ለዉጥ የሚሻዉ ጎጂ ልማድ | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ለዉጥ የሚሻዉ ጎጂ ልማድ

የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት ይፋ ባደረገዉ ዘገባ መሠረት በመላዉ ዓለም 200 ሚሊየን ልጃገረዶች እና ሴቶች ላይ ግርዛት ተፈፅሟል። ከእነዚህ መካከል ግማሹ ደግሞ የሚገኙት በሶስት ሃገራት ዉስጥ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:36
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:36 ደቂቃ

የሴት ልጅ ግርዛት

ሴቶች ልጆችን መግረዝም ሆነ ማስገረዝ ይቁም የሚለዉ ምክር በሰፊዉ በተዳረሰበት በዚህ ወቅት በተለይ ግብፅ ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ለማሳሰቢያዉ ቁብ የሰጡት አይመስሉም። ከተጠቀሰዉ ቁጥር ገሚሱ የተመዘገበዉ በእነዚህ ሃገራት ነዉ።

የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF እንደሚለዉ ከሆነ ባለፉት ዓመታት ከነበረዉ አካሄድ ታይቶ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2014 ዓ,ም ከተገመተዉ ይበልጥ ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተስፋፍቶ ታይቷል። ሴት ልጆች ላይ ግርዛት መፈፀሙ የሚያስከትለዉ የጤና እክል፤ እንዲሁም የስነልቦና ጫና በተደጋጋሚ ሲገለፅ፤ አስከፊነቱም በፊልም በተደገፉ መረጃዎች አማካኝነት ለማሳየት ተሞክሯል። እንዲያም ሆኖ ግን የሚፈለገዉን ያህል ለዉጥ ማምጣት አለመቻሉን ነዉ ዘገባዎች አሁንም የሚያሳዩት። በዩኒሴፍ የማኅበረሰብ ንቅናቄ ባለሙያ ወ/ሮ ዘምዘም ሽኩር፤ ችግሩ መኖሩ ባይካድም ከፍተኛ ለዉጦች አሉ ባይናቸዉ።

Genitalverstümmelung Messer

ለግርዛት የሚዉለዉ መቁረጫ

ኢትዮጵያ በብሄራዊ ደረጃ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የሚያስችል ስልት ቀርፃ በሥራ ላይ ያዋለች ሀገር ናት። ወ/ሮ ዘምዘም እንደሚሉትም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን መከላከል እንዲሁም የድርጊቱ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች የጉዳቱ መጠን እንዲቀንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራ ተሠርቷል። በሐገሪቱ ሕግ መሠረት ይህን መፈፀም የሚያስቀጣ በመሆኑ ወደሕግ አካል እንዲመጡ እና የሕግ አካልም ተገቢዉን ምላሽ መስጠት የሚችልባቸዉ መመሪያዎች መኖራቸዉንም ይገልፃሉ። ኢትዮጵያም ይህ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ደጋግማ መፈረሟንም ይዘረዝራሉ።

የሴት ልጅ ግርዛትንም ሆነ አጠቃላይ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ ኅብረተሰብን በማስተማርና በማንቃት ከፍተኛ ተግባር አከናዉነዉ ዉጤት ካስመዘገቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ከንባታ ሜንቲ ጌዝማ ነዉ። የድርጅቱ መሥራች እና መሪ ዶክተር ቦጋለች ገብሬ የሴት ልጅን የመዋለጃ አካል የሚጎዳዉን ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም 23 በመቶ ነዉ የቀረዉ የሚለዉን አይቀበሉትም።

Äthiopien Kampagne gegen weibliche Genitalverstümmelung

ኢትዮጵያ ዉስጥ ጎጂዉን ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም የሚካሄደዉ ዘመቻ

ዩኒሴፍ በ90 ሃገራት ቅኝት አካሂዶ ነዉ በተለይ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ዉስጥ የሴት ልጅ ግርዛት ሰለባዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያመለከተዉ። በነገራችን ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሴት ልጅ ግርዛት የተወሰኑ የአፍሪቃ፤ የመካከለኛዉ ምሥራቅ እና የእስያ ሃገራት ማኅበራዊ ችግር ብቻ መሆኑ ቀርቶ፤ አዉሮጳ እና አሜሪካንንም ማሳሰብ መጀመሩ እየተነገረ ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት የቶምሶን ሮይተርስ ተቋም ያወጣዉ ዘገባ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡ ሴቶች እና ልጃገረዶች ለግርዛት ይጋለጣሉ የሚል ስጋት መኖሩን ያመለክታል። እንደዘገባዉ እነዚህ ልጆች አንድም ድርጊቱ በሚፈፀምበት ሀገር የተወለዱ ናቸዉ አንድም ወላጆቻቸዉ ከእንዲህ ያሉ ሃገራት የመጡ ናቸዉ። ይህ ስጋት የአሜሪካን ብቻ አይደለም የአዉሮጳ የተለያዩ ሃገራትም እንደሚጋሩት ነዉ የሚነገረዉ። ሁሉም ግን ቃላቸዉ አንድ ነዉ፤ ችግሩ ባህር ተሻግሮ በማይታወቅበት አካባቢ መታየት የቻለዉ ድርጊቱ ከሚፈፀምባቸዉ ሃገራት የፈለሱ በመበራከታቸዉ ነዉ። እናም ማኅበረሰባቸዉ ይህን ባይፈፅምም ሕግ መደንገጉ ግድ ሆኖባቸዋል። ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንደባህላዊ እሴት የሚመለከተዉ ኅብረተሰብ ጉዳቱን ተረድቶ እስከወዲያኛዉ እንዲተወዉ ምን ቢደረግ ይሻላል? ለሚለዉ ወ/ሮ ዘምዘም ሃሳባቸዉን እንዲህ ሰጥተዋል። ዝርዝሩን ከድምፅ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic