ለናዚ ሰለባዎች የቆመው ድርጅት እምነት ማጉደሉ፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ለናዚ ሰለባዎች የቆመው ድርጅት እምነት ማጉደሉ፣

የዩናይትድ እስቴትስ ባለሥልጣናት፣ የናዚዎች ሰለባዎች ለሆኑ ሰዎች ካሣ ይሆን ዘንድ የተከፈገንዘብን አጭበርብረዋል ሲሉ 17 ሰዎችን መክሰሳቸውን የአሜሪካ የወንጀል ተከታታይ መሥሪያ ቤት (FBI) ከትናንት በስቲያ አስታውቋል።

default

ከናዚዎች ጭፍጨፋ የተረፉ ይሁዲዎች፣ ያለቁትን ወገኖቻቸውን በሚያስታውሱበት ስብሰባ ላይ፣

FBI እንዳለው፣ አጭበርባሪው ቡድን፣ ከምሥራቅና ማዕከላዊ አውሮፓ፣ ተሰደው አሜሪካ የገቡ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎችን መልምሎ፣ አትራፊ ላለሆነው ካሣ ጠያቂ ጉባዔ ማመልከቻ እንዲያስገቡ አድርጎአል። ይኸው ካሣ ጠያቂ ጉባዔ የጀርመን መንግሥት የሰጠውን ገንዘብ ለናዚ ሰለባዎች የሚያከፋፍል ነው። የዶቸ ቨለ ቴሌቭዥን አገልግሎት ባልደረባ፣ ፍሎሪያን ኤካርት ያሰናዳውን አጭር ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

በናዚዎች የህዝብ ማጎሪያ ጣቢያ ፣ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባቸው ፣ ብዙ ፍዳ ተቀብለው ከጭፍጨፋ የተረፉ ይሁዲዎች፣ እጎ አ በ 1951 ዓ ም በተመሠረተው፣ ካሣ ጠያቂ ማኅበር በኩል ለመጦሪያም ቢሆን ከተመደበ ገንዘብ ክፍያ እንዲያገኙ ሁኔታዎች ቢመቻቹም፣ የዚሁ ማኅበር አባላት ገንዘቡን በአግባቡ እናዳላዋሉት ተደርሶበታል። የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ግሬግ ሽናይደር---

«አሳፋሪ ነው፣ አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው። እንዴት አንድ ከዚህ የካሳ ገንዘብ ይሠርቃል!?--ግን፣እንዲህ ዓይነት ማጭበርበር ከቶውንም እንደዋዛ አይታለፍም ። የተሠራውን አውቀነዋል። መዝግበነዋል። እናም ለወንጀል መርማሪው መ/ቤት (FBI) አቅርብነዋል። መርምረናል። ስለሆነም በማጭበርበር ማመልከቻ የቀረበበትን እያንዳንዱን ሰነድ ፈልገን እናገኘዋለን። »

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ባከተመ በ 6 ኛው ዓመት (እ ጎ አ በ 1951 ዓ ም፣ )የተመሠረተው የካሣ ጠያቂ ማኅበር የተሰኘው ድርጅት፣ እጅግ አሳፋሪ ስም የሚያጎድፍ ሁኔታ ነው አሁን ያጋጠመው። በቀረበው የክስ ሰነድ ላይ፣ አጥፊዎች ናቸlwe የተባሉት የማኅበሩ ሠራተኞች፣ በጋዜጦች እርዳታ ማስታወቂያ በማውጣት የግል ሰነዶችን ለማፋለስ ሞክረዋል። በአመዛኙ የዚህ የማጭበርበር ተግባር መሣሪያ የሆኑት ከምሥራቅ አውሮፓ ፈልሰው የሠፈሩ አይሁድ ናቸው።

ፕሪት ባራራ የተባሉት የህግ ጠበቃ እንዲህ ይላሉ።

«የእርዳታ ጥያቄም ሆነ ማመልካቻ እንዲያስገቡ ተወትውተው ይህን የፈጸሙ አብዛኞቹ ከሩሲያ ተሰደው የሠፈሩ የአይሁድ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው። የመታወቂያ ሰነዶቻቸውን ግልባጭ ፤ ማለት የልደት የምሥክር ወረቀትና ፓስፖርት እንዲያቀርቡ ተጠይቀው፣ ለዚህ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር በተያያዘ፣ ከተመደበ ካሣ፣ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ነው ቃል የተገባላቸው። »

በማጭበርበር የተከሰሱት ሰዎች ፣ በተሳሳተ ማመልከቻ በመጠቀም፤ ከ 30 ሚሊዮን ዩውሮ በላይ ለግላቸው እንዳካበቱ ተደርሶበታል። በተለይ ጀርመን የከፈለችው የካሣ ገንዘብ፣ በአንዲህ ዓይነት የማጭበርበር ተግባር እንደባከነ ታውቋል። እ ጎ አ በ 2000 እና 2009 ዓ ም ብቻ፤ በማጭበርበር የቀረቡ 4,957 ማመልከቻዎች ተቀባይነት ማግኘት እንደቻሉ ተደርሶበታል። በማጭበርበር የተከሰሱት ሰዎች ፣ ቢያንስ የ 20 ዓመታ እሥራት ሳይበየንባቸው እንደማይቀር ነው የተነገረው።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ