ለንደን ማራቶን፥ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ፈይሳ ሊሌሳ | ዓለም | DW | 22.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ለንደን ማራቶን፥ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ፈይሳ ሊሌሳ

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ፈይሳ ሊሌሳ ነገ በለንደን ማራቶን ይፎካከራሉ። የ5,000 እና 10,000 ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰኖች ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ በማራቶን የግል ምርጥ ሰዓቱን ሊያሻሽል ማቀዱን ተናግሯል። ቀነኒሳ በኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ የተያዘውን የውድድሩን ክብረ-ወሰን የማሻሻል ዕቅድ እንዳለውም ገልጧል

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ፈይሳ ሊሌሳ ነገ በለንደን ማራቶን ይፎካከራሉ። የ5,000 እና 10,000 ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰኖች ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ በማራቶን የግል ምርጥ ሰዓቱን ሊያሻሽል ማቀዱን ተናግሯል። ቀነኒሳ በኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ የተያዘውን የውድድሩን ክብረ-ወሰን የማሻሻል ዕቅድ እንዳለውም ገልጧል። በሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ባለመሳተፉ ዛሬም ድረስ ንዴት እንደሚሰማው የተናገረው ቀነኒሳ በኦሎምፒክ መድረክ እጆቹን ከፍ አድርጎ በማጣመር የኢትዮጵያ መንግሥትን ተቃውሞ ለስደት የተዳረገው ፈይሳ ሊሌሳን ይገጥማል።

የ27 አመቱ ፈይሳ ከሪዮ ኦሎምፒክ በኋላ አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፉን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግሯል። «ለአምስት ወራት ከቤተሰቦቼ ተነጥዬ በአሜሪካ ቆይቻለሁ» ያለው ፈይሳ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ ሰዎች እየተገደሉ እና ለእስር እየተዳረጉ ነው ሲል ተናግሯል፤ በለንደን ማራቶንም መንግሥትን በመቃወም ምልክት እንደሚያሳይ ገልጧል። ቀነኒሳ እና ፈይሳ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና የመንግሥት ርምጃ ተቃራኒ ምላሾችን ከሰጡ በኋላ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል። ተስፋዬ አበራ፤ጥላሁን ረጋሳ፤ አሰፋ መንግስቱ በወንዶቹ ጎራ ከቀነኒሳ እና ፈይሳ ጋር ይፎካከራሉ።

ጥሩነሽ ዲባባ፤ አሰለፈች መርጊያ፤ ማሬ ዲባባ፤ አበሩ ከበደ እና ትዕግስት ቱፋ በሴት አትሌቶች ጎራ የሚወዳደሩ ኢትዮጵያውያት ናቸው። የኤርትራ ተወላጆቹ ግራማይ ገብረሥላሴ እና አማኑኤል መሰል እንዲሁም ኬንያውያኑ አቤል ኪሩይ እና ዳንኤል ዋንጂሩም ተፎካካሪዎች ናቸው። በሴቶች ዘርፍ በሪዮ ኦሎምፒክ በ400 ሜትር ከተወዳደረች በኋላ ለስደት የተዳረገችው ሶማሊያዊቷ ዘምዘም መሐመድ ፋራሕ በለንደን ማራቶን ትፎካከራለች።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ