ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች በማሽን የትርጉም አገልግሎት የሚሰጠው ልሳን | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 30.09.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች በማሽን የትርጉም አገልግሎት የሚሰጠው ልሳን

ለአራት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በማሽን የትርጉም አገልግሎት ለማቅረብ በበርሊን ከተማ የተቋቋመው ልሳን የተባለ ኩባንያ ሥራ ጀምሯል። በኢንተርኔት በነፃ የሚሰጠው የትርጉም አገልግሎት ለአማርኛ ከቀናት በፊት ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን ለትግርኛ፣ ለኦሮሚኛ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች በመጪዎቹ ጊዜያት ይቀጥላል። ለመሆኑ ማሽን የትርጉም ሥራ እንዴት ይማራል?

ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፦ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች በማሽን የትርጉም አገልግሎት የሚሰጠው ልሳን

ከአስራ ስድስት አመታት ገደማ በፊት አንድ ተብሎ የተጀመረው የዊኪፒዲያ አማርኛ ገጽ እስከ ዛሬ ድረስ በውስጡ የያዛቸው መጣጥፎች ከአስራ አምስት ሺሕ በታች ናቸው። የኦሮሚኛ ቋንቋ ገፅ ከአንድ ሺሕ በታች መጣጥፎች ሲይዝ በትግርኛ ቋንቋ የሚገኙት መጣጥፎች 200 እንኳ አይሞሉም። ይኸን ለማነፃጸር በሌሎች ቋንቋዎች የሚዘጋጁ የዊኪፒዲያ ገፆችን መመልከት ጠቃሚ ይሆናል።

ለምሳሌ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የዊኪፒዲያ ገጽ ከስድስት ሚሊዮን በላይ መጣጥፎች ይገኛሉ። የጀርመንኛ ሁለት ሚሊዮን፤ በቻይንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጃፓንኛ እና አረብኛ ገፆች እያንዳንዳቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ መጣጥፎች ይዘዋል። እንግሊዘኛ፣ ጀርመንኛ ወይም ፈረንሳይኛ ለማይናገሩ አፋቸውን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም ትግርኛ ለፈቱ ሰዎች ከኢንተርኔት መረጃዎችን ለማግኘት ምን ያክል ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ዊኪፒዲያ አንድ ማሳያ ነው።

“በድር የሚገኙ አብዛኛዎቹን ይዘቶች ከተመለከትክ የሚቀርቡት በእንግሊዘኛ እና በሌሎች በጣት የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ነው። ለምሳሌ እውቀት ተደራጅቶ የሚሰነድበትን ዊኪፒዲያን ውሰድ። የትግርኛ ዊኪፒዲያ ወይም የአማርኛ ዊኪፒዲያን ብትመለከት ያን ያክል መጣጥፎች አታገኝም። የመፈለጊያ ድሮችን መረጃ ስትጠይቃቸው ከእነዚህ የእውቀት ማከማቻዎች የምትፈልገውን ሊያቀርቡልህ አይችሉም። ምክንያቱም በአማርኛ ወይም በትግርኛ አልተጻፉም” የሚለው ኢትዮጵያዊው አስመላሽ ተካ ይኸ በኢንተርኔት በሚቀርብ የትርጉም አገልግሎት ሊቀየር ይችላል የሚል ዕምነት አለው።

በኢንተርኔት የሚገኙ መጣጥፎችን፣ መረጃዎችን ወይም ሰነዶችን በሰው ኃይል ተርጉሞ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ረዥም አመታት እንደሚወስድ የሚገልጸው አስመላሽ “የማሽን ትርጉም (machine translation) በመጠቀም እነዚህን የእውቀት ማከማቻዎች ሰዎች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ እንችላለን” ሲል ይናገራል።

አስመላሽ የጠቀሰው የማሽን ትርጉም (machine translation) ከዚህ ቀደም ጉግል እና ማይክሮሶፍትን በመሳሰሉ ኩባንያዎች ሲሰራበት የቆየ ነው። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን በኢትዮጵያ ጀምሮ በአውሮፓ የማስተርስ እና የፒኤችዲ ዲግሪውን የተማረው አስመላሽ ከሥራ ባልደረባው አዳም ቡድዌይን በመተባበር ለአማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች የትርጉም ግልጋሎት የሚሰጥ ልሳን የተባለ ኩባንያ አቋቁሟል።

የልሳን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዳም ቡድዌይን “ሁለታችንም ድርን ለሁሉም ማኅበረሰቦች ተደራሽ የማድረግ ፍላጎት አለን። ምክንያቱም በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት፤ አስርት አመታት ወይም በሕይወት እስካለን ድረስ በድር በኩል የሚገኝ በርካታ ዕድል አለ። እነዚያን ዕድሎች ሁሉም ማግኘት መቻሉ እጅግ ጠቃሚ ነው”ሲል ከልሳን መቋቋም ጀርባ ያለውን ገፊ ምክንያት አስረድቷል።

የልሳን መሥራቾች የሰው ልጆች ሁሉ በድረ-ገጽ የሚገኙ መረጃዎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሊያገኙ ይገባል የሚል አቋም አላቸው። “ሁሉም ሰው ዓለምን ለመረዳት ይችል ዘንድ እኩል መረጃ የማግኘት ዕድል እንዲኖረው ማረጋገጥ እንፈልጋለን” የሚሉት የልሳን መሥራቾች በኩባንያው ድረ-ገጽ ባሰፈሩት መረጃ ሰዎች ከመላው ዓለም ከተለያዩ ምንጮች መረጃ እዲያገኙ በማመቻቸት የሐሰት ዜናን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት የመደገፍ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

Detuschland Berlin | Startup | Lesan Übersetzungsmaschine

በኢንተርኔት በነፃ የሚሰጠው የትርጉም ግልጋሎት ለአማርኛ ከቀናት በፊት ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን ለትግርኛ፣ ለኦሮሚኛ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች በመጪዎቹ ጊዜያት ይቀጥላል

አዳም ቡድዌይን እና አስመላሽ ተካ የተገናኙት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማጣመር በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ነው። በመድረኩ ለሶስት ወራት የመወያየት ዕድል የሚያገኙት ባለሙያዎች ሐሳብ ይለዋወጣሉ፤ ዕቅዶቻቸውን ይነጋገራሉ፤ ደንበኛ ሊሆኑ ከሚችሏቸውም ይመክራሉ።

“አስመላሽ ይኸ በኢትዮጵያ ትልቅ ችግር እንደሆነ ያውቅ ነበር። ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥሩ machine translation system ወይም automatic translation system ባለመኖሩ ይኸ መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ ትልቅ ችግር መሆኑን ታዝቦ ነበር። ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስፈልገው ቴክኒካዊ እውቀትም ከሞላ ጎደል ነበረው። በዚያ ላይ ተመስርተን መስራት ጀምረን እያደገ ሔዶ በዚህ ኩባንያ ስንሰራ ይኸው አመት ከስድስት ወር ገደማ ሆነን” ይላል አዳም ቡድዌይን ስለኩባንያው አመሠራረት ሲያስረዳ።

አንድ አመት ተኩል በላይ ከወሰደ ሥራ በኋላ ልሳን በድረ-ገጽ በኩል ይፋ ሆኗል። የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ልሳን ኤአይ በተባለው ድረ-ገጽ ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ ወይም ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ አጫጭር አረፍተ ነገሮችን ካለፈው መስከረም 01 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መተርጎም ይችላሉ። የትግርኛ ቋንቋ ትርጉም አገልግሎት በመጪዎቹ ሳምንታት ይጠበቃል። ኦሮሚኛ እና ሶማሊኛ ይከተላሉ።

የልሳን ትርጉም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለ ሰው ዕገዛ ለዚሁ ሥራ በተዘጋጀ ማሽን ብቻ የሚከወን ነው። ለዚህም የልሳን ቴክኖሎጂ ቋንቋ መማር ይኖርበታል። አስመላሽ እንደሚለው ልሳንን ሥራ ላይ ለማዋል ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የትርጉም ሥርዓት ለመገንባት ግልጋሎት ላይ ከዋሉ ዘዴዎች የተለየ ቴክኖሎጂ ተጠቅመዋል።

“ሥርዓቱ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ምሳሌዎች ይማራል። Thirteen months of sun shine የአስራ ሶስት ወራት የጸሀይ ብርሀን I like Enjera እንጀራ እወዳለሁ። እንዲህ አይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምሳሌዎች ይኖራሉ። አንድ ሰው I like sun shine ብሎ ሲጽፍ፤ እንዲህ አይነቱ ምሳሌ በስልጠና ሒደቱ ታይቶ ባይታወቅም ሥርዓቱ sun shine የሚለውን ቃል፦ የአስራ ሶስት ወራት የጸሀይ ብርሀን ከሚለው ምሳሌ ወስዶ ይተረጉማል። I like የሚለውን ከሌላኛው የማስተማሪያ ምሳሌ፦ እንጀራ እወዳለሁ ከሚለው ይወስዳል። ከዚያ ይኸ አረፍተ ነገር ጸሀይ ብርሀን እወዳለሁ የሚል ትርጉም እንዳለው ይረዳል”ሲል ማሽንን ትርጉም የማሰልጠን ሒደት ምን እንደሚመስል አስመላሽ በምሳሌ አስረድቷል።

ልሳን እንደ ጉግል እና ሌሎች ተመሳሳይ ግልጋሎት አቅራቢ ቴክኖሎጂዎች ሁሉ አጫጭር አንቀፆችን ይተረጉማል። ተጠቃሚዎች በርከት ወይም ረዘም ያለ ጽሁፍ ካላቸው ወደ አጫጭር አገዳዎች በመከፋፈል እንዲተረጉምላቸው ማቅረብ እንደሚገባቸው አስመላሽ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። ለአጫጭር ዓረፍተ ነገሮችም ሆነ ለአንቀጾች እንደ ልሳን አይነቶቹ ቴክኖሎጂዎች የሚሰጡት ትርጉም ሁልጊዜ የተዋጣለት አይሆንም።

Detuschland Berlin | Startup | Lesan Übersetzungsmaschine

ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ የልሳን የማሽን ትርጉም

“እኛም ሆንን ጉግል፤ ማንኛውም የማሽን ትርጉም አቅራቢ ዋስትና ማቅረብ አይችልም። ማሽን በመሆኑ ሁልጊዜ መቶ በመቶ ትክክለኛ ትርጉም ሊሰራ እንደማይችል ሁሉም ሰው ያውቃል። ለአንዳንድ ቋንቋዎች የተሻለ ነው፤ ለሌሎች ደግሞ የከፋ ይሆናል። ተጠቃሚዎች ቴክኒካዊ ጽሁፎች ለመተርጎም ቢሞክሩ ትርጉሙ ፍጹም እንደማይሆን ግልጽ ነው” የሚለው አዳም ቡድዌይን ለሰነዶች “በጣም ጥሩ ትርጉም መሥራት የሚችል አገልግሎት አለን” ብሏል።

አዳም እንዳለው ይኸኛው አገልግሎት ቴክኖሎጂን በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሙያተኛ ተርጓሚዎች ጋር በማጣመር አስተማማኝ ትርጉም የሚያቀርብ ነው። “አሁን በነፃ ማንኛውም ሰው እንዲጠቀምበት የጀመርንው የትርጉም አገልግሎት የተለመዱ ጽሁፎችን ለመተርጎም የተሰራ ነው። ለምሳሌ እኔ ለጀርመንኛ ዴፔል የተባለውን መተርጎሚያ ስጠቀም ስህተት እንደሚሰራ አውቃለሁ። ስለዚህ ተገልጋዮች ትርጉሙ ፍጹም እንዳልሆነ በፍጥነት ይረዳሉ። በአግባቡ የሚሰራ በጣም ጥሩ መተርጎሚያ ቢሆንም ሁልጊዜም የሚፈጠሩ የአውድ ስህተቶች ይኖራሉ። ምክንያቱም ለማሽን ትርጉም ፍጹም መሆን በጣም ከባድ ነው”

ለዚህ አንቱታ ጥሩ ምሳሌ ነው። በአማርኛ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ ያለው አንቱታ በእንግሊዘኛ ውስጥ በቀጥታ አይገኝም። የልሳን የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ የሆነው አስመላሽ እንደሚለው አንቱታ በትርጉም ሒደት ውስጥ ሊያመጣ የሚችለውን ልዩነት ለማስተማር ጊዜ ይፈጃል። “አሁን ያለን ሥርዓት ይኸን ችግር አልፈታውም። ለረዥም ጊዜም ፈታኝ ሆኖ ይቆያል። የትኛውን አንቱታ በየትኛው አውድ እንደምንጠቀም ለማስተማር በርካታ ምሳሌዎች መስጠት ይፈልጋል።  ዕድሜያቸው ከፍ ስላሉ ሰዎች እየተናገርክ ከሆነ ወደ መደበኛው የአክብሮት አጠራር ለመቀየር ወይም ከጓደኛ ጋር በሚደረግ ንግግር መደበኛ ያልሆነውን ለመጠቀም ከሁለት ወይም ሶስት አረፍተ ነገሮች በመማር ይጀምራል። በሒደት ሰዎች ልሳንን ሲጠቀሙ እነዚህን የተለያዩ አውዶች እየተለማመደ እና እየተማረ ይሔዳል” ብሏል አስመላሽ።

Screenshot Google Translator Virus in Bangla

ከተጀመረ 14 አመታት ያስቆጠረው የጉግል የማሽን ትርጉም አማርኛን ጨምሮ ለ109 ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል

ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ ወይም በተቃራኒው የትርጉም አገልግሎት በመስጠት ረገድ ጉግል ከአመታት በፊት የጀመረው ሥራ ይጠቀሳል።  የልሳን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዳም ቡድዌይን “በርካታ ሰዎች ያለባቸውን ይኸን ችግር ለሚፈታ ጥሩ የትርጉም አገልግሎት ፍላጎት እንዳለ እርግጠኞች ነን። በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ሰራተኞች ወይም የቪዛ ሰነዶች መሙላት በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ የትርጉም አገልግሎት ፍላጎት አለ። ለእንግሊዘኛ እና ለአማርኛ ትክክለኛ ትርጉም መስራት የሚችል ግዙፍ መረጃ ያለው ቋት እና አጠቃላይ ሥርዓት በማዘጋጀታችን ልሳንን ልዩ የሚያደርገው ይመስለኛል” ሲል በኢትዮጵያ ገበያ ለእንዲህ አይነት ግልጋሎት ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን እንደተረዱ ለዶይቼ ቬለ ገልጿል።

“ለትግርኛ እና ለኦሮሚኛ ቋንቋዎች እንዲህ አይነት አገልግሎት በማቅረብ እኛ የመጀመሪያ ነን። ለእነዚህ ቋንቋዎች የማሽን ትርጉም የሚሰራ ሥርዓት የለም” የሚለው አስመላሽ ከገበያው ፍላጎት በተጨማሪ ከዚህ ቀደም መሠል ግልጋሎት ላልነበራቸው ቋንቋዎች የማሽን ትርጉም ማቅረባቸው ላቅ ያለ ሚና አለው ብሎ ያምናል።

ልሳን በድረ-ገጽ ከሚያቀርበው ነፃ የትርጉም አገልግሎት በተጨማሪ ለንግድ ኩባንያዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ይሁን ለግለሰቦች አማርኛን ጨምሮ ለተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሰነዶች ይተረጉማል።  ይኸ የልሳን ቴክኖሎጂ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችን በማቀናጀት የሚሰራ ሲሆን ትርጉሙ ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን አዳም ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። ሌላው የልሳን ቴክኖጂን ያለ ገደብ የመጠቀም ፍላጎት ላላቸው የሚሰጠው የኤፒአይ (API) አገልግሎት ነው። ይኸ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አረፍተ ነገሮች መተርጎም ለሚሹ ጀማሪ ኩባንያዎች፣ ዜና እያሰባሰቡ ለተጠቃሚ የሚያቀርቡ ድረ-ገጾች እና ለመሳሰሉ በክፍያ የሚቀርብ ግልጋሎት ነው። ይኸ የግልጋሎቱ ተጠቃሚዎች አረፍተ ነገሮችን በቁጥቁጥ ከመተርጎም ይልቅ ከድረ-ገጾቻቸው በማስተሳሰር ስራውን ለማቅለል ይረዳቸዋል።

ልሳን የትርጉም አገልግሎት የሚያቀርብባቸው አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች የሚያሰባስበው የስነ ልሳን መረጃ እየተደራጀ ሲሔድ ምን አልባት ሌላ ግልጋሎት ሊጀምር ይችላል። "ወደ እንግሊዘኛ እና ከእንግሊዘኛ ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ቋንቋዎች መካከል የትርጉም አገልግሎት መጀመር ቀጣዩ እርምጃችን ይሆናል። ይኸ ድርን ለሁሉም ሰው ክፍት ማድረግን ብቻ ሳይሆን እርስ እንዲገናኙ ስለሚያደርግ ከተልዕኳች የተስማማ ነው" ሲል አስመላሽ ተካ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic