1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሰላም ጥሪ የተደረገ ሠልፍ በሀዋሳ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 3 2014

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች «ሰላም ለኢትዮጵያ» በሚል መሪ ቃል ዛሬ ሰላማዊ ሠልፍ አካሄዱ። ሰልፎ እንደከዚህ ቀደም ሰልፎች ፉከራ ሳይሆን የሰላም መልዕክቶች ላይ ያተኮሩ መፈክሮችን ተሰምተውበታል። የሰላም ምልክት የሆነ ነጭ ሰንደቅን የማውለብለብ ሥነ ሥረዓትም ተከናውኗል።

https://p.dw.com/p/4GajR
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«ጦርነቱ በሰላማዊ መፍትሄ ይቁም»

  
ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል ። « ሰላም ለኢትዮጵያ» በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ሰልፍ ላይ በሰላም በጎነት ላይ ያተኮሩ መፈክሮች ተስተጋብተዋል፣ የሠላም ምልክት የሆነ ነጭ ባንዲራ የማውለብለብ ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል። ዶቼ ቬሌ DW ያነጋገራቸው የሠልፉ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ አሁን ያለው ጦርነት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። ሰላም ለአገራችን ያስፈልጋል ብዬ ነው ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ የወጣሁት ያሉት ያዕቆብ ፀጋዬ  የተባሉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ «ተቃራርነው የወጡ ሀይሎች በሙሉ ወደ ድርድር በመምጣት ልዩነቶቻቸውን ተነጋግረው እንዲፈቱ ምኞቴ ነው » ብለዋል።በሠልፉ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለሠልፈኞቹ ባሰሙት ንግግር  በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት መንግሥትና ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውን ገልጸዋል። 
ይህ ጦርነት የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል፤ ዕድገታችንንም ወደ ኋላ ጎትቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ‹‹ጦርነቱ የሕዝቦቻችንን ሰላም እያደፈረሰ ይገኛል። መንግሥታችንና ሕዝባችን ጁንታውን ( የትግራይ ሀይሎችን ማለታቸው ነው ) ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የክፋት ቡድን ሃይ ከማለት ይልቅ ሲያበረታታ ታይቷል። ስለዚህ ሰላማችንን ለመበጥበጥ የሚነሱ ሀይሎችን ሁሉ  ወደ ድርድርና ሰላም እንዲመጡ እንጠይቃለን። ለዚህ ዛሬም ነገም በራችን ክፍት ነው። ከዚህ አልፈው የሚሄዱ ከሆነ ግን ሰላማችንን ለመጠበቅ የሚቃጣብንን ትንኮሳ እንመክታለን» ብለዋል። 
በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ሀይሎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ድርድር ከመከነ ወዲህ በከተማው ይኽን መሠሉ ሠልፍ ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። በዛሬው ሰላማዊ ሠልፍ እንደከዚህ በፊቶቹ ከቀረርቶና ሽለላ ይልቅ የሰላም አስፈላጊነት ጎልቶ የተንፀባረቀበት ሆኖ ተስተውሏል።

Äthiopien | Friedensdemonstration in Hawassa
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ