ለድሆች ያልበጀ የእርሻ ፖሊሲ | ኤኮኖሚ | DW | 23.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ለድሆች ያልበጀ የእርሻ ፖሊሲ

በዓለም ላይ በዛሬው ጊዜ በረሃብ የሚሰቃየው ሕዝብ አንድ ሚሊያርድ ገደማ ይጠጋል። በዚህ ሁኔታ የድህነት ኑሮ የሚገፋው አብዛኛው ደግሞ በአነስተኛ ደረጃ የሚገኝ ገበሬ ነው።

በዓለም ላይ በዛሬው ጊዜ በረሃብ የሚሰቃየው ሕዝብ አንድ ሚሊያርድ ገደማ ይጠጋል። በዚህ ሁኔታ የድህነት ኑሮ የሚገፋው አብዛኛው ደግሞ በአነስተኛ ደረጃ የሚገኝ ገበሬ ነው። ለዚህም ምክንያቱ የእርሻ ልማት በታዳጊና በበለጸጉ ሃገራት በጥቅሉ ችላ መባሉ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። አነስተኛ ገበሬዎች መሬትና ማልሚያ ውሃም ሆነ የአማካሪዎች ዕርዳታ፣ ወይም ዘርና ብድር የማግኘት የረባ ድጋፍ የላቸውም። ይህን የሚሉት የኦክስፋም ግብረ-ሰናይ ድርጅት የምግብና የንግድ ጥያቄዎች ዓለምአቀፍ ባለሙያ የሆኑት ማሪታ ቪገርታለ ናቸው።

በዓለም ገበያ ላይ የሚከሰት የዋጋ ውጣ-ውረድ እንዲሁም ድርቅና የአካባቢ አየር ለውጥን ተከትሎ የጠነከረው ጎርፍም ተጨማሪዎቹ ችግሮች ናቸው። ቪገርታለ እንደሚሉት ገንዘብ ለጋሾችና ታላላቅ ድርጅቶች ለትናንሽ ገበሬዎች ሣይሆን ለመዋዕለ-ነዋይና ለታላላቅ የካፒታል ባለቤቶች አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ነው አጥብቀው የሚጥሩት። እንግዲህ የእርሻው ኢንዱስትሪ ትናንሽ ገበሬዎችን መሬት አልባ እያደረገ ሲሆን በዓለም ላይ የተንሰራፋውን ረሃብ ለማስወገድ የሚያስችል አልሆነም።

ጉዳዩ በዚህ በጀርመን ሲካሄድ በሰነበተው «አረንጓዴ ሣምንት» በመባል በሚታወቀው በዓለም ላይ ታላቁ የበርሊን የእርሻ ልማትና ምግብ ትርዒት አኳያ ዓቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር። በመድረኩ ከ 80 መንግሥታት የሚበልጡ ተጠሪዎችና ባለሙያዎች ተሰብስበው ሲነጋገሩ የጀርመኗ የእርሻ ሚኒስትር ኢልዘ አይግነር በመንግሥታዊና በግል መዋዕለ ነዋይ አቅራቢዎች መካከል የሚደረግ የጠበቀ የጋራ ጥረት ለተሳካ የእርሻ ልማት ትብብር ቁልፍ እንደሚሆን ነው ያስገነዘቡት።

ይህ የጀርመን የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት መጀመሪያ የትናንሽ ገበሬዎችን የእርሻ ልማት ለማራመድ አስፍኖት ከነበረው መርህ ጋር የሚጣጣም ነው። ፖሊሲው ትናንሽ ገበሬዎች ለገበዮች እንዲበቁ፣ የሙያ ሥልጠናና የፊናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የገጠር አካባቢ ልማትን በማጠናከሩ ላይ ያልማል። በሌላ በኩል ዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት መንግሥታት የሚከተሉት መንገድ የተሳሳተ ነው የሚል ነው።

የድርጅቱ ባልደረባ ማሪታ ቪገርታለ እንደሚያስረዱት ምናልባት ከዘመናዊው ሰንሰለት በመተሳሰር ለምሳሌ በኮንትራት ከታላላቅ ኩባንያዎች ለመተባበር የሚበቁ ጥቂት አነስተኛ ገበሬዎች ሊገኙ ይችላሉ። ሆኖም የኦክስፋሟ ባለሙያ ትናንሾቹ ገበሬዎች የተደራጁ ባለመሆናቸው ስጋታቸው ከፍተኛ ነው። ሃሣቡ እንዲሳካ ወይም ፍሬ እንዲሰጥ ከተፈለገ መንግሥታት ትናንሽ ገበሬዎች ወደ ገበዮች እንዲዘልቁ፣ እንዲሁም ብድርና ዘር እንዲያገኙ ማድረጋቸው ቅድመ-ግዴታ ነው የሚሆነው።

ይሁንና መንግሥታዊው የልማት ዕርዳታ ይበልጥ የታላላቁን የእርሻና የምግብ ኢንዱስትሪ ሚና በማጠናከሩ ላይ አተኩሮ ይገኛል። ዛሬ ከቡድን-8 የምግብ ዋስትና ሕብረት ዓባላት ወይም ከጀርመን የታዳጊና ራማድ ያሉ ሃገራት የእርሽ ልማትና የምግብ ምርት ማራመጃ አካል ዓባላት መካከል ግዙፉን የንጥረ-ነገር ኩባንያዎች ባየርንና BASF-ን፣ ወይም ሞንሣንቶን፤ ኔስትለንና ሢንጌንታን የመሳሰሉት ይገኙበታል። የጥረቱ ዓላማ የዕርሻ ልማትን ማራመድና በዚሁም ለምግብ ዋስትና አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።

ይሁን እንጂ አዘውትሮ የሚታየው በልማቱ ረገድ ተጻራሪው ሁኔታ ሲከሰት ነው፤ FIAN በሚል አሕጽሮት የሚጠራው የጀርመን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ ጌርትሩድ ፋልክ የሚናገሩት። ኩባንያዎች በእርሻ ልማት ላይ መዋዕለ-ነዋይ የሚያደርጉት ሕጋዊ ዋስትና ሲኖራቸው ብቻ ነው መባሉን ተገቢው መንገድ አድርገው አይመለከቱም። ይሄው በታዳጊ ሃገራት ያለውን ባሕላዊ ስርዓት ወደ ጊዜው ሕጋዊ ስርዓት የሚለውጥ ነው። እናም ወደ መሬት መሸጥ ይወስዳል። በዚህ ደግሞ በተለይ ድሃውና ረሃብተኛው የመግዛት አቅሙ አይኖረውም። እናም ተጎጂ ነው የሚሆነው።

ፋልክ እንደሚናገሩት በዚህ ሁኔታ በተለይ ተጎጂ ሆነው የሚገኙት ለነገሩ በእርሻው መስክ እጅግ ታላቅ ሚና ያላቸው ሴቶች ናቸው። በባሕላዊው ስርዓት ውስጥ ሴቶች የመሬት መብት የላቸውም። መሬት በይዞታቸው ስለማይገኝ ደግሞ ብድር መውሰድ አይችሉም። መረጃዎችን ለተመለከተ አፍሪቃ ውስጥ ብቻ ከ 90 በመቶ የሚበልጠው መሠረታዊ ምግብና 30 በመቶው ለገበያ የሚቀርብ ፍራፍሬ የሚመረተው በሴቶች ነው። በብዙ ታዳጊ ሃገራት በአነስተኛ ገበሬ ደረጃ በሚካሄደው የእርሽ ልማት ዘርፍ ከ 70 እስከ 80 በመቶው የሥራ ሃይልም የሴቶች ሆኖ ይገኛል።

የሆነው ሆኖ በዓለም ላይ ለተንሰራፋው ረሃብ ተገቢ ምላሹ በእርሻ ኢንዱስትሪዎች መዋዕለ-ነዋይ ምርት እንዲጨምር ማድረጉ አይደለም። በጌርትሩድ ፋልክ አባባል በዓለም ዙሪያ ዘጠኝ ሚሊያርድ ሕዝብን ለመቀለብ የሚያበቃ ምግብ ይመረታል። ችግሩ ያለው ይበልጡንም በክፍፍሉና በውስጣዊ ገበዮች አግባብ ማግኘቱ ላይ ነው።

ኡጋንዳን እንደ ምሳሌ ብንወስድ አገሪቱ ለም ስትሆን በመሠረቱ ለጎረቤት ሃገራት ጭምር በተረፈች ነበር። ግን ገበሬዎቿ መንገድንና ማመላለሻን የመሳሰሉ መዋቅራዊ ይዞታዎች ይጎሏቸዋል። እናም ለገበያ ለማቅረብ ባለመቻል፤ አቀዝቅዞ ለማስቀመጥ ኤሌክትሪክ ባለመኖሩም በዚያ በየቀኑ ብዙ ወተት ነው ፈሶ የሚቀረው። እነዚህ ናቸው ብዙዎችን ለረሃብ የሚዳርጉት።

ሌላው የእርሻ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ዓላማ ያስከተለው ችግር Landgrabbing ማለት የመሬት ቅርምት በመባል የሚታወቀው ነው። ታላላቅ በተለይም የውጭ ባለሃብቶች በመንግሥት ድጋፍ የአገሬውን መሬት ይነጥቃሉ። እርግጥ በዚሁ በእርሻ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አዳዲስ የሥራ ቦታዎች ሊፈጠሩ መቻላቸውን ፋልክም ይናገራሉ። እንደርሳቸው አባባል ይህ ደግሞ ብዙዎቹን አዳጊ ሃገራት የሚያስፈልጋቸውም ነው። ግን አብዛኛውን ጊዜ የላባቸው ዋጋ በራሳቸው ቢያመርቱ ያገኙት ከነበረው ገቢ በጣሙን ያነሰ ሆኖ ይገኛል።

በዓለም ዙሪያ ዛሬ ሁለት ሚሊያርድ ሕዝብን ለመቀለብ የሚያስችሉ 500 ሚሊዮን የአነስተኛ ገበሬ ማምረቻ ይዞታዎች መኖራቸው ይገመታል። አነስተኛ ገበሬዎችን በኤኮኖሚና በማሕበራዊ ረገድ ማገዙ ጠቃሚ መሆኑን ብራዚል «ዜሮ-ረሃብ» በሚል ዕቅዷ አሳይታለች። ለምሳሌ ለትምሕርት ቤቶች ቀለብ የሚያስፈልገው የምግብ ምርት የሚገዛው ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ ገበሬዎች ነው። ይሄ ደግሞ የትምሕርት ቤት ሕጻናትንም አነስተኛውን ገበሬም ይጠቅማል።

ግን ይህም ሆኖ ቪገርታለ እንደሚሉት ብራዚል ውስጥ በ 2009 እና በተከታዩ ዓመት መንግሥት ለእርሻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያፈሰሰው ገንዘብ ለትናንሽ ገበሬዎች ካወጣው ስድሥት ዕጅ ይበልጥ ነበር። ይህ ደግሞ ምን እንዳስከተለ መገመት አያዳግትም። ውጤቱ እንደተለመደው ትናንሽ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ መሬትን ለታላላቅ አምራቾች ማሸጋገር፤ እንዲያም ሲል የተክል ዓይነትንና ለም መሬትን ማጣት ነው የሆነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ሸንጎ በወቅቱ በገጠር አካባቢ የሚገኙ ገበሬዎችንና ሌሎች ሠራተኞችን መብት መከበር በተመለከተ አንድ መግለጫ እያረቀቀ ይገኛል። ለዚሁ መነሻ የሆነውም ሸንጎው ባለፈው መስከረም ወር ስብሰባው የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ቢቃወሙትም ያስተላለፈው ውሣኔ ነበር። ውሣኔው የትናንሽ ገበሬዎች መብት እንዲከበር አስፈላጊውን የስነ-ልቦና ለውጥ ቢያስከትል ምንኛ በጠቀመ!

ለጊዜው የሚቀረው በተሥፋ መጠበቅ ብቻ ነው። የእርሻ ልማትን ፍቱን ማድረግ ካልተቻለ በዓለም ላይ ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ የሚሄድውን ሕዝብ መቀለቡ ወደፊት የሚቻል አይሆንም። ችግሩን መቋቋም እንዲቻል በተለይ በታዳጊው ዓለም የእርሻ ዘርፍ ብዙ ገንዘብ መፍሰስ ይኖርበታል። እርግጥ ለመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ትልቁ ነገር ትርፍ ማግኘት ነው። በዓለምአቀፉ የምግብ ምርቶች ንግድ ዛሬ ከእርሻ ኢንዱስትሪዎች ባሻገር ባንኮች ሳይቀር ገበያውን ለመጠቀም የተሰማሩ ሲሆን ምግብ እንደማንኛውም ዕቃ የሚታይበት ዝንባሌም እየተጠናከረ ነው የመጣው።

ንግድ ላይ የሞራል ጥያቄ የለም የሚሉት የፊናንሱና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠሪዎች ጥቂቶች አይደሉም። በበርሊኑ «አረንጓዴ ሣምንት» አኳያ በተካሄደው ዓለምአቀፍ የእርሻና የምግብ መድረክ ጉባዔ ላይ የዶቼ ባንክ አመራር አካል ሊቀ-መንበር ዩርገን ፊትሽን ለካፒታል በር ሳይከፈት የእርሻ ልማት ሊስፋፋም ሆነ ሊሻሻል እንደማይችል ነው ያስገነዘቡት።

«አንድ በእርሻ ልማት ረገድም መታለፍ የማይችል ለእያንዳንዱ የመዋይለ-ነዋይ ውሣኔ የሚሰራ ሃቅ አለ። ማለት እያንዳንዱ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤት ገንዘቡን ስራ ላይ በማዋሉ ለዚሁ በቀላሉ ተገቢውን ትርፍ ማግኘት ይፈልጋል። ይህ እንግዲህ ሁሉም ወገን ሊቀበለው የሚገባ ነው። በእርሻ ልማት ዘርፍም ንግድ እንደሌላው ሁሉ ንግድ መሆኑን ከሞራላዊ ስሜት የተነሣ ሊቀበል የማይፈልግ ካለ እዚህ ላይ ችግር አለን»

ፊትሽን ስሜታዊነት ሚና ሊኖረው አይገባም ሲሉ ሌላዋ የበርሊኑ የእርሻና የምግብ ጉባዔ ተሳታፊ የጀርመኑ የዓለም የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት ፕሬዚደንት ቤርብል ዲክማን በአንጻሩ በእርሻው ዘርፍ የሚታየው ትርፍ የማጋበስ ዘይቤ የዋጋ መናርን በማስከተል በተለይም ከባድ ረሃብ በሚፈጠርባቸው ሁኔታዎች ችግሩን ያባብሰዋል ባይ ናቸው።

«በዓለም ዙሪያ 850 ሚሊዮን ሕዝብ ተርቦ በሚገኝበት፣ በዓለም ላይ በቂ ምግብ ተመርቶም ሕጻናት በምግብ እጥረት በሚሰቃዩበት ሁኔታ፣ ምግብ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል አለመቻሉንና ረሃብ ጠንካራ በሆነባቸው ሃገራት የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ለትናንሽ ገበሬዎች በማይበጅ መንገድ ገንዘብ በስራ ሲያውሉ ሳይ አዎን ስሜታዊ ነኝ»

ከትናንሽ ገበሬዎች ተገዝቶ ወይም ተነጥቆ በሚወሰድ መሬት ተመርቶ ውጤቱ ወደ ውጭ የሚሸጥበት የፊናንስ ንግድ የለየለት የገንዘብ ሽግሽግ ተግባር እንጂ በእርሻ ልማት ላይ የዋለ ሊባል አይችልም።

ለነገሩ ባለፉት አሠርተ-ዓመታት በእርሻ ልማት ዘርፍ የተደረገው መዋዕለ-ነዋይ አቆልቋይነት የታየበት ነው። በወቅቱ በታዳጊ ሃገራት ትናንሽ ገበሬዎች በአማካይ ስራ ላይ የሚያውሉት ካፒታል በዓመት 114 ኤውሮ ቢደርስ ነው። ይሁንና በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በፋኦ ግምት በ 2050 ዓ-ም ገደማ የዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብን የምግብ ፍላጎት ለመሸፈን በዘርፉ በያመቱ 83 ሚሊያርድ ዶላር መዋዕለ-ነዋይ መደረግ ይኖርበታል። ጉዞው ከባድ ነው፤ በተለይም የተጣጣመ የፖሊሲ ተሃድሶና ገቢርነት በጣሙን ያስፈልጋል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 23.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Pat
 • ቀን 23.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Pat