ለአካባቢ ጥበቃ የወጣቶች ተሳትፎ | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ለአካባቢ ጥበቃ የወጣቶች ተሳትፎ

አሜሪካኖች « ምድራችንን ከቀዳሚ አባቶቻችን አልወረስናትም፤ ይልቁንም ከልጆቻችን ተበደርነዉ እንጂ፤» የሚል አባባል አላቸዉ። አባባሉ በሕይወት ዘመናችን ያለንባትን ምድር የተፈጥሮ አካባቢ በአግባቡና ለመጪዉ ትዉልድ እያሰብን ተጠቅመን እንድናልፍ ለማሳሰብ ያለመ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:06 ደቂቃ

ለአካባቢ ጥበቃ የወጣቶች ተሳትፎ

በየዓመቱ ግንቦት ወር ማለቂያ ላይ የተመድ ስለአካባቢ ተፈጥሮ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር ለማበረታታት የአካባቢ ተፈጥሮ ቀንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስባል። የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ መርሃግብር ለዚህ ዓመት ያነሳዉ መሪ ሃሳብ የሰዎች፤ የተፈጥሮና የኤኮኖሚ ደህንነት ምድራችን ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ መጠቀም ላይ ምን ያህል የተመረኮዘ እንደሆነ የሚያጠይቅ ነዉ። ድርጅቱ እንደሚለዉ የሰዉ ልጅ መሬት በዘላቂነት መለገስ ከምትችለዉ በላይ ተፈጥሮን እየበዘበዘ እየተጠቀመ እንደሚገኝ ይገልጻል። ለዚህም በመረጃነት አብዛኛዉ የመሬት ስነምህዳር በሰዎች ቁጥር መብዛትና በኤኮኖሚ ልማት ስም ዳግም ተመልሶ በማይገኝበት ደረጃ ለጉዳት መዳረጉንም ያመለክታል። ያለምንም ማስተካከያ ርምጃዎች በዚህ አያያዝ የሚዘልቅ ከሆነም በጎርጎሪሳዊዉ 2050ዓ,ም የዓለም ሕዝብ ቁጥር 9,6 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል፤ ለዚህ የሕዝብ ብዛት ተገቢዉን የተፈጥሮ ሃብት ለማግኘትም ሶስት ፕላኔቶች ሊያስፈልጉ እንደሚችሉ ከወዲሁ ያስጠነቅቃል። እናም የተሻለ የወደፊት እጣ ፈንታ እንዲኖረን ከተፈለገ የተፈጥሮ አካባቢን በአግባቡ መያዝና መጠቀም አማራጭ የሌለዉ መሆኑ ልብ እንዲባልም ይመክራል።

Weltumwelttag 2015 US Botschaft Addis Abeba

ስለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ከተወያዩት ተማሪዎች በከፊል

የዘንድሮዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ቀን በሌላዉ ዓለም እንደተደረገዉ ሁሉ ኢትዮጵያም ዉስጥ ታስቦ ነበር። ዕለቱ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ጤና ቀበናና ግንፍሌን እናፅዳ የተሰኘዉ ማኅበር እዚያ ከሚገኘዉ የአሜሪካን ኤምባሲ ጋ በመተባበር ያዘጋጀዉ በተለይ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ግንዛቤ የማስጨበጫ መድረክ ነበር። በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ተጋባዦች ተማሪዎቹ ለተፈጥሮ አካባቢ ትኩረት እንዲሰጡ ያነቃቁ ንግግሮችን ከማድረጋቸዉም ሌላ በርካታ ትምህርት ቤቶች በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያከናዉኗቸዉን ተግባራት በማሳየት ገጠሙን ያሏቸዉን ችግሮች በማመልከት የመፍትሄ ሃሳቦችን ከተሰብሳቢዎቹም ሆነ ከራሳቸዉ እንዲመነጭ መደረጉን የጤና ቀበና ሊቀመንበር ደሳለኝ ፍሬዉ ገልጾልናል።

ተማሪዎቹ በየትምህርት ቤታቸዉ ለተለያዩ መረጃዎች መለዋወጫ የሚጠቀሙበትን የሚኒ ሚኒዲያ መድረክ ለተፈጥሮ አካባቢ ግንዛቤ ማስጨበጫነት እንዴት ሊያዉሉት እንደሚችሉ ማብራሪያ ከሰጧቸዉ አንዱ በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ሙያ ከ10 ዓመታት በላይ እንደሠሩ የገለፁልን አቶ ደግሰዉ አማኑ ነበሩ።

Weltumwelttag 2015 US Botschaft Addis Abeba

የአረንጓዴ ምድር ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ አምለሰት ሙጬ በገለፃ ላይ

በዝግጅቱ ከተሳተፉት መካከል አረንጓዴ መሬት የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ያዘጋጀችዉ በፊልምና ትወና ሥራ ላይ እንደምትገኝ የገለችልን የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ባለቤት ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ አካባቢ ተፈጥሮ ላይ ስለለተደቀነዉ አሳሳቢ ችግር ካነጋገረቻቸዉ የዘርፉ ባለሙያዎች የበለጠ ግንዛቤ ማግኘቷን ትናገራለች። ከልጅነቷ ለተፈጥሮና ለአትክልቶች የነበራት ፍቅር እያደገ መሄዱን የምትናገረዉ የአረንጓዴ ምድር ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ፤ መሬት አረንጓዴ መሆን አለባት የሚል መልዕክት ያዘለዉን የእሷን ሥራ የተመለከቱ ወገኖች ተማሪዎች ቢመለከቱት አስተማሪነቱ ታምኖበት ቅዳሜ ዕለት በተካሄደዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ቀን መቅረቡን አጫዉታናለች። ለጥናታዊ ፊልሟም በዘርፉ እዉቀት ያላቸዉን፤ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሠሩና በግል ተነሳሽነትም አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሰዎችን አነጋግራለች። ይህን ዘጋቢ ፊልም ለማዘጋጀትም ወደተለያዩ አካባቢዎች መጓዝ ነበረባት። ያ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ አግኝታ እሷ የተረዳችዉን ለሌሎችም እንድታጋራ ኃይል ሆኗታል። ወ/ሮ አምለሰት የአካባቢ ተፈጥሮን ስለመጠበቅ ሲታሰብም በግልና በራስ አካባቢ እንደሚጀምር ነዉ የምታስገነዝበዉ። ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic