ለኖቤል የታጩት ተጠረጠሩ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 10.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ለኖቤል የታጩት ተጠረጠሩ

ባሕር ሲያቋርጡ ለመስመጥ የተጋለጡ ስደተኞች የድረሱልኝ ጥሪ ሲያደርጉላቸዉ፤ ለሚደርሱላቸዉ ነብስ አድኖች ያሳዉቃሉ።በሕይወት ተርፈዉ አዉሮጳ በተለይ ኢጣሊያ ለሚገቡ ስደተኞች ምግብ መጠለያ፤ ሰነድ-መኖሪያ እንዲያገኙ ይረዳሉ።ይሕ ሰብአዊ እርዳቸዉ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤል እንዲሸለሙ እስከመታጨት ደርሰዉ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:35 ደቂቃ

ለኖቤል የታጩት ወንጀለኛ በመርዳት ተጠረጠሩ

ኤጄንሲያ-ሐበሻ የተሰኘዉ ስደተኞችን የሚረዳ ድርጅት መሥራችና መሪ ካሕን አባ ሙሴ ዘርዓትይ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የሚያሸጋግሩ ሰዎችን ይረዳሉ የሚል ምርመራ እየተደረገባቸዉ ነዉ።ኤርትራዊዉ የካቶሊክ ቄስ እና ድርጅታቸዉ የሜድትራኒያንን ባሕርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት አደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን ከሞት በማትረፍና በመርዳት የታወቁ ናቸዉ።የደቡብ ኢጣሊያ ትራፓኒ ከተማ አቃቤ ሕግ በፃፈላቸዉ ደብዳቤ ግን ሕገ-ወጥ ስደተኛ አሸጋጋሪዎችን ይረዳሉ በሚል ጥርጣሬ እየተመረመሩ ነዉ።አባ ሙሴ ጥርጣሬዉን «ሐሰት» ብለዉታል። 

 

ጊዜዉ ራቅ ይበል እንጂ እሳቸዉም ስደተኛ ነበሩ።ገና ለአካለ መጠን ሳይደረስ፤ እናት አባት-ወይም ዘመድ ወዳጅ ሳያጅበዉ ብቻዉን ተጉዞ  ኢጣሊያ ገባ-አዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደዘገበዉ።ያኔ አስራ-ስድት አመቱ ነበር።ተማረ፤ ቀሰሱ (አንቱ ሆኑ)።ከዓፍሪቃ ወደ አዉሮጳ የሚፈልሰዉ ስደተኛ ቁጥር እያየለ፤ ስደተኛዉ የሚገጥመዉ ፈተና እየጠከረ ሲመጣ፤ የድሮዉ ስደተኛ አዲሶቹን ለመርዳት እንድ-ሁለት ይሉ ያዙ።

                             

በግልም በማሐበርም የሚሰጡት ርዳታ በነፃ ነዉ።ባሕር ሲያቋርጡ ለመስመጥ የተጋለጡ ስደተኞች የድረሱልኝ ጥሪ ሲያደርጉላቸዉ፤ ለሚደርሱላቸዉ ነብስ አድኖች ያሳዉቃሉ።በሕይወት ተርፈዉ አዉሮጳ በተለይ ኢጣሊያ ለሚገቡ ስደተኞች ምግብ መጠለያ፤ ሰነድ-መኖሪያ እንዲያገኙ ይረዳሉ።ይሕ ሰብአዊ እርዳቸዉ

የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤል እንዲሸለሙ እስከመታጨት ደርሰዉ ነበር።

ሰሞኑን በተቃራኒዉ አጭበርባሪ ደላሎችን ይረዳሉ ተብለዉ መጠርጠራቸዉ ለብዙዎች በርግጥ ከማስገረምም በላይ ነዉ።እሳቸዉ ግን የደነቃቸዉ አይመስልም።ምክንያቱን አላጡትምና።

                                    

በርግጥም ስደተኛ የሚገባበትን ቀዳዳ በሙሉ ለመድፈን የሚባትሉት የአዉሮጳ መንግስታት ስደተኛ የሚረዳዉን ሁሉ ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ ከየሥራዉ እያሰናከሉት ነዉ።የዚያዉ የትራፓኒ አቃቤ ሕግ አንድ የጀርመን የርዳታ ድርጅት ጀልባን አስሮ ድርጅቱን ከስሷል።ዩገንድ ሬተት የተባለዉ ድርጅት ጥፋቱ ልክ እንደ ኤርትራዊዉ ቄስ ሁሉ ስደተኞችን ከሞት ማትረፉ ነዉ።ስደተኞችን የሚረዱትን መክሰስ፤ መወንጀል መፍትሔ አይሆንም ባይም ናቸዉ።

                                  

ስደተኛዉ ከየአገሩ እንዳይወጣ መፍትሔዉ የፖለቲካ ነፃነትን ማስከበር፤ የጦርነት እና የረሐብ መንስኤዎችን ማቃለል እንደሆነ ያልተናገረ ፖለቲከኛ፤ ለጋሽ፤ ተንታኝም የለም።እስካሁን ግን የሰማ እንጂ ያደመጠ መኖሩ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

Audios and videos on the topic