“ለውጡ” ተቀልብሷልን? | ኢትዮጵያ | DW | 08.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

“ለውጡ” ተቀልብሷልን?

ትላንት መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ‘9 ሚሊዮን ከሚጠጉ ኢትዮጵያውያን መካከል፥ 3.8 ስምንት ሚሊዮኖቹ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ናቸው’ የሚለውን በመግለጫ እያሳወቀ ባለበት ሰዓት በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሔዱ ነበር። ሰልፎቹ የተረጂዎች ቁጥር እንዴት ይህን ያህል ይሆናል በሚል አልነበረም።

በፍቃዱ ኃይሉ 

ትላንት መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ‘9 ሚሊዮን ከሚጠጉ ኢትዮጵያውያን መካከል፥ 3.8 ስምንት ሚሊዮኖቹ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ናቸው’ የሚለውን በመግለጫ እያሳወቀ ባለበት ሰዓት በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሔዱ ነበር። የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ይህንን ያህል ከፍ ማለት ያልቀሰቀሰውን ተቃውሞ፥ ኦሮሚያ የአስተዳደር ክልል ውስጥ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሰጠታቸው ግን አስነስቶታል። 

የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞችን በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚወሰዱ እርምጃዎች አንድ የሚያደርጋቸውን ያህል ሌላ የሚያሥማማቸው ነገር ያለ አይመስልም። ከአዲሱ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) አመራሮች መምጣት በፊት የነበሩትን ተቃውሞዎች ከጫፍ እስከ ጫፍ በአመፅ ያንቀሳቀሰው “የአዲስ አበባ መስፋፋት” ጉዳይ ነበር፤ አሁንም የትላንት እና ከትላንት ወዲያ ተቃውሞዎች እና ማጉረምረሞችን የወለዳቸው ይኸው የአዲስ አበባ በሌላ መልኩ መሥፋፋት ጉዳይ ነው።

የተቃውሞዎቹን መጋጋል ተከትሎ ኦዴፓ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መግለጫ አውጥቷል። ኦዴፓ በመግለጫው “የኦሮሚያ ወሰንን ተሻግረው የተሠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከክልሉ ዕውቅና ውጪ ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸው ትክክለኛ አለመሆኑን” አስታውቋል። 

መግለጫው ተቃውሞዎቹን ለማስታገስ የወጣ ነው ወይስ እውነትም ኦዴፓ ስለጉዳዩ ምንም ዕውቀት አልነበረውም? እውነት የኦዴፓ አባል የሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የመኖሪያ ቤቶቹን ዕጣ አወጣጥ ፓርቲያቸው ሳያውቅ ነው ያከናወኑት? የዕጣ አወጣጡ መርሐ ግብር ላለፉት ወራቶች ሲራዘም ቆይቶ በዚህ ሳምንት ከትላንት በስቲያ እንደሚወጣ ሲነገር ኦዴፓ የት ነበር? ከሁሉም በላይ ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር ክልል ውስጥ ሲገነቡ የክልሉ መንግሥት እንዴት ዝም አለ? የአዲስ አበባ መስተዳድርስ ከአስተዳደር ወሰኑ ተሻግሮ ግንባታውን ለማካሔድ እንዴት ደፈረ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች በዚህ ጽሑፍ አጥጋቢ መልስ መስጠት አይቻልም። ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹ በራሳቸው አብዛኛውን ድርጊት የቲአትር ገጽታ ያላብሱታል። 

በብሔርተኞች እጅ የወደቀው ለውጥ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምንም በላይ በዕጩነት ለተጠቆሙበት የኖቤል ሽልማት የጓጉ ይመስላሉ። ለዚህም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማምጣት ደፋ ቀና እያሉ የጎረቤት አገራትን መሪዎች በማሥማማት በተጠመዱበት ወቅት ግን አገራቸው በውስጣዊ ቀዝቃዛ ጦርነት እየታመሰች ነው። የጎረቤት አገራት ኩርፊያ ያስጨነቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገር ውስጥ የዘውግ ብሔርተኞችን (ethnonationalists) ፍጥጫ እና ቀዝቃዛ ጦርነት ለማስታገስ ያላቸው ቁርጠኝነት፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቀዛቀዘ ይመስላል። 

በዘውግ ተኮር ግጭቶች ምክንያት ብቻ ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁ ዜጎች ቁጥር 3.1 ሚሊዮን መሆኑን መንግሥት ትላንት አምኗል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በትግራይ እና አማራ ሕዝብ መካከል “ወደ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ፀብ አጫሪነቶቸን” እንደማይቀበል የካቲት 26 ቀን 2011 መግለጫ አውጥቷል። መንግሥታዊ ያልሆኑ በኅቡዕ የተደራጁ አካላት ከመፈርጠማቸው የተነሳ፥ ዜጎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የደኅንነታቸው ጉዳይ ያሳስባቸው ይዟል።

ይህ ሥጋት ገበያውን እያቀዛቀዘው መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ ተፅዕኖው እንዳይበረታ ተፈርቷል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ውጥረት መካከል የፌዴራል መንግሥቱ የትኩረት አቅጣጫ ምን እንደሆነ ግራ እስከሚያጋባ ድረስ ዝምታን መርጧል። ፍጥነቱ አስደናቂ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራርም እጅግ በጣም መንቀራፈፍ አምጥቷል። ሌላው ቀርቶ ቢሳካ የለውጡ ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚቆጠረው የአፋኝ አዋጆች ክለሳ ሒደቱ ከአጀማመሩ አንፃር እጅግ ዘግይቷል።

ይህ በእንዲህ እያለ የዘውግ ብሔርተኞች ግን ሁሉንም ነገር “የኔ ነው”፣ “የኔ ነው” በሚል ሽሚያ የየክልል መንግሥቶቻቸውን እየጠመዘዙ ነው። በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል የሚታየው ውጥረት እንዲሁም አዲስ አበባን በተመለከተ የሚነሳው ውዝግብ የዚሁ አልጠግብ ባይ ብሔርተኞች ጥያቄ የወለደው ነው። የክልል መንግሥታቱም ሕዝባዊ ቅቡልነት ለማግኘት ወይም ያገኙትን ላለማጣት ሲሉ የየብሔርተኞቹን ጥያቄ በማስታመም፣ ውሳኔያቸውን ከብሔርተኞቹ ጋር ለማሥማማት በመሞከር እና ወጥ አቋም ይዞ የለውጡን ፍላጎት በሚመጥን መልኩ በፍጥነት በመገስገስ ፈንታ፣ ወትሮም ፍኖተ ካርታ ያልነበረውን የለውጥ እና የመሻሻል ሒደት በብሔርተኞቹ ጮርቃ ሕልም እንዲመራ ወደማድረጉ አዝምመዋል። በዚህ ከቀጠሉ በኦዴፓ እና አዴፓ መካከል የተመሠረተው እና ለለውጡ አንድ አስተዋፅዖ አበርካች የተባለለት ጥምረትም እንዳይላላ ያሰጋል።

ከአዙሪቱ መውጫ

ከዚህ በፊት፣ በዚሁ አምድ ላይ ባሰፈርኩት አጭር መጣጥፌ፣ ብሔርተኝነት ለውጡን ለማምጣት ዐቢይ መንሥኤ እንደሆነ ሁሉ፣ ለውጡንም ለመቀልበስ እንደሚችል ስጋቴን አስፍሬ ነበር። ይሁንና ለውጡ ሊቀለበስ የሚችልበትን ዕድል አሁን እያየነው እንደመሆኑ እንዳይቀለበስ ምን ይደረግ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ዋነኛው ጥያቄ አሁን ያለው አመራር ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘበትን እና የለውጥ አመራር የሚል ማዕረግ ያስሰጠውን ሥራ ወይም ቃል ኪዳን በማስታወስ፣ ግልጽ ዕቅድ እና የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት እንዲሁም ለዕቅዱ ተፈፃሚነት ሙሉ ትኩረት እና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በማሳየት በተለያዩ የጥቅም ቡድኖች ሳይወዘወዙ ወደ ፊት መገስገስ ነው። ምን፣ መቼ ይደረጋል?

“የለውጥ አመራሩ” ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘው በዋናነት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እና ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል መድረክ ለመፍጠር ነው። ይህንን በተግባር ለማሳየት፣ አገር ለማረጋጋት፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ እና ጅምር ሥራዎችን ለመጨረስ “የለውጡ” መባቻ ላይ የታየው ፍጥነት፣ ትጋት እና ሕዝብን አዳማጭነት አሁንም መመለስ አለበት። 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

ተዛማጅ ዘገባዎች