ለተመላሽ ስደተኞች የሚሰጥ ርዳታ   | አፍሪቃ | DW | 28.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ለተመላሽ ስደተኞች የሚሰጥ ርዳታ  

ፍልሰትንና የፍልሰተኞች ጉዳይ ፖለቲካን በተመለከተ የጀርመናዉያኑና የአዉሮጳ ኅብረት መርህ «የስደተኝነት ምንጩን መዋጋት» ይላል። በዚህ አባባል አታካች ሆኖ የሚሰማዉን የስደተኞች እና ተገን ጥያቄዎችን ጉዳይ ቀለል ማድረግ የተፈለገ ይመስላል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14

ለተመላሽ ስደተኞች ርዳታ  

የእዚህ ፖለቲካ እዉነታ ግን ስደተኞች በፈቃዳቸዉ ወደ መጡበት እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ መርዳት ነዉ። ግን በርግጥ ይህ ይሆን ይሆን? ኦዛይኒ ዴጄቦ የአነስተኛዉን የህክምና ጣብያ በር አንኳክቶ ገባ። አንዲት የጤና ረዳት አንድ እጁ ላይ ጉዳት የደረሰበትን ሰዉ ርዳታ እየሰጠች ነበር። በዚህ የሕክምና ጣብያ በሰዉነታቸዉ ላይ አደጋ የደረሰባቸዉ እንዲሁም በአዕምሮ ህመም የሚሰቃዩ ሰዎችን  ማየቱ የተለመደ መሆኑን የአጋዴ  የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ተጠሪ ኦዛይኒ ዴጄቦ ይናገራል።  አብዛኞቹ ወደ አጋዴዝ የሚመጡት ከሊቢያ የሚመጡ ስደተኞች ናቸዉ። በሊቢያ ሁኔታዉ እጅግ አስከፊ መሆኑንም ይናገራሉ።   «አስከፊነዉ፤ እጅግ አስከፊ ነዉ። ስደተኞቹ በሆነ የግለሰብ አልያም በመንግሥት እስር ቤቶች ነዉ ተይዘዉ የሚቆዩት። ታድያ እነዚህ ሰዎች ከተያዙበት ለማምለጥ የቻሉ ጊዜ ወደዚህ ነዉ የሚመጡት። አብዛኞቹ በጥይት የቆሰሉ እንዲሁም የአይምሮ መረበሽ ያለባቸዉ ናቸዉ»

በዚህ የስደተኞች መጠለያ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ወደመጡበት ወደ ሃገራቸዉ መመለስን ይሻሉ። ለዚህ ምክንያቱ ከአጋዴዝ የትም መሄድ ስለማይችሉ፤  በሊቢያ ሳሉ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ስለተፈጸመባቸዉ ነዉ። አልያም በአልጀርያ ሳሉ ሲተገብሩት የነበረዉን ሥራ በማጣታቸዉና አሁን በጃቸዉ ላይ ምንም ገንዘብ ስለሌለ ነዉ። 

ለምሳሌ የ 39 ዓመቱ ላይቤሪያዊ ሞሲስ ወደእዚህ የመጣዉ ከነዚህ በአንዱ ምክንያት ነዉ። የሞሲስ የስደት ሕይወት ተሞክሮ ከብዙዎች ጋር ተመሳሳይ ነዉ። ሞሲስ በሃገሩ በላይቤሪያ ስራ ባለማግኘቱ ነበር እንደምንም  ገንዘብ አዘራቅሞ  ወደ ሊቢያ የተጓዘዉ። በሊቢያም ስራ እየሰራ ገንዘብ ለቤተሰቦቹ ወደ ላይቤርያ ይልክ ነበር።  ግን ቀስ እያለ ስራ ቀጣሪዉ ለስደተኞች ደሞወዝ መክፈሉን አቆመ። አንድ ቀን አለ ሞሲስ በምሰራበት ቦታ ፖሊስ ይዞ ወደ ኒጀር ጠረፍ ወሰደኝ፤ ከዝያ የስደት ኑሮይ ተቋረጠ። 

«እዚህ ለመድረስ ከ 1000 ዶላር ከፍያለሁ ። በእጄ ላይ አሁን ምንም ገንዘብ የለም። የምበላዉ ነገር  እንኳ አጥቼ ነበር። መንገድ ላይ ስልኬን ሳይቀር ያለኝን ነገር ሁሉ ወስደዉብኛል።» ከዝያም ሞሲስ አጋዴዝ ስለሚገኘዉ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መጠለያ ጉዳይ ሰምቶ በመጠለያዉ ጣብያ ኑሮዉን ጀምሮአል። በሕይወቱ አዲስ ምዕራፍን ለመጀመር ተስፋን ሰንቆቀአል።

በኒጀር መዲና ኒያሚ ላይ የሚገኘዉ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM)ዋና ተጠሪ ጉስፔ ሉፕሪት  በጎርጎረሳዊ 2016 ዓ,ም   በርካታ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸዉ እንዲመለሱ ረድተናል ሲሉ ገልፀዋል።  « 2016 ዓ,ም በራሳቸዉ ፍላጎት ወደ ሃገራቸዉ ለሚመለሱ ከ 5000 ለሚበልጡ ሰዎች ርዳታ ሰጥተናል። ይህ ቁጥር ከ 2015 ዓምቱ ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ ይበልጣል።»

ሉፕሪት መስርያ ቤታቸዉ ወደ ሃገራቸዉ መመለስ የፈለጉ ስደተኞችን በሃገራቸዉ መቋቋም እንዲችሉ ርዳታዉን ለመስጠት እንደሞከረ ተናግረዋል።  ይህ የገንዘብ ርዳታ እስካሁን አንዳንድ ጉዳዮችን ለመደጎም ብቻ መብቃቱን የተናገሩት ዋና ተጠሪዋ በአሁኑ ወቅት አዲስ ስምምነት እንዳለ ገልፀዋል።

«ከአዉሮጳ ኅብረት ጋር አንድ አዲስ የፊናንስ ዉል ላይ ደርሰናል። በመሆኑም በዉሉ  መሠረት በ 14 ሃገራት ስራዉን ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን የሚል ተስፋ አለን። ይህ ማለት ደግሞ ስደተኞቹ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ። አሁን እኛ ማድረግ ያለብን ስደተኞቹ ከተሰደዱባቸዉ ሃገራት የሚታየዉን አኗኗርና ሕይወት ለማስተካከል መስራት ነዉ። »

በዉሉ መሠረት በ 14 ሃገራት መረሃ-ግብሩን ለማስፈፀም 100 ሚሊዮን ይሮ የተመደበ ሲሆን መረሃግብሩ በተለይ   በቅድምያ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመልክቶአል። በዚህ መረሃ ግብር (IOM)እና አጋር የርዳታ ድርጅቶች ስደተኞች በሃገራቸዉ በመጡበት ከተማ አልያም በአነስተኛ የገጠር መንደር የትምህርት፤ የንግድ ስራን ለመክፈት ብሎም አነስተኛ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶችን ለማቋቋም የሚረዳ ድጋፍ እንደሚደረግላቸዉ ተገልጾአል።  

እዚህ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳዉ ነገር ለስደት ያልወጡትና ስራ አጥተዉ በሃገራቸዉ የተቀመጡ ወጣቶች የዚህ ርዳታ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ከስደት የተመለሱት ይህን ርዳታ ማግኘታቸዉ ነዉ። ጉስፔ ሉፕሪት ፤ « እኛ እንዲህ አይነቱ ወሪ እንዲኖር አንፈልግም። ከሃገር ተሰደህ ስኬት ባለማግኘትህ ሃገርህ ለመመለስ ርዳታ ነዉ የምታገኘዉ። የርዳታዉ ዓላማ፤ ለአራት ለአምስት ሆነዉ ተሰደዉ የነበሩትን በአንድ ላይ  ለመርዳት ነዉ» 

በአጋዴዝ እንደሚገኘዉ የ «IOM» ማዕከል ሁሉ ኒያሚ በሚገኘዉ «IOM» ማዕከልም ወደ ሃገራቸዉ መመለስ የሚሹ አልያም መመለስ ያለባቸዉ በርካታ ስደተኞች ይገኛሉ። ከስምንት ወር በፊት ከጋምቢያ የተሰደደዉ ወጣት ባካሪ ማኔ፤ ለጉዞዉ የሚሆነዉን ገንዘብ አሰባስበዉ የሰጡት ቤተሰቦቹ ናቸዉ። ባካሪ ማኔ በስደት መንገድ ላይ ሳለ ገንዘቡን በመጨረሱ ቤተሰቦቹ ስደቱ ተሳክቶለት ሰርቶ ይከፍለናል በሚል ተስፋ በሃብትነት የያዙትንይዘዉት የነበረዉን መሪት ሸጠዉ ልከዉለታል። ባካሪ በዚህ ገንዘብ ከሃገሩ ከጋምቢያ ተነስቶ ሊቢያ ድረስ ብቻ ነበር መድረስ የቻለዉ።

 ባካሪ ማኔ አሁን በ «IOM» ርዳታ ወደ ሃገሩ ሊመለስ ዝግጅት ላይ ነዉ። እስካሁን ስለደረሰዉ ሁኔታ በሃዘን እንዲህ ይገልጻል። «ሁልጊዜ የማስበዉ ቤተሰቦቼ እንዴት እንደሚሰቃዩ ነበር። እነሱን ደስተኛ ለማድረግም ለስደት የበቃሁት። ግን እንደፍላጎቴ አልተሳካልኝም። ያ ደግሞ እኔን በጣም በጣም ጎድቶኛል። ቤተሰቦቼን ለመርዳት ቢያንስ አሁን እዚህ ኒጀር ዉስጥ ስራ ባገኝ ጥሩ ነበር። ግን አሁን ወደ ሃገሪና ወደ ቤተሰቦቼ መመለሱ በጣም ፍርሃት አሳድሮብኛል።»    

የባካሪ ማኔ እንደተሸናፊ ወደ ሃገሩ ለመመለስ መዘጋጀቱ በፍርሃት አሸማዎታል። «IOM»  በሃገሩ በጋምቢያ ይርዳዉ አያርዳዉ ግን በርግጥ የሚያዉቀዉ ነገር የለም። የድርጅቱ ሠራተኞችም ምንም የነገሩት ነገር የለም። ባካሪ ይህን ቃለ ምልልስ ሲያደርግ የ «IOM» ቃል አቀባይ ሞኒካ ኬሪክ ይከታተሉ  ነበር ፤ ነገሩ ይላሉ።

«ይህ አንደ ግለሰብ ሁኔታ ይለያያል። በርግጥ ርዳታዉ በቅድምያ ሴቶች ሕጻናት አልያም ደግሞ በራሳቸዉ መንቀሳቀስ የማይችሉ ርዳታ የሚያስፈልጋቸዉን  ሰዎች ያካትታል። በዚህ ዓመት በሚከናወነዉ የመልሶ ማቋቋምያ መርሃ-ግብር 20 ጥቃቅን ፕሮጀክቶችን እንጀምራለን። በዚህም ለምሳሌ በግብርና በርካታ ሰዎችን እንረዳለን። ከነዚህ መካከል 50 የሚሆኑ  ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ»

በመረሃ ግብሩ ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰዉ መቋቋም የሚችሉት ሰዎች ስንት መሆናቸዉ አጠያያቂ ነዉ። በጎርጎረሳዊ 2016 ዓ,ም ብቻ በአማካኝ 420 ሺህ ስደተኞች ወደ ሊቢያና አልጀርያ ተሰደዋል። «እዚህ ለመድረስ ከ 1000 ዶላር ከፍያለሁ ። በእጄ ላይ አሁን ምንም አይነት ገንዘብ የለም። የምመገበዉ እንኳ አጥቼ ነበር። በመንገድ ላይ ያለኝን ነገር ሁሉ ስልኬን ሳይቀር ዘርፈዉኛል»

 

የንስ ቦርሸርስ / አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic