ለሶማሊያ ነዳጅ የጉቦ ቅሌት | አፍሪቃ | DW | 05.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ለሶማሊያ ነዳጅ የጉቦ ቅሌት

ሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ ኩባንያ ለሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናትን ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ፈጽሟል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሰ። ኩባንያው በአቅም ግንባታ ስም ለሶማሊያ መንግስት ፔትሮሊየምና ማዕድን ሀብት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች በሚያደርገው ክፍያ ተፎካካሪ እንዳይኖረው ከማድረግ ባሻገር ተጨማሪ ይዞታዎች ለመውሰድ እየሞከረ ነው ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:20
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:20 ደቂቃ

ለሶማሊያ ነዳጅ የጉቦ ቅሌት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ የተሰኘዉ ኩባንያ ለሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት በመቶ ሺዎች ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሳይከፍል አልቀረም።በዓለም አቀፉ ድርጅት የሶማልያእናየኤርትራተቆጣጣሪቡድንመርማሪዎች ለፀጥታጥበቃውምክርቤትየማዕቀብኮሚቴአባላት ባቀረቡትክስ የኩባንያው ክፍያ የሶማልያ የመንግስት ተቋማትን በሙስና የሚያዳክም ነው ብለዋል።

ሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ ኩባንያ የሶማልያ ፔትሮሊየምና ማዕድን ሀብት ሚኒስቴርን አቅም ለማጎልበት በሚል ሰበብ ከአምና ጀምሮ ለሶማሊያ ባለሥልጣናትና ባለስልጣናቱን ላግባባዉ ጠበቃ በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ መክፈሉን የመርማሪዎቹ ዘገባ ያትታል። ለሚኒስቴሩ ባለሙያዎች ተከፈለ የተባለው ገንዘብ በተግባር ኩባንያው ሐቻምና ከሶማሊያ ከመንግስት ጋር የተፈራረመው የነዳጅዘይትፍለጋስምምነትእንደተጠበቀእንዲያቆይለትና ተጨማሪ የፍለጋ ስምምነት ለማግኘት ያደረገው ነው ሲል መርማሪ ቡድኑ ወንጅሏል።

በታላቋ ብሪታኒያ በስልጣን ላይ በሚገኘው የወግ አጥባቂ ፓርቲ የቀድሞ መሪ ሎርድ ማይክል ሀዋርድ የሚመራው ሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ የነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማራው በሶማሊያ ብቻ ነው። በቻተም ሃውስ የሶማሊያ ፖለቲካ ተንታኝ አህመድ ሱሌይማን የኩባንያው ድርጊት የሶማሊያ ተቋማትን ጥያቄ ውስጥ የከተተ እንደሆነ ይናገራሉ።

«በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለጸጥታው ምክር ቤት የማዕቀብ ተመልካች ኮሚቴ ሰኞ እለት የቀረበው የ28 ገጽ ዘገባ የሶማ ድርጊት የሶማሊያ የመንግስት ተቋማትን በሙስና የሚያዳክም እንደሆነ ያትታል። ጉዳዩ በታላቋ ብሪታኒያ የአሳሳቢ የማጭበርበር ጉዳዮችን በሚመለከው ቢሮም እየተመረመረ የሚገኝ ነው። ምርመራው ወደ 700 ሺህ ዶላር የሚደርስ አጠራጣሪ ክፍያ መፈጸሙንና 500 ሺህ ዶላር ለሶማሊያ የፔትሮሊየምና ማዕድናት ሃብት ሚኒስቴር ባለፈው አንድ አመት ለአቅም ግንባታ በሚል መከፈሉን ይህም የመንግስት ባለስልጣናትን ለመደለል የተደረገ ሳይሆን አይቀርም በማለት ይወነጅላል።»

ብሪታኒያ አሳሳቢ የማጭበርበር ጉዳዮች ቢሮ (Serious Fraud Office)በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቆ ከሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ ኩባንያ ጋር ያለውን ግንኙነት ከመግለጽ ተቆጥቧል። የኩባንያው የለንደን ቢሮ ግን ባለፈው ሳምንት ብርበራ እንደተካሄደበት ሬውተርስ ዘግቧል።

ሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ ኩባንያም ይሁን የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት የሙስና ውንጀላውን አስተባብለዋል። ይሁንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪዎች ለጸጥታው ምክር ቤት የማዕቀብ ኮሚቴ ያቀረቡት ዘገባ የኩባንያውን ቅሌት የከፋ አድርጎታል። እንደ ዘገባው ከሆነ የሶማሊያ የነዳጅ ሀብትን ብቻ ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመው ኩባንያ የመደለያ ክፍያ የፈጸመው ለመንግስት ባለስልጣናት ብቻ አይደለም። የሶማሊያ መንግስትን በነዳጅ ዘይት ላይ የሚያማክረውና መንግስትን ወክሎ የሚደራደረው ጄ. ጄይ. ፓርክ (J. Jay Park) የተሰኘ የካናዳ የጥብቅና ተቋም ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሶማ ኦይል ኤንድ ጋዝ ተከፍሎታል። አህመድ ሱሌይማን ሁነቱን « ይህ ግልጽ የጥቅም ግጭት ነው። ኩባንያው የሶማሊያ የፔትሮሊየም ሚኒስቴር ሃላፊዎችንና የጠበቆችን ክፍያ መክፈል አይገባውም ነበር።»ሲሉ ይገልጹታል።

ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣሪዎች የሶማሊያ ፔትሮሊየምና ማዕድን ሀብት ሚኒስቴርን የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችን በመቅጠር አቅም ለማጎልበት በሚል የተከፈለው ገንዘብ የኩባንያውን ጥቅም ለማስጠበቅ የተደረገ ሳይሆን አይቀርም። ኩባንያው ከሶማሊያ መንግስት ጋር በገባው ውል መሰረት ተጨማሪ ጥቅሞችን ያለተወዳዳሪ የማግኘት እድልም እንዳለው አህመድ ሱሌይማን ይናገራሉ።

«ሶማ ኦይልና ጋዝ ኩባንያ ከ ጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ እንዲሰማራ ፈቃድ አለው።ይህ የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ወደ ስራ በመግባት የመጀመሪያው ኩባንያ ያደርገዋል። ለአሰሳ ስራው ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቷል። ለመንግስትም የነዳጅ ይዞታዎቹ የሚገኙበትን ቦታዎች የሚጠቁም የመረጃ ቋት እየገነባ መሆኑን አስታውቋል። አስቸጋሪው ነገር ኩባንያው ከሶማሊያ መንግስት ጋር የፈጠረው የጠበቀ ወዳጅነት ነው። በዚህም ኩባንያው በባህር ዳር በሚገኙ አስራ ሁለት የነዳጅ ጉድጓዶች የመጫረት መብት ተሰጥቶታል። እናም በዚህ አመት መጨረሻ የማምረትና ክፍፍል ፈቃድ ለመፈራረም በዝግጅት ላይ ነው። »

ሶማሊያ ያላት ቅምጥ ነዳጅ ሃብት ይዞታ በግልጽ ባይታወቅም የመስኩ ባለሙያዎች የሳዑዲ አረቢያን ግማሽ ወይም 110 ቢሊዮን በርሜል እንደሚደርስ ይገምታሉ።

የብሪታንያዉ ኩባንያ ከሶማሊያ ባለሥልጣናት ጋር ገብቷል የተባለው ህገ-ወጥ ስምምነት በሁለት እግሩ ለመቆም ለሚንገዳገው የሞቃዲሾ መንግስት ሌላ ፈተና ከመሆኑ ባሻገር እንደ ሶማሌ ላንድና ፑንት ላንድ ከመሳሰሉ ግዛቶች ጋር ያልተቋጨ ጉዳይ በመኖሩ የርስ በርስ ግጭት ሊፈጥር እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን አስታውቋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic