ለፍርድ የሚቀርቡት ቴይለር | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.04.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ለፍርድ የሚቀርቡት ቴይለር

በጦር ወንጀለኝነት ተከሰዉ ለመሰወር ያደጉት ሙከራ ከሽፎ የቀድሞዉ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ቻርልስ ቴይለር በቁጥጥር ስር ከዋሉ ቀናት ተቆጥረዋል።

ቴይለር ልዩ ፍርድ ቤቱ ሲቀርቡ

ቴይለር ልዩ ፍርድ ቤቱ ሲቀርቡ

የፍርድ ሂደታቸዉ ከአገራቸዉና ከሴራሊዮን ዉጪ ሳይካሄድ እንደማይቀር ነዉ የተገመተዉ። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች በመብቶች ጥሰት የተከሰሱት ቴይለር ጉዳይ በፍትሃዊ መንገድ እንዲታይ እየጠየቁ ነዉ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ የህዝቡን አመኔታ እንዲያገኝ እዚያዉ ነዉ መዳኘት ያለባቸዉ ይላሉ።
የዜና አዉታሮች የቀድሞዉ የምዕራብ አፍሪካ የጦር አበጋዝ ያሏቸዉ ቻርለስ ቴይለር ሰብዓዊ መብታቸዉ ተከብሮ ነዉ በተከሰሱባቸዉ ጉዳዮች የፍርድ ሂደታቸዉ የሚከናወነዉ።
ትናንት ሁለት እህቶቻቸዉ ፍሪታዉን ከተማ ድረስ ሊያዩዋቸዉ እንዲሄዱ ሲፈቀድ ሌሎች ዘመዶች ነን የሚሉ ደግሞ ዝምንድናቸዉ እስኪጣራ ሞንሮቪያ ለመቆየት ተገደዋል።
አንደኛዋ እህታቸዉ ቴልማ ቴይለር ሳዬ ከጋና በስልክ ለተደረገላቸዉ ቃለ መጠይቅ ቴይለር ደህና መሆናቸዉ ቢገልፁም ከእህታቸዉ ሌላ ባላቸዉና የአክስት ልጆች ዝምድናቸዉ በላይቤሪያ መንግስት ይጣራ በመባሉ ተቆጥተዋል።
አያይዘዉም እህትየዉ ይህ አግባብ አይደለም፤ የሞኖሮቪያ መንግስት የቴይለርን ቤተሰቦች አያዉቅም ይልቁንም እኛን ለማስጨነቅ ጨዋታ ቢጤ መጀመሩ ነዉ ይላሉ።
ቴይለርንም ሴራሊዮን ዉስጥ ለሰባት ቀናት በቆዩበት በተባበሩት መንግስታት ልዩ ፍርድ ቤት ማቆያ ስፍራ ከሁለት ሰዓት በላይ ለማነጋገር እድል አግኝተዋል።
በሌላ በኩል ቴይለር ሴራሊዮን ዉስጥ ፈፅመዉታል የተባለዉን ጨምሮ ለተከሰሱባቸዉ 11 ነጥቦች ከደሙ ንፁህ ነኝ በማለት ነዉ ቃላቸዉን የሰጡት።
ቤተዘመዶቻቸዉ እንደሚሉት ቴይለር ዩናይትድ ስቴትስ፤ ላይቤሪያና ጋና ባሏቸዉ የህግ አማካሪዎቻቸዉ አማካኝነት መከላከያቸዉን ለማቅረብ ጉድ ጉድ እያሉ ነዉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በበኩሉ የቀድሞዉ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት የፍርድ ሂደት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ዓለም ዓቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ አሳስቧል።
በፍትሃዊ መንገድ ጉዳያቸዉ ታይቶም ወንጀለኝነታቸዉ በፍርድ ቤቱ ሳይረጋገጥ ጥፋተኛ ተደርገዉ መወሰድ እንደሌለባቸዉና በእስር ቤትም በተቻለ መጠን በአግባቡ እንዲያዙ ጠይቋል።
የቴይለር ጉዳይ አሁን በርካታ ደጋፊዎች እንዳሏቸዉ በሚነገርበና የደህንነት ስጋት ባለበት በምዕራብ አፍሪካ ከሚካሄድ ይልቅ በኔዘርላንድ ሄግ ቢሆን ይበጃል ባይ ነዉ ፍርድ ቤቱ።
ኔዘርላንድ ጉዳዩን ለማስተናገድ ዝግጁነቷን ብታሳዉቅም ቴይለር በእስርም ሆነ በጥገኝነት የት እንደሚወሰዱ ዉሳኔ ተሰጥቶ ባስቸኳይ ከተወለዱበት ቀዬ እንዲለቁ ትፈልጋለች።
ለዚህም የፀጥታዉ ምክር ቤት የፍርዱ ሂደት የት መሆን እንደሚኖርበት በቅርቡ ዉሳኔ ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ታዛቢዎች ግን ከዉጪ በሚቋቋሙ ፍርድ ቤትና ዳኞች የሚሰጠዉ የፍትህ ጉዳይ በደል በተፈፀመበት በላይቤሪያ አለመሆኑ የኋላ ኋላ ከዚህ በፊት የደረሰን ስህተት መድገም እንዳይሆን ይላሉ።
ፍሪታዉን ዉስጥ ለረጅም ወራት የቆዩት ጀርመናዊዉ የዓለም ዓቀፍ ህግ ምሁር ያን ቬትሰል እንዲህ ይላሉ «በጀርመን ሀገር ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ የኑረንበርጉን ችሎት በሚመለከት የቀረበዉን ዓቢይ ሂስ በሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ ጉዳይ የተያዘዉን ምርመራ ጭምር የምናዉቀዉ ነዉ። ፍርድ ቤቱ በዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ተፅዕኖ የተመሰረተ ባዕድ ብይን ሰጪ አካል ነዉ። መንግስት ትልቅ ድርሻ ኖሮት ሕዝቡም በቂ ምልክት ማግኘት ነበረበት። ህዝቡ ይህ የኛ ፍርድ ቤት እንጂ ከዉጪ የተቋቋመ ባዕድ ችሎት ነዉ እንዲል ማድረግ ባልተገባ ነበር።»
የአባት ዕዳ ለልጅ እንዲሉ የቴይለር ጦስ ለልጃቸዉ ተርፎ የ29 ዓመቱ ቻርለስ ማርቱር ኢማኑዌል የሀሰት ፓስፓርት በመያዝ ሚያሚ አዉሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ስር ዉሏል።
ቦስተን የተወለደዉና የአሜሪካ ዜግነት ያለዉ ትንሹ ቴይለር እንደየስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣናት አገላለፅ ከሆነ ፓስፓርቱን ለመቀበል ቅፅ ሲሞላ የአባቱን ማንነት ዋሽቷል።
ኢማኑኤል በአባቱ የስልጣን ዘመን የላይቤሪያ ፀረ ሽብር አገልግሎት ኃላፊ ሆኖ ሰርቷል። የተባበሩት መንግስታት የመንቀሳቀስ እግድ ከጣለባቸዉ ላይቤሪያዉያን መካከልም አንዱ ነዉ።
በአፍሪካ ከዚህ በፊት በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፤ በሙስናና በማን አለብኝነት የተፈረጁ መሪዎች መካከል እነ ቦካሳ፤ ሞቡቱ ሴሴኮ፣ እንዲሁም ኢዲ አሚንን መጥቀስ ይቻላል።
እንዳለመታደል ሆኖ አፍሪካ ከሰብዓዊ መብቶች ረጋጮችና በሙስና ተዘፍቀዉ ዜጎቻቸዉን ከሚያጎሳቁሉ መሪዎች አለመላቀቋ እንዳለ ሆኖ የቴይለር ለፍርድ መቅረብ በሌሎች አገራት ተጠግተዉ ለሚገኙት ቀደምት ተጠያቂ መሪዎችም የሚያስተላልፈዉ መልዕክት ያለ ይመስላል።