ለኢትዮጵያ አዲስ ርእሠ ብሔር ተሾመ
ሰኞ፣ መስከረም 27 2017የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት እና ለረጅም ዓመታት በዲፕሎማሲ ዘርፍ ያገለገሉት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ርእሠ ብሔር ሆነው ተሾሙ።
በሀገሪቱ የፕሬዝዳንትነት ታሪክ ስድስተኛው ሆነው ዛሬ መስከረም 27 ቀን የተሾሙት ርእሠ ብሔር ታዬ ሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነ ጽሑፍ ያጋሩትን የቀድሞዋን ፕሬዝዳንት ሳኅለ ወርቅ ዘውዴን ተክተው ስልጣኑንና የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ተረክበዋል።
አስከትለው የዓመቱን የሁለቱን ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በ2017 ዓ.ም መንግሥት " የፀጥታ ሥጋትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን እንዲሁም ሕገ-ወጥነትን ለመቀነስ በርትቶ ይሠራል" ብለዋል።
መንግሥት "በተናጠልም ሆነ በጋራ በሰላማዊ መንገድ ከማንኛውም ወገን ጋር ለመነጋገር ምንጊዜም ዝግጁ ነው" ሲሉም ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግ በተሰጠው ዕጩ ርእሠ ብሔር የማቅረብ ሥልጣን መሠረት ዛሬ ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ .ም ከተደረገው የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ መክፈቻ አስቀድሞ በዝግ ባተደረገ አጭር ስብሰባ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩትን አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴን ለዚሁ ኃላፊነት አቅርቧል። ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 369፣ ከፌደሬሽን ምክር ቤት 108 አባላት እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ጉባኤ ላይ በቅቀረቡት ዕጩ ላይ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተሿሚው "ብቃትም፣ ጥንካሬም" ያላቸው መሆኑን አስተያየት የሰጡ ሲሆን የሹሙት ጥያቄውም በአምስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ስላሴ የመክፈቻ ንግግራቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ የገጠማት ያሉትን ችግር በምሳሌ በማስገንዘብ ነው። በእሳቸው አገላለጽ ሀገራቸው "እንድትንገላታ" ተገዳለች።
"የምትሻገር ሀገር በማይሻገር ሐሳብ እየተናጠች ቆይታለች። የሚታረምና የሚታረቅ የፖለቲካ ልዩነት እንደማይታረም እና እንደማይታረቅና ተደርጎ በመሠራቱ ሀገር በማይጠራ የፖለቲካ ሳንካ እንድትንገለታ ተገዳለች ። አሁን ላይ ጋን በጠጠር ይደገፋል የሚለውን ነባራዊ ሀገራዊ ብኂል ጠጠር በጋን ይደገፋል ወደሚል ትርጉመ-ቢስ አባባል የቀየርነው ይመስላል"።
ከተሰናባቿ የኢትዮጵያ የቀድሞ ርእሠ ብሔር ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ የሥልጣንም፣ የሕገ መንግሥትም ርክክብ ያደረጉትአዲሱ ፕሬዝዳንት የዚህ ዓመት የመንግሥት የሥራ ትኩረት ምን እንደሚሆንም አብራርተዋል።
"ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቁልፍ ሥራዎች ይሆናሉ። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቶች አፈፃፀም የሚሻሻልበት ይሆናል። በመንግሥት በኩል ዛሬም የሰለም በሮችን ሁሉ ወለል ብለው እንደተከፈቱ ናቸው"።
በተለያዩ ሀገራት በአምባሳደርነት ሲሰሩ በአጠቃላዩም በዲፕሎማሲ መስክ ከአርባ ዓመታት በላይ ያገለገሉት አዲሱ ተሿሚ ርእሠ ብሔር በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሰርተዋል፣ በቅርቡ በተደረገው 79 ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይም የተገኙት እሳቸው ነበሩ። በሀገር ውስጥ የፀጥታ ችግር እና በእርስ በርስ ግጭት በምትታመሰው ኢትዮጵያ፣ መንግሥት ለንግግር ዝግጁ መሆኑንም ዘለግ ባለው ንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
"በተናጠልም ይሁን በጋራ በሰላማዊ መንገድ ከማንኛውም ወገን ጋር ለመነጋገር መንግሥት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። ከዚህ ውጭ ግን የኃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጓቶችን ለማሟላት የሚደረጉ ማናቸውንም ዕኩይ ተግባራትን መንግሥት በልበ ሰፊት የሚያይበት ዕድል እጅግ የጠበበ ነው። ሕህዝባችንን የዘመናት አብሮነትና እሴት የሚያላሉ ተግባራት በሚፈፅሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ፤ በጥላቻ ንግግር የሕዝብን አብሮነትና ማሕበራዊ ሕይወት አደጋ ላይ በሚጥሉና ሕዝብን ከሕዝብ በሚያጋጩ አካላት ላይ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃን የሚወስድ ይሆናል።»
ድህነትና ኋላ ቀርነት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀጥሏል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ ዓመት መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገቱን በ 8.4 የማሳደግ ውጥን እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዓመት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ እኩልነት፣ ከነጠላ ይልቅ ሀገራዊ ያሉት ትርክት እንዲጎላ ጥረት የሚደረግ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥረቷን ገፍታ እንደምትቀጥልበት ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ እንዲሆን "ትጉህ ተሳትፎ" እንደምታደርግ ገልፀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ