ለትራኮማ ተጠቂዎች የደረገ ቀዶ ህክምና | ጤና እና አካባቢ | DW | 29.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ለትራኮማ ተጠቂዎች የደረገ ቀዶ ህክምና

ባለፈው ዓመት ከዚህ አለም በሞት በተለዩት ካርል ሄንዝ በም የተቋቋመው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ለ1862 በትራኮማ ለተጠቁ ሰዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማቅረቡን አስታወቀ። ድርጅቱ ትራኮማን ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።


ትራኮማ (የዓይን ማዝ) Chlamydia Tracomatis እየተባለ በሚጠራ በሽታ አምጪ ተኅዋሲ ሳቢያ የሚከሰትና ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ነው፡፡ በቀላል ንኪኪ፣ በዝንቦች፣ ፎጣና ከአይን ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በመዋዋስ መጠቀም እና ተኅዋሲው በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል።፡፡ በሽታው በአብዛኛው ከድህነት ጋር የሚያያዝና በቂ ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች በስፋት የሚታይ ነው፡፡ የትራኮማ (የዓይን ማዝ) በሽታን በቀላሉ መከላከልና በሽታው ከተከሰተም በኋላ በቀላል ህክምና ማዳን የሚቻል ቢሆንም ይህንን ባለማድረግ ብቻ እጅግ በርካቶች ለአይነ-ስውርነት አደጋ እንደሚጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዶክተር አስናቀ ወርቁ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የፕሮግራም ማስተባበሪያ ሃላፊ ናቸው።


''እ.ኤ.አ. በ2006 በተካሄደ ጥናት በኢትዮጵያ የትራኮማ መጠን 41.3 በመቶ ነው።አማራ፤ኦሮሚያና በደቡብ ክልል የሚገኙ አካባቢዎች በሽታው በስፋት ተንሰራፍቶ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ናቸው።''
እንደ ዶክተር ዶክተር አስናቀ ወርቁ ኢትዮጵያ በዓለም በሽታው በስፋት ከሚገኝባቸው ሃገሮች መካከል ትመደባለች።በዓለም ጤና ድርጅት መሰረት ትራኮማ በኢትዮጵያ ለአይነ-ስውርነት መንስኤ በመሆን በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህንን ህመም ለመከላከል ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል በአለም የጤና ድርጅት የተቀየሰና ትራኮማን ለመከላከልና ለማከም ያስችላል የተባለው ሴፍ ስትራቴጂ ይጠቀሳል።የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ደግሞ ይህን መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ከሚተገብሩት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆኑን ዶክተር አስናቀ ወርቁ ይናገራሉ።

S - Surgery- በዓይን ለይ የተፈጠረን ጠባሳ በቀላል የቀዶ ህክምና ዘዴ በማስወገድና በማስተካከል
A - Antibiotics - ችግሩ ላጋጠማቸው ወይንም ለችግሩ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ለሚኖሩ ሰዎች መድኃኒቶችን በመስጠት በሽታው የሚያስከትለውን ጥፋት በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ፤
F - Facial Cleaning - በቂ ውሃና የንፅህና መጠበቂያ እንዲኖር በማድረግ፣ዜጎች በተለይም ህጻናት ፊታቸውን እንዲታጠቡ ማስተማርና ተግባራዊነቱን ማመቻቸት
E- Environmental improvement - የአካባቢን ንፅህናና የመጸዳጃ ቤት መጠቀምን ማበረታት ናቸው።የሰዎች ለሰዎች ድርጅት አራቱን መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ ትራኮማን ለመከላከል ይሰራል።
ግንቦት 21/2006 ዓ.ም. ከዚህ አለም በሞት በተለዩት ካርል ሄንዝ በም የተቋቋመው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፈው አመት ብቻ ለ1862 የትራኮማ ተጠቂዎች ቀዶ ህክምና በመስጠት የአይን ብርሃናቸውን መልሷል።ከ50 000 በላይ ሰዎች ደግሞ ሰዎች ለሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዓይን ቀዶ ህክምና አገልግሎት አግኝተዋል። የንጹህ መጠጥ ውሃ፤ትምህርት፤ጤና ግብርናና መሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ለማሳደግ የሚሰራው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የጸረ-ትራኮማ ዘመቻውን ከሌሎች ስራዎች ጋር በማቀናጀት እንደሚቀጥልበት ዶክተር አስናቀ ወርቁ ይናገራሉ።
''ትልቁ ፈተና የባህሪ ለውጥ የማምጣት ጉዳይ ነው።ሰዎች ህጻናት በተለይ ደግሞ ፊታቸውን በቀን ሁለት ጊዜ መታጠብ እንዳለባቸው ማስተማር ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ዝም ብሎ በደረቁ ፊታችሁን ታጠቡ ብቻ ሳይሆን ውሃ ለማቅረብም እንሞክራለን።ሽንትቤት እንዲጠቀሙ አካባቢያቸውን እንዲያጸዱ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ እስከ አቅርቦት ድረስ ሰፊ ስራ እየሰራን ነው ያለንው።''

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic