ለኢንተርኔት ክልከላ የባለሙያ መላ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 20.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ለኢንተርኔት ክልከላ የባለሙያ መላ

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ድረገጾችን መጎብኘትም ሆነ አፕልኬሽኖችን መጠቀም እንዳልቻሉ ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ ከመዲናይቱ አዲስ አበባ ውጭ ያሉ ተጠቃሚዎች ደግሞ የተንቃሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት ጭርሱኑ መቋረጡን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

የኦሮሚያ ነዋሪዎች “ኢንተርኔት በሞባይል አይሰራም” ይላሉ

በኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ወዲህ የፖለቲካው የሙቀት መለኪያ ከፍ ባለ ቁጥር ይከተላል ተብሎ የሚሰጋው ግድያ እና እስራት ብቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ የፖለቲካው አየር ይበልጥ መዳመን ሲይዝ በብዙ ከተሜ ወጣት ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚጠበቅ አንድ ነገር አለ - የኢንተርኔት መቋረጥ፡፡ በዚህ እርምጃ ዋነኛ ተጠቂ የሚሆነው ደግሞ “በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ 4ጂ ድረስ ተመንድጓል” በሚል በብቸኛው የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ኢትዮ -ቴሌኮም ብዙ የሚወራለት የተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ሳምንትም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአዳማ ነዋሪ በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ኢንተርኔትን አብዝተው እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ በስልካቸው ኢንተርኔት ካገኙ ግን አንድ ሳምንት እንዳለፋቸው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የገጠማቸውን ችግር ያስረዳሉ፡፡ “ምንም የለም፡፡ ፌስ ቡክ የለም፡፡ ኢንተርኔት በአጠቃላይ ምንም የለም፡፡ ዜሮ ነው፡፡ ምንም ነገር የለም፡፡ እኛ በጣም ተቸግረናል፡፡  ከውጭ ጋር የምንገናኝበት፣ መረጃ  የለንም፡፡ አንድ ነገር የሚተላለፍ የለም፡፡ በስቃይ ላይ ነው ያለነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተማሪዎች ዳውንሎድ እናደርጋለን እንላለን፡፡ እንድ የረባ ነገር የለም፡፡ ከዓለም ጋር፣ ከሀገር ውስጥም ከምንም ግንኙነታችን ተቋርጧል” ይላሉ የአዳማው ነዋሪ፡፡

የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት እኚሁ የአዳማ ነዋሪ ለትምህርታቸው የሚጠቅማቸውን መረጃ ብዙውን ጊዜ ከኢንተርኔት ያፈላልጋሉ፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ግን “ከኢንተርኔት መረጃዎች ማውረድ (ዳውንሎድ) ይቅርና ከጓደኞቻቸው ጋር እንኳ መልዕክት መለዋወጥ አልቻልኩም” ይላሉ፡፡ የግድ ሲሆንባቸው ግን ብሮድባንድ እና ገመድ አልባ የኢንተርኔት ግንኙነት ያለባቸው ቢሮዎች እየሄዱ ደጅ ይጠናሉ፡፡ የተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት ወደነበረበት ይመለሳል በሚል በየጊዜው መሞከራቸውንም አልተውም፡፡  

“ለምሳሌ ኢትዮ ገበታ የሚባል አለ፡፡ እንገዛለን፡፡ ብራችንን ይዞ እዚያው ይቀልጣል፡፡ የኢንተርኔት እና የድምጽ የጥቅል አገልግሎት አለ፡፡ ካልተጠቀምክ በ24 ውስጥ ያልቃል፡፡ እኛ ለዛሬ ማታ ዳውንሎድ እናደርጋለን ብለን ከገዛን ወይም ዛሬ ቀን ካደረግን ከ24 ሰዓት በኋላ የለም፡፡ ገዝተን እንደዚያ ቀልጧል፡፡ ሳይነገረን ነው የተቋረጠው፡፡ ብራችን እዚያው ቀርቷል” ሲሉ ያማርራሉ፡፡  

የአዳማው ነዋሪ የኢንተርኔት መቋረጡ በእርሳቸው ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎችም እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡ “ኦሮሚያ ጠቅላላ የለም፡፡ አንድም ቦታ የለም፡፡ እኔ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ሀረርጌ፣ አሰላ፣ ባሌ፣ ቦረና፣ ወለጋ አይሰራም፡፡ ተማሪዎች ነን፡፡ ሁላችንም እንገናኛለን፡፡ እንደዋወላለን፡፡ ከቤተሰብ ጋር እንገናኛለን፡፡ ከጓደኞች ጋር በየቀኑ በፌስቡክ በቻት እንገናኛለን፡፡ [ካለፈው] ሳምንት ጀምሮ ተቋርጧል፡፡ የለም” ይላሉ የአዳማው ነዋሪ፡፡  

የአዳማውን ነዋሪ እማኝነት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሱሉልታ ነዋሪም ይጋራሉ፡፡ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን የመደበኛ የተንቀሳቃሽ አገልግሎት የኔትወርክ ችግር እንዳለ ከዘመድ ጓደኞቻቸው መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡ የኔትወርክ ሙሉ ለሙሉ የመቋረጥ ችግር ትላንት ማክሰኞ ታኅሳስ 10 በሱሉልታም ተከስቶ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በአካባቢያቸው ስላለው የተንቃሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት ችግር ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡ “አሁን ያለው ሁኔታ ምንም ነገር አናይም፡፡ ፌስ ቡክ ተዘግቷል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወደዚህ ወደ ሱልልታ ጭራሽ ዳታው አይከፍትም፡፡ ከዋትስ አፕ ፎቶ እና የተቀዳ ድምጽ አይወርድም፡፡ ጽሑፍ ብቻ እናያለን፡፡”

የሱሉልታው ነዋሪ የኢንተርኔት አገልግሎት መስተጓጉሉን “ከባድ ችግር ነው” ይሉታል፡፡ የፈጠረባቸውን ችግር ደግሞ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፡፡ “ከባድ ተጽእኖ ነው፡፡ በስራም በሁሉም ነገር፡፡ በሀገሪቱን ሁኔታ አንዳንድ የምናገኘውን መረጃ አለማግኘት ራሱ በጣም ከባድ ነው” ይላሉ ነዋሪው፡፡ 

ከሱሉልታ አቅራቢያ በምትገኘው በመዲናይቱ አዲስ አበባም የኢንተርኔት ችግር ይስተዋላል፡፡ አገልግሎቱን በተለይ ማግኘት የማይቻለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለመጠቀም ሲሞከር እንደሆነ ተገልጋዮች ይናገራሉ፡፡ ማንነቱ እንዳይገለጽ የሚፈልግ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ይህን የተጠቃሚዎችን አስተያየት ያረጋግጣል፡፡ 

“አዎ በእርግጥ የተወሰኑ የማኅበረሰብ ድረገጾች እና አፕልኬሽኖች ተዘግተዋል፡፡ ከእነሱ መሃል እነ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም ተዘግተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ቫይበር እና ዋትስ አፕ ላይ የጽሁፍ ግንኙነት የተፈቀደ ቢሆንም ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን መለዋወጥ የተከለከለ ነው፡፡ በዚያ መልኩ ነው የተዘጋው፡፡ ግን አዘጋጉን ይሄ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ጠዋት አካባቢ ቫይበርም ሆነ ዋትስ አፕ አይሰራም ነበር፡፡ አሁን እየሰሩ ናቸው፡፡ ቴሌግራምም፣ ሁሉም ይሰራሉ፡፡ እና እንደ መጣ፣ እንደመሄድ ነገር እያለ ነው፡፡ ግልጽ ሆኖ እነኚህ ተዘግተዋል፤ እነዚያ አይዘጉም ለማለት የሚያስቸገርበት ቦታ ላይ ነው ያለነው” ይላል ባለሙያው፡፡ 

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንዲህ እንዳሁኑ ጊዜ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን እንዳይጠቀሙ እቀባ ሲጣልባቸው እገዳውን ጥሰው አገልግሎቱን የሚያገኙባቸው ዘዴዎች ነበሩ፡፡ እንደ ሳይፎን (Psiphon)፣ ኦፔራ ማክስ (Opera Max) እና አልትራሰርፍ (UltraSurf) አይነት አፕልኬሽኖችን በመጠቀም የተከለከሏቸውን ድረ ገጾች ሲጎበኙ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የነበረው የኢንተርኔት እገዳ እነዚህንም ከአገልግሎት ውጭ ያደረገ ነበር፡፡ ከቀናት በኋላ የተወሰኑት እንደቀድሞው መልሰው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተጠቃሚዎችም ሆነ ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ እንዲህ ሄድ መለስ የሚል የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ለተጠቃሚዎች እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ “ኢንተርኔት ተዘጋ” ሲባል ግን ወይ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ ይቋረጣል አሊያም የተወሰኑ አገልግሎቶች ተለይተው እገዳ ይጣልባቸው ነበር፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው ባለፈው ዓመት ከግንቦት ወር መጨረሻ ግድም ጀምሮ የነበረውን የኢንተርኔት መቋረጥ ከአሁኑ የአገልግሎቱ እቀባ ጋር ያነጻጽራል፡፡ 

“ባለፈው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የሆኑ ድረገጾች ወይም የሆኑ አፕልኬሽኖች በግልጽ ተዘግተው ነበር፡፡ ከዚያ ወደ በኋላ ሁሉም ተዘግቶ ነበር፡፡ ጭራሽ የሆነ ጊዜ ላይ ምንም አይነት የdata ግንኙነት በስልክም፣ በኮምፒውትርም፣ በኤድኤስኤልም (ADSL)፣ በገመድ አልባም (wireless) የለም ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሰው ሲመጡ መጀመሪያ የADSL ተለቀቀ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ data ተመጣና የቀሩት ድረ-ገጾች ተለቀቁ ማለት ነው፡፡ አሁን ግን በግልጽ እነዚህ ድረገጾች ተዘግተዋል ልልህ አልችልም፡፡ እኔ ጋር ትላንት ሳይፎን አይሰራም ነበር፡፡ ዛሬ ይሰራል፡፡ ADSL ዋትስአፕ አይሰራም ነበር፡፡ ያለሁበት አካባቢ ቆሞ ነበር፡፡ ዛሬ እየሰራ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ነገ ደግሞ ያለው ሁኔታ አሁን የሆነ ነገር ብልህ ተቀይሮ ነው የሚጠብቅህ” ሲል በየጊዜው ተለዋዋጭ ስለሆነው የኢንተርኔት አዘጋግ ያስረዳል፡፡  

እንዲህ በየጊዜው ተቀያያሪ በሆነው የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ክልከላ ለተጠቃሚዎች ሁነኛ መላ የሆነው የVPN ግንኙነትን አሊያም ፕሮክሲ ሰርቨሮችን (Proxy Servers)  መጠቀም ነው፡፡ ኢንተርኔት በሚዘጋባቸው በሌሎች ሃገራትም በመፍትሄነት እያገለገሉ ስለሚገኙት ስለእነዚህ ሁለት ዘዴዎች ባለሙያው ማብራሪያ አለው፡፡ 

“VPN ማለት ሲተነተን Virtual Private Network ነው፡፡ ኢንተርኔት ያው በጣም ትልቅ፣ ሰፊ ነው፡፡ በኢንተርኔት ውስጥ የትም አካባቢ ሆነህ የራስህ የሆነ ትንሽዬ ኔትወርክ [መፍጠር ነው]፡፡ እንደ ኢንተርኔት ቤት ያለ ኔትወርክ አስብ፡፡ በመላው ዓለም ባሉ የተወሰኑ ኮምፒውተሮች ላይ እንደዚያ አይነት ኔትወርክ መስራት ነው የVPN ሀሳብ፡፡ ፕሮክሲም በተመሳሳይ ነገር ነው የሚሰራው ግን የደህንነት ነገሩ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ፕሮክሲ ኔትወርክ ነው ስልህ ከአንተ እና ከዚያኛው አግልግሎት ጋር አስተማማኝ በሆነ የመረጃ ማስተላለፊያ፣ የራሳችሁ የሆነ ምስጢራዊ ነገር መላላክ የምትችሉበት የተመቻቸ ነገር ነው፡፡ 

በቀላሉ ለመግለጽ ለምሳሌ አንድ ሰው ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ ከተከለከለ እና ከጎረቤት ሀገር ደግሞ ሌላ ሰው መሄድ የሚችል ከሆነ መጀመሪያ ወደ ጎረቤት ሀገር ይሄድ እና ቀጥሎ ወደዚያኛው [ወደተከለከለው ሀገር] መሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ያችን የጎረቤት ሀገር እንደ VPN ወይም እንደ proxy server ተጠቀመባት ማለት ነው፡፡ የVPN እና የproxy server ሀሳቡ ይሄው ነው” ይላል ባለሙያው፡፡

በአሁኑ የኢንተርኔት እገዳ የተወሰኑ የVPN አፕልኬሽኖች ለቀናት መዘጋታቸው “ምኑን መፍትሄ ሆኑት?” የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ባለሙያው “ለዚህም ቢሆን መላ አለ” ባይ ናቸው፡፡ “ቪ.ፒ.ኤኖቹ ለእኛ አገልግሎቱን በሚያቀርብልን ድርጅት ወይም በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ቀጥታ ወደ ፌስቡክ እና ወደዋትስ አፕ የምንልካቸውን በዚያ የሚያልፉትን ትራፊኮች አዙረው ወደሌላ ወዳልተከለከለ ድረገጽ በኩል አድርገው ስለሚያሳልፉት ያንን ለመከልከል አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ እያንዳንዳቸውን እግር በእግር ተከታትሎ መዝጋት ይቻላል፡፡ ሆኖም ይህ እንዳለ ሆኖ የተሻለ አማራጭ የሚመስለኝ በዛ ያሉ ቪ.ፒ.ኤኖችን በስልክም ሆነ በኮምፒውተር ይዞ መገኘት ነው” ሲል መፍትሔውን ይጠቁማል፡፡ 

ባለሙያው ተጠቃሚዎች ሊገለገሉባቸው የሚችሏቸውን የVPN አፕልኬሽኖች እንዲህ ይዘረዝራቸዋል፡፡ “VPN Speed የሚባል አፕልኬሽን አለ፡፡ ጥሩ ነው፤ ይሰራል፡፡ ግን ኮኔክት ሲያደርግ ትንሽ ዘግየት ይላል፡፡ VPN Master የሚባልም አለ፡፡ እርሱ በነጻ አይገኝም ግን የአፕልኬሽኑ premium version በደንብ ይሰራል::  እስካሁን ምንም ዓይነት ችግር አላየሁበትም፡፡ ቀጥሎ ደግሞ VPN Gate የሚባል አለ፡፡ እርሱም በአሁን ሰዓት በደንብ ይሰራል፡፡ Super VPN የሚባለው ከሆነ ጊዜ በኋላ መስራት አቁሟል፡፡ ስለዚህ እርሱን እንድትጠቀሙ አልመክርም፡፡ ምክንያቱም እንደድሮው ፍጥነት የለውም፡፡ አገልግሎቱም ያን ያህል አይደለም፡፡ ሳይፎን አሁንም በትክክል ይሰራል፡፡ በተጨማሪ Open VPN አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ አፕልኬሽኖች በGoogle Play Store ላይ የሚገኙ አፕልኬሽኖች ናቸው፡፡ ወይም ደግሞ ከጓደኞቻችሁ Xenderን በመጠቀም መለዋወጥ እና መጠቀም ይቻላል፡፡ 

ሶፍትዌር መጫን ለማይችሉ ለMac ተጠቃሚዎች ደግሞ VPNme.me የሚባል ድረገጽ አለ፡፡ ከዚያ ላይ የመጠቀሚያ ስም (username) እና የይለፍ ቃል (password) ብቻ በማውረድ የVPN አገልግሎት ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ተጨማሪ ሶፍትዌር መጫን ሳያስፈልግ አፕል ስልኮች ላይም ሆነ ማክ ኮምፒውተሮች ላይ ይሄን ነገር መጠቀም ቀላል አማራጭ ነው” ይላል ባለሙያው፡፡ 

በኢትዮጵያ በብዙ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚዘወተሩ ውሱን አፕልኬሽኖች አሉ፡፡ ባለሙያው እንደዚህ አይነት ቪ.ፒ.ኤኖችን አስመልክቶ የመጨረሻ ምክር አለው፡፡

“ብዙ ዝነኛ የሆኑ ቪ.ፒ.ኤኖች ስትጠቀም ትራፊክ በጣም ስለሚጨምር ኮኔክት የማድረግ ዕድልህ እና የምታገኘው ፍጥነት በዚያው ያህል እየወረደ ስለሚሄድ የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ የምመክረው ጥናት አድርጎ የተሻሉ ነገሮችን ወይ ብዙ ሰው የማያውቃቸውን ነገሮች  ብትጠቀም ጥሩ ነገር ታገኛለህ” ሲል ይደመድማል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic