1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለወልቃይትና ራያ አወዛጋቢ አካባቢዎች ፖለቲካዊ መፍትሔ ተጠየቀ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10 2016

የወልቃይት፣ ጠገዴ ጠለምትና ራያ ጉዳይ በፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲፈታ በአሜሪካ የሚገኙ 8 ኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ።

https://p.dw.com/p/4ewP1
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈራሚዎች ከአፍሪቃ ኅብረት አደራዳሪዎች ጋር
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈራሚዎች ከአፍሪቃ ኅብረት አደራዳሪዎች ጋርምስል PHILL MAGAKOE/AFP

ወቅታዊ ምላሽ የሚፈልገው የማንነት ጥያቄ

የወልቃይት፣ ጠገዴ ጠለምትና ራያ ጉዳይ በፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲፈታ በአሜሪካ የሚገኙ 8 ኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ።  ድርጅቶቹ "ማንነቱን እና ርስቱን አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ ኖሮም አያውቅ"በሚል ርዕስ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ መንግስት ለወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ሕዝብ  የማንነት ጥያቄ በአፋጣኝ እውቅና እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የፌዴራል መንግሥት፣ጉዳዩን ለመፍታት የመንግሥት፣ የዐማራና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ በሥራ ላይ መሆኑን ገልጿል። 

ድርጅቶቹ በዚሁ መግለጫቸው፣ የዐማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ያነሳባቸው ወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ፣ ከህገ መንግስቱ መጽደቅና ከፌደራል ስርአቱ መዋቅር በፊት እንደሆነ፣ መንግስት በተደጋጋሚ የገለጸው እውነት መሆኑን አውስተዋል።

ወቅታዊ ምላሽ የሚፈልገው የማንነት ጥያቄ

ነገር ግን ለእዚህ ፍትሃዊ ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ መስጠት ሲገባ፣ ከሚገባው በላይ እየተጓተ በትግራይና በዐማራ ሕዝብ መኻከል አላስፈላጊ ውጥረትና ሽብር የፈጠረ ነው ሲሉ አመልክተዋል።

የመግለጫውን ዓላማ አስመልክቶ የነጋገርናቸው፣በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የልሳነ ግፉዓን ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪ፣ አቶ ቻላቸው አባይ እንደሚከተለው መልሰዋል።

" የመግለጫው ዋና ዓላማ፣እንዲተላለፍ የፈለግነው፣ የፌዴራል መንግሥቱና ሃገር በቀል ጠላት የሆነው ትህነግ፣በጋራ ለዐማራ ሕዝብ ያላቸው ንቀትና ጥላቻ በተግባር ለመፈጸም፣ሃገሪቷንም ለመበታተን፣ህዝቦቿንም  ለማጫረስ፣ መሬቷንም ለመውረር ሕጋዊና ፍትሓዊ ጥያቄዎችን ለማዳፈን፣እየሄዱበት ያለውን የሃገር ክህደት በመገንዘብ፣ ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡና  ሃገርም የማፍረስ ወገንን ለዳግም እልቂት እንዲታደጉ ለማሳሰብ እና መሰል ጉዳዮች በሚመለከት፣እነዚህ ስምንት ድርጅቶች በዐማራም በኢትዮጵያም በአጠቃላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተሰባስበው ይህንን መግለጫ ለመውጣት ተገደዋል።"

የሕወሓትት እና የፌዴራል መንግስት በናይሮቢ ድጋሚ በተገናኙ ጊዜ
ፎቶ፦ ከማኅደር ። የሕወሓትት እና የፌዴራል መንግስት ከናይሮቢው ስምምነታቸው በኋላ በናይሮቢ ድጋሚ በተገናኙ ጊዜምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የአካባቢዎቹ  ሕዝብ ፍትሃዊ ጥያቄ በህዝቦች መኻከል ግጭት ከመፍጠሪያነት ወጥቶ፣ በአፋጣኝ ግልጽ እና ፍትሃዊ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል ድርጅቶቹ።

ስለሆነም፣የኢትዮጵያ ህዝብ ከወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ህዝብ ፍትሃዊ ጥያቄ ጎን በመቆም፣ ህዝቡ ፍትሕ እንዲያገኝ በመንግስትና በውሳን ሰጪ አካላት ላይ ጫና  እንዲፈጥር ጥሪ አቅርበዋል።

ፖለቲካዊ ውሳኔ

ጉዳዩ የሚፈታው፣በፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑ ለማንም ግልጽ እንደሆነም አመልክተዋል።  አወዛጋቢ ከሆኑት አካባቢዎች መኻከል፣ በራያ አካባቢ  የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክቶ የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪው የሚከተለውን ብለዋል።

"በራያ አካባቢ የተደረገው፣ይህ አሁን እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ከፌዴራል መንግስቱ እውቅና ውጭ አለመሆኑን፣ይልቁንም በጋራ እየሰሩት መሆናቸውን በሚገባ ገልጸውልናል።ምንም ጥርጥር የለውም ይህ ሊደረግ እንደሚችል እናውቃለን።በተለይ በወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምት ያለው ህዝብ ይሄ እንደሚመጣ ከአሁኑ ተገንዝቦ፣ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረገ ነው።"

የፕሪቶሪያው ስምምነት

የፕሪቶሪያው ስምምነት፣በወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ላይ፣ የመፍትሄ መመሪያ ሊሆን እንደማይችል የድርጅቶቹ መግለጫ አመልክቷል።

የትግራይ ሕዝብ በተለይ ልሂቃኑ ጠብ አጫሪነት ያሉትን የህወሓት እርምጃ ሊያወግዙና ለሰላምና ፍትህ ዘብ እንዲቆሙ ያሳሰበው መግለጫው፣ በዝምታ ድጋፍ መስጠት እና የጥፋቱ ተባባሪ መሆን ከታሪክና ትውልድ ተጠያቂነት አያድንም ብለዋል።

ፎቶ፦ ከማኅደር፤ አማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋዘጋቢ ቦታ
ፎቶ፦ ከማኅደር፤ አማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋዘጋቢ ቦታምስል Tsegaye Eshete/DW

የወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው፣በሕዝበ ውሳኔ እንደሆነ የፌዴራል መንግስቱ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል።

የፌዴራል መንግስት የመፍትሔ አቅጣጫ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በቅርቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፣ጉዳዩን ለመፍታት ከፌደራል መንግስት እንዲሁም ከሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ ስራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

"መንግሥት የማንነትና የወሰን ጥያቄ  በሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንደሚፈታ ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጧል።ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ፣ለጊዜው ትርፍ የሚያስገኝ ቢመስልም፣ዘላቂነት አይኖረውም።ይህንን ታሳቢ በማድረግ፣ከፌዴራል መንግስትና ከሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች የተውጣጣው ዐቢይ ኮሚቴ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።የወሰንና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የፌዴራል መንግሥት ማለትም የመከላከያ ሰራዊታችን ሰላምና ደህንነት ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በትብብር ይቆጣጠራል፣ይጠብቃል።"ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ