ለጋሱ እቅድ ከምን ደረሰ? | ኤኮኖሚ | DW | 14.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ለጋሱ እቅድ ከምን ደረሰ?

የኢትዮጵያ መንግሥት የእንቁላል፤ የዶሮ እና የስጋን ምርት እና ፍጆታን ሊያሳድግ እቅድ ከነደፈ ሁለት አመታት ተቆጠሩ። ለአምስት አመታት በ760 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረው እቅድ በተጨባጭ የለወጠው ነገር ስለመኖሩ ግን የሚታወቅ ነገር የለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14

የኢትዮጵያ የቤት እንስሳት ልማት ፍኖተ-ካርታ

አንድ እንቁላል ከ2.80 እስከ 3 ብር በሚሸጥባት ሞጣ ከተማ እና አካባቢዋ ዶሮ እርባታ ትኩረት የሚሰጠው የሥራ ዘርፍ አይደለም። የሞጣ አካባቢ የአየር ንብረት ለዶሮ እና ከብት እርባታ ምቹ ቢሆንም የማኅበረሰቡ ዋነኛ የኑሮ መሠረት ግን የእርሻ ሥራ ነው። ሞጣ የሚኖሩት አቶ እንደሻው ምስጋናው እንደሚሉት የከተማዋ ነዋሪ የሚፈልገውን ወተት በገበያ እንደልብ አያገኝም። 

ከአዲስ አበባ በ371 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው ዕድሜ ጠገቧ ሞጣ ከተማ የሚስተዋልባት የእንስሳት ተዋፅዖ እጥረት የብቻዋ አይደለም። የአገሪቱ አመታዊ የወተት እና እንቁላል ምርት እና ፍጆታ ከሌሎች አገሮች አኳያ እጅጉን አናሳ ነው። የኢትዮጵያ የቤት እንስሳት ልማት ፍኖተ-ካርታ እንደሚጠቁመው በዓመት ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ወተት በሚመረትባት አገር አማካኝ ግለሰባዊ ፍጆታ 0.03 ሊትር አካባቢ ብቻ ነው። አራት ቢሊዮን ገደማ እንቁላል በዓመት ሲመረት የኢትዮጵያውያኑ አማካኝ አመታዊ ፍጆታ ደግሞ 43.3 መሆኑን ይኸው ሰነድ ያትታል። 

መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ የመሰለፍ እቅድ የሰነቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ታዲያ አገሪቱ ያላትን የቤት እንስሳት ሃብት ለማልማት የአምስት አመታት እቅዱን ይፋ አድርጓል። 760 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለው ውጥን ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ሁለት አመታት ያስቆጠረ ሲሆን ከ11 ሚሊዮን አርብቶ አደሮች የ2.3 ሚሊዮኑን ሕይወት ይቀይራል ተብሎለታል። የኢትዮጵያ እንስሳት እና ዓሣ ሐብት ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሐም ተስፋዬ እንደሚሉት የእንስሳት ዝርያ እና ጤና አጠባበቅን ማሻሻል እንዲሁም የመኖ አቅርቦት ችግርን መፍታት ትኩረት እንደተደረገባቸው ይናገራሉ። 

ዓለም አቀፍ የእንስሳት ጥናት ተቋም እና ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በጥምረት የተዘጋጀው አገራዊ እቅድ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. የእንቁላል ምርትን የዛሬ አምስት ዓመት ከነበረው በ828 በመቶ ለማሳደግ ውጥን ይዟል። ወተት 93 በመቶ፤ የዶሮ ሥጋ 147% እንዲሁም የቀይ ሥጋ ምርት 52% በመቶ እንዲያድጉ ተወጥኗል። ዓለም አቀፍ የእንስሳት ጥናት ተቋም በአማካሪነት የሚያገለግሉት ባሪ ሻፒሮ እቅዱ ለጋስ መሆኑን አይሸሽጉም። አማካሪው በፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ላይ በፃፉት ሐተታ በጥንቃቄ ከተጠና ሊተገበር በሚችል እቅድ ከተሰራ ስኬታማ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ባለሙያው ኢትዮጵያ የተዳቀሉ ዝርያዎች እንደሚያስፈልጓት፤ የተሻለ መኖ ማቅረብ እና የእንስሳት ጤና አገልግሎት አጠባበቋም ሊሻሻል እንደሚገባም አክለዋል። አቶ አብርሐም ተስፋዬ ለወተት ሥጋ እና እንቁላል ምርት አመቺ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተዋል ሲሉ ይናገራሉ።እቅዱ ታዲያ በሁለት አመታት ውስጥ ምን አሳካ? አቶ አብርሐም መንግሥታቸው አቅዶ ያሳካውን በቁጥር ሊናገሩ ባይችሉም ለውጥ ግን አለ ባይናቸው። 

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic