ለአፍሪቃውያን ስደት ተጠያቂው ማን ነው? | ወጣቶች | DW | 16.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ለአፍሪቃውያን ስደት ተጠያቂው ማን ነው?

ወጣቶች እንዲወያዩ መድረክ የሚከፍተው #77ከመቶው የወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን ለዛሬ ርዕሱ ያደረገው ለአፍሪቃውያን ስደት ተጠያቂው ማን ነው? የሚል ነው። ዝግጅቱም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለጥያቄው ምላሽ ነው የሚሉትን እና የአውሮፓ ህልማቸውን ግማሽ መንገድ ላይ አቋርጠው ሞሮኮ ውስጥ ኑሮዋቸውን የመሠረቱ አፍሪቃውያንን ያስቃኛኘናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

ለአፍሪቃውያን ስደት ተጠያቂው ማን ነው?

እኢአ በ 2050 ዓም በዓለም ላይ የስደተኞች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይታመናል። አፍሪቃውያን ወደፊትም የሚሰደዱባት አህጉር ደግሞ አውሮጳ ሆና እንደምትቆይ ነው የአውሮፓ ኮሚሽን ምሁሮች የሚተነብዩት። ግን ለአፍሪቃውያን ስደት ተጠያቂው ማን ነው?

በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመሰደድ እንደ መሸጋገሪያ በሚጠቀሟት ጅቡቲ ኑርየ ይኖራሉ። ከዚህ በፊት በርካታ ስደተኞች ጅቡቲ ላይ  በሰው አዘዋዋሪዎች በደል እየደረሰባቸው እንደሆነ  በ2010 መጀመሪያ ላይ ገልጸውልን ነበር፤ አሁን ያለውስ ሁኔታ ምን ይመስላል?  « በግምት ከ 50 እስከ 120 እና 130 ሰው በቀን ሲጓዝ አያለሁ። ቁጥሩ ጨምሯል።» ይላሉ።

በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን  የስራ እድል ፍለጋ በተሰደዱባት ሀገር ሳውዲ አረቢያ ተሚማ አህመድ ትኖራለች። በህጋዊ መንገድ ነው ሳውዲ አረቢያ የገባችው፣ ስራ መርጬ ሳይሆን አጥቼ ነው ትላለች። ለስደቷም ተጠያቂ የምታደርገው የኢትዮጵያን መንግሥትን ነው።

ለአፍሪቃውያን ስደት ማሕበራዊ ጫና፣ የፊልም ኢንዱስትሪ  እና  አፍሪቃዉያን አውሮጳ ሆነው ሥለ አውሮጳ ገፅታ የሚያንፀባርቁት የተሳሳተ ምሥል ሌሎች እንደ  ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው። ኔዘርላንድስ ውስጥ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ አውሮፓ የመጣው ዋለልኝ አያሌው «እኛ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ሳንወጣ ስለ አውሮፓ ያለን ምስል የተሳሳተ ነው» ይላል። ሀገሩን ለቆ ሲጓዝ የመጀመሪያው ጊዜ ነው።  « ስለ አውሮፓ ሲወራ ያለው ስልጣኔ ነው። ኢትዮጵያ ያለው ወጣት ወደዚህ ሲመጣ እንደዚህ አንደሰለጠነው ማህበረሰብ የተመቸው ኑሮ የሚኖሩ ይመስላቸዋል። ነገር ግን እዚህ ያለው ሲስተም ጥብቅ ነው»

 

የአውሮፓ ህልማቸውን ግማሽ መንገድ ላይ ያቋረጡት አፍሪቃውያን 

 

ወደ አውሮፓ ለመሰደድ አፍሪቃውያን ከሊቢያ ሌላ እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሟት ሀገር ሞሮኮ ናት። ስደተኞቹ ሰሜን አፍሪቃዊቷ ሀገር እንደደረሱ ወደ ስፔን ለመግባት ሙከራ ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ አውሮፓ የመግባት ህልማቸውን ትተው እዛው ሞሮኮ ውስጥ ለመኖር  ይጥራሉ። የዶይቸ ቬለው ጋይ ሄይጄኮ ወደ ካዛብላንካ ገበያ ጎራ ብሎ ካነጋገራቸው አፍሪቃውያን አንዱ ሪቻልድ ዌኖንግ ይባላል። ካሜሮናዊ ነው።« በመጀመሪያ ሞሮኮ የመጣሁት ወደ አውሮፓ መጓዝ ስለፈለኩ ነው። ከዛም ያን ያህል ወሳኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ምክንያቱም የቴክኒክ ባለሞያ እንደመሆኔ እዚህም ልሰራቸው የምችላቸው ስራዎች አግኝቻለሁ። እና ራሴን እዚህ ለማዋሀድ ችያለሁ። ስለዚህ ወደ አውሮፓ መሄድ አያስፈልገኝም። »

ባለፉት አራት አመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ከሰሐራ በስተ ደቡብ ያሉ ሀገራት ዜጎች የሞሮኮ የመኖሪያ ፍቃድ አግኝተዋል። ሪቻልድ በአሁኑ ወቅት ፍቃዳቸውን ለማግኘት ከሚጠባበቁት 20 000 የሚጠጉ ስደተኞች አንዱ ነው። መሀመድ ምቦዮ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው የመጣው። ጋዜጠኛው ከአምስት ዓመት በፊት በፖለቲካ ምክንያት ክስ ሸሽቶ ነው ሞሮኮ የገባው። ዛሬ ሞሮኮ ውስጥ የራሱ የሬዲዮ ዝግጅት አለው።« በዲሞክራሲ እጦት እና ሀገሬ ባለው ግጭት ምክንያት ሀገሬን ጥዬ መሄድ ነበረብኝ።  ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አስቸጋሪ ስፍራ እንደሆነ ይታወቃል። ጋዜጠኛ ሆኜ በምሰራበት ወቅት ከመንግሥት አንዳንድ መስፈራራት ደርሶብኛል። እና ህይወቴን ለማዳን ስል ሀገሪቱን ጥዬ መሄድ ነበረብኝ።»

መሀመድ እንዲደራጅ ድጋፍ ያረገለት አማፕ የተባለ ትናንሽ ንግዶችን የሚያበረታታ ማህበር ነው። ማህበሩ ራሳቸውን ለሚያስተዳድሩ የምክር፣ የገንዘብ እና የስልጣና ድጋፍ ይሰጣል። ከዚህ ደግሞ አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች ከሰሀራ በስተ ደቡብ የመጡ ስደተኞች ናቸው። « አማፕ የገንዘብ ድጋፍ ነው ያደረገልኝ። ለጋዜጠኝነት ስራዬ አስፈላጊ የሆነውን መሳሪያ ኮምፒውተር ገዝቶልኛል። »

ከሞሮኮያዊያን ጋር ተወህዶ ለመኖር ፈረንሳይኛ መናገር ለሚችል ሰው ስራ የማግኘት እና የመኖር እድሉ የተሻለ ነው ይላል መሀመድ።  የአማፕ ማህበር ባልደረባ የሆኑት ሀሳን ኢሪፊ በርካታ ስደተኞች እንዴት አመለካከታቸውን ሞሮኮ ውስጥ ሊቀይሩ እንደቻሉ ያብራራሉ። « ነገሮች ተቀይረዋል። ስደተኞች ውጭ ሳይሆን ሀገራቸው እንዳሉ ይሰማቸዋል። ይህ ደግሞ ለስደተኞቹ ወይም ለተገን ጠያቂዎቹ የዚች ሀገር ፣ የባህሉ አካል እንደሆኑ ስሜት ፈጥሮላቸዋል። በዚህ ምክንያት ሞሮኮ መሸጋገሪያ ሀገር ብቻ ሳትሆን እንግዳ ተቀባይም ሀገር እየሆነች መጥታለች።»

በሺ የሚቆጠሩት ስደተኞችን ህጋዊ ለማድረግ ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ ይጠይቃል። በህዝቡ ዘንድስ ስደተኞቹ ምን ያህል ተቀባይነት አላቸው።« እኛ ሌሎች ሀገራት ፈረንሳይ እና አሜሪካ እንደሚያደርጉት ነው እያደረግን ያለነው። ስለዚህ አዲስ ነገር አይደለም። በስራቸው ጎበዝ ከሆኑ ለኢኮኖሚው እድገት በእርግጠኝነት አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።»ይላል ሞሮኮዋዊው የዩንቨርስቲ ተማሪ። የሞሮኮ ኢኮኖሚ ከበርካታ የአውሮፓ ሀገራት በበለጠ መልኩ በማደግ ላይ ይገኛል። ለኢኮኖሚውም እድገት ባለፉት አመታት ሞሮኮ ህይወታቸውን የመሰረቱ አፍሪቃውያን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ጋይ ሄይጄኮ/ ልደት አበበ

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች