«ሊሸጡን ነው» አፍሪቃውያን ስደተኞች ከእስራኤል | አፍሪቃ | DW | 19.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

«ሊሸጡን ነው» አፍሪቃውያን ስደተኞች ከእስራኤል

እስራኤል በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞችን በግዳጅ ከሀገር ለማስወጣት መወሰኗን ተከትሎ ስደተኞቹ እስራኤል «ልትሸጠን ነው» ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠዋል። ስደተኞቹ እና የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ክኔሴት በሚባለው የእስራኤል ምክር ቤት ፊት ለፊትም ተቃውሞዋቸውን ገልጠዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21

እስራኤል በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ልታስወጣ ነው

እስራኤል ውስጥ 27,000 ኤርትራውያን እና 7,700 ሱዳናውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይጠቀሳል። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል በጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009 ዓም የጥገኝነት ፈቃድ የተሰጠው ለ11ዱ ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስደተኞቹ በመላ ከሀገር ሊባረሩ እንደሆነ መገለጡ ከፍተኛ ተቃውሞ እና  ብርቱ ቁጣን ቀስቅሷል፤ ጥልቅ ስጋትም አሳድሯል። የቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪው ኤርትራዊው ስደተኛ ፍትዊ ዮሴፍ እስራኤል ውስጥ ላለፉት ሰባት ዓመታት ኖሯል። አሁን በእስራኤል መንግሥት ከሀገር የመባረር ስጋት አጥልቶበታል። «ሙሉ ለሙሉ ነው የሚያሰጋን። ከዚህ ወጥተህም የምትሄድበት የለም። አነሱም ደግሞ እየሸጡን እንጂ ወደተሻለ ሀገር  እያሸጋገሩንም አይደለም። እዛም ያለው ድምፅ የምንሰማው  እንደሚሸጡ ነው። ገንዘብ ይከፍሏቸዋል እነሱን ከዛ ወደማንፈልገው ሀገር ነው የሚልኩን ያሉት።»

የእስራኤል መንግሥት ስደተኞቹ በፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ አለያም ወደ ሌላ «ሦስተኛ ሀገር» ከሄዱ $3,500 ዶላር እንደሚከፍል እና የአውሮፕላን ቲኬት በነጻ እንደሚሰጣቸው አስታውቋል። አብዛኞቹ ስደተኞች ግን ከሀገራቸው ለስደት የዳረጋቸው ጦርነት እና ክትትል እንደሆነ ይናገራሉ።  ፍትዊን ጨምሮ ብዙዎቹ ስደተኞቹን ለመቀበል ከእስራኤል ጋር መስማማታቸው ወደተነገረላቸው «ሦስተኛ ሀገራት» ማለትም ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ ከመሄድ እዛው እስራኤል እስር ቤት መቆየቱን ይመርጣሉ። እስራኤል ስደተኞቹን በጥቂት ሣምንታት ውስጥ ከሀገር ለማስወጣት ዝታለች።

 

የእስራኤል ዛቻ እንደ ሌሎቹ አፍሪቃውያን ስደተኞች ፍትዊንም ግራ አጋብቷል፦ «እንግዲህ ወዴት እሄዳለሁ? ወይ ይሸጡናል፤ በኃይል ገፍተው ወደዛ ይወረውሩናል  ወይ ደግሞ እስር ቤት ውስጥ ያስገቡናል ማለት ነው። ይኼን ብለን መወሰን አንችልም።»

ስደተኞች እና የመብት ተሟጋቾች ከትናንት በስትያ እየሩሳሌም ከተማ በሚገኘው የእስራኤል ምክር ቤት ወይንም ክኔሴት ፊት ለፊት ተሰልፈው ነበር። ስደተኞቹ ከወገባቸው በላይ እርቃን ኾነው፤ እጅ እና እግራቸው በሰንሰለት ታስሮ ከፊት ለፊታቸው መሬት ላይ «የሚሸጡበት ዋጋ» መጠን እንደሆነ በተምሳሌት የገለጡበት የገንዘብ መጠን በወረቀት ይታያል። የዚህ ተቃውሞ አስተባባሪ አይሁድ ላልሆኑ አፍሪቃውያን ስደተኞች መብት ተሟጋቿ እስራኤላዊት ሲጋል ኩክ አቪቪ ናቸው። ከእስራኤል ወደ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ የተላኩ ሰዎች ገንዘብ እና ንብረታቸው ተቀምቶ ለዳግም ስደት እንደሚዳረጉ ገልጠዋል። 

«እነዚህ ሰዎች በእውነቱ ለእነዚህ የአፍሪቃ ሃገራት የተሸጡ ናቸው» ይላሉ የመብት ተሟጋቿ። «ነገሩ ውሃ ቅዳ መልስ አይነት ነው። የአፍሪቃ ሃገራቱ ስደተኞቹን እንደገና ወደ ስደት እንዲገቡ ይገፏቸዋል። ሰዎች እንደ ሸቀጥም በለው ምን ግን እየተጠቀሙባቸው ነው» ሲሉም አክለዋል።

ስደተኞቹን የጫነው አውሮፕላን የሩዋንዳ ኤርፖርት ምድርን እንደነካ እዛ ሰነድ ይዘው የሚጠብቁ ሰዎች ስደተኞቹ ወደ ፍተሻ ጣቢያው ሳይደርሱ እንደሚወስዷቸው እስራኤላዊቷ የመብት ተሟጋች ይፋ አድርገረዋል። 

«ስደተኞቹ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ይነጠቃሉ። ኪጋሊ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የግል ቪላ ውስጥ ተወስደው ለ24 ሰአታት በልዩ ጥበቃ ውስጥ ይቆያሉ። ከዚያም ያለአንዳች ሰነድ ሩዋንዳን ለቀው እንዲወጡ ይገደዳሉ። እስራኤል ሀገሯ ውስጥ ደህንነታቸው ያልተጠበቀውን ስደተኞች ለእንደዚህ ያለ ሁኔታ እንዲጋለጡ አድርጋለች።»

የመብት ተሟጋቿ ሲጋል አቪቪ ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ በአካል በመገኘት ከእስራኤል የተላኩ 25 ስደተኞችን አመጣጥ እና የገጠማቸውን መከራ ከራሳቸው ከስደተኞቹ አንደበት መስማታቸውን ጠቅሰዋል። ከአፍሪቃ ጉዟቸው መልስም ከእስራኤል የተባረሩ በርካታ ስደተኞች በሊቢያ እና በባሕር አደገኛ ጉዞ አድርገው አውሮጳ መግባታቸውን ለመብት ተሟጋቿ ነግረዋል።  

እስራኤል ስደተኞችን በግዳጅ ከሀገር ማባረር ከጀመረችው ሰንበትበት ማለቱን  የገለጡት ሲጋል ኩክ አቪቪ ለስደተኞች አዘኔታ ያላቸው የእስራኤል ምክር ቤት አባላት የስደተኞቹን መከራ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ ሄደው እንዲመለከቱ ተማጽነዋል። ጆሮ ዳባ ልበስ መባላቸው ግን አሳዝኗቸዋል። እስራኤል ስደተኞች ያለጥበቃ እንዲንገላቱ ማድረጓን ማቆም እንዳለባትም ጥሪ አስተላልፈዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽንን (UNHCR)  ጨምሮ በርካታ የመብት ተሟጋቾች እስራኤል ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞችን ከሰሃራ በታች ወደሚገኙ ሃገራት ለመላክ የወሰነችበትን ፖሊሲ እንድታጥፍ ተማጽነዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic