማንያም እንዲሁ ዜጎቿን የምታወጣበትን አዉሮፕላን መላኳን ገልጻለች። ቻይና ከ33ሺ በላይ ዜጎቿን ማጓጓዣ ለመላክ የሊቢያን ፈቃድ እየጠበቅ መሆኗን አመልክታለች። የጀርመን ጦርኃይል 3,000 ከባድ ተሽከርካሪዎችን በእቃ መጫኛ መርከቦች ወደቱርክ ማጓጓዙን አመልክቷል። ጣሊያን በበኩሏ ከሊቢያ የስደተኞች ጎርፍ ሊከተል እንደሚችል ስጋቷን አሰምታለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሠ

DW.COM