ለመርከቦች ከባህር ላይ ወንበዴዎች ከለላ ሰጪ ኩባንያዎች | ኢትዮጵያ | DW | 15.08.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ለመርከቦች ከባህር ላይ ወንበዴዎች ከለላ ሰጪ ኩባንያዎች

ከጥቂት ቀናት በፊት የጀርመናውያኑ ሀንሳ ስታቫንገር የተባለችው የንግድ መርከብ ከአራት ወራት እገታ በኋላ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚልዮን ዩሮ ቤዛ፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሌላዋ ቢክቶርያ የተባለችው መርከብ አንድ ነጥብ ሶስት ሚልዮን ዩሮ ቤዛ ተከፍሎ ከእገታ ሊላቀቁ በቅተዋል።

default

የመርከቦቹ ባለቤት ኩባንያዎች ከመጀመሪያው መርከቦቻቸው በአደገኛው የሶማልያ ባህር በሚያደርጉት ጉዞዋቸው ላይ አስፈላጊውን ከለላ የሚያገኙበትን ሁኔታ ቢያመቻቹ የመርከቦቻቸው ሰራተኞች ለንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ሰለባ ባልሆኑ ነበር፡ ይህን ያህል ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያም ማድረግም አያስፈልጋቸውም ነበር።

ይህንን የሚሉት መርከቦችን በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተበራከተ ከመጣው የባህር ላይ ወንበዴዎች ጥቃት የመከላከሉን አገልግሎት የሚሰጡ እና ለዚሁ አገልግሎታቸውም ብዙ ገንዘብ የሚያስከፍሉት የግል ጸጥታ ጥበቃ ተቋማት እና ዓለም ቀፍ የመድን ድርጅቶች ናቸው። ሶማልያውያኑ የባህር ላይ ወንበዴዎች ካለፈው የካቲት ወር ወዲህ በኤደን የባህር ሰላጤ አንድ መቶ ሰላሳ መርከቦችን ያጠቁ ሲሆን፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመርከቦች ላይ የተጣለው የባህር ላይ ወንበዴዎች ጥቃት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በእጥፍ ጨምሮዋል።
የጸጥታ ጥበቃ አገልግሎት ከሚሰጡት ተቋማት መካከል አንዱ ሀርት ሴኪውሪቲ ካምፓኒ ሲሆን፡

Hansa Stavanger nach ihrer Freilassung

በአየር፡ በየብስና በባህር ከለላ ይሰጣል። በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚታገቱት መርከቦች ቁጥር እየጨመረ ከሄደ ወዲህ ይኸው መንበሩ በእስያዊቱ ሀገር ሲንጋፖር የሚገኘው ኩባንያ በየመን መዲና ሰንዓ አንድ ጽህፈት ቤት ከፍቶ መንቀሳቀስ ጀምሮዋል። ለአደገኛውን የጸጥታ ጥበቃ ስራቸው አስፈላጊውን የጦር መሳሪያ የታጠቁት ሰራተኞቹም የባህር ላይ ወንበዴዎች ሰለባ የመሆን ስጋት ከተጠናከረበት ከስዌዝ ቦይ እስከ ፋርስ ባህረ ሰላጤ ድረስ የሚጓጓዙ መርከቦችን የማጀብ ስራ ያከናውናሉ፡ ይህንኑ ስራቸውን እንዴት እንደሚያካሂዱም የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ማርክ ፒሄማ ሲያስረዱ፡
« የተቋሙ ሰራተኞች ወደ ፖርት ሰይድ በመሄድ ከለላ ለሚያስፈልጋት መርከብ ከስዌዝ ቦይ ጀምረው በቀይ ባህር በኩል አድርገው እስከ ኤደን ባህረ ሰላጤ ድረስ አጀበው ይጓዛሉ። የመጀመሪያው የሰራተኞች ቡድን ለምሳሌ፡ የባህር ላይ ወንበዴዎች በቀላሉ ወደ መርከቢቱ እንዳይገቡ ለማከላከል መጀመሪያ የመርከቢቱን መግቢያ በሮችን ቦታ ይቀያይራሉ። ከዚያ ልክ የየመን የባህር ክልል እንደደረሱ መርከቢቱን እስከ ኦማን ድንበር አጅቦ የሚያደርሰው ዋነኛው ከጥቃት ተከላካዩ ቡድን ስራውን ይረከባል። »
እንደ መርከቢቱ ፍጥነት ከሜድትሬንየን ባህር እስከ ፋርስ ባህረ ሰላጤ ጉዞ እስከ ስድስት ቀን ሊፈጅ ይችላል። ለዚሁ አገልግሎት የመርከቦቹ ባለንብረቶች ምን ያህል ገንዘብ እንደሚከፍሉም ሆነ ደምበኞቻቸው እነማን እንደሆኑ ማርክ ፒሄማ ለመግለጽ አልፈለጉም። ለታወቀው ትልቁ የብሪታንያውያኑ የመድን ድርጅት ሎይድ የሚሰሩት ፖል አጋተም ቢሆኑ፡ ልክ እንደ ፒሄማ አንዳችም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም። ይሁን እንጂ፡ ለመድን ዋስትና የሚከፈለው ገንዘብ ባለፉት ዓመታት ከፍ ማለቱን ፖል አጋተ አረጋግጠዋል።
« በኤደን የባህረ ሰላጤ የባህር ላይ ውንብድና መካሄድ ከጀመረ ወዲህ በዚሁ የባህር መስመር ለሚጓዙ የንግድ ጭነት መርከቦች የሚከፈለው የመድን ዋስትና ተወዶዋል። ክፍያው በአስር እስከ አስራ አምስት እጥፍ ጨምሮዋል። »
አንዲት በባህር ላይ ወንበዴዎች ቁጥጥር ስር የምትውል መርከብን በነጻ የማስለቀቁ ተግባር አንድን የመድን ዋስትና ድርጅት ከሶስት እስከ አራት ሚልዮን ዶላር ሊያስወጣው ይችላል። ይህ ለአጋቾቹ የሚከፈለውን ቤዛ እና ጉዳት ለደረሰበት በመርከቢቱ ለተጫነው ዕቃ ካሳን ያጠቃልላል። ይህም ቢሆን ግን እስከዛሬ በዚሁ ክፍያ የተነሳ አንድም ድርጅት ክስረት አልደረሰበትም፤ ምክንያቱም፡ ፖል አጋተ እንዳስረዱት፡ ድርጅቶቹ ይህንኑ በማሰብ ሂሳባቸውን ደምበኛቻቸውን በሚያስከፍሉት ገንዘብ ያጣጣሉና።
« በአንድ ቀን ውስጥ በኤደን ባህረ ሰላጤ አንድ መቶ መርከቦች ቢተላለፋና ከነዚህም አንድዋ ልትታገት የምትችልበት ሁኔታ ከመቶ አንድ ብቻ ነው። እና አሁን ከሚያስከፍሉት ዋጋ ጋር ሲያስቡት ጥሩ ገቢ ሊያገኙ ይችላሉ። »
ሎይድ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ሁለት አዳዲስ የዋስትና አሰጣጥ ስምምነቶችን ለደምበኞቹ አቅርቦዋል። የመጀመሪያው ከሀንስ ሴኪውሪቲ ካምፓኒ ጋር ያደረገው ስምምነት ነው። በዚህ ተቋም የጸጥታ ጥበቃ ሰራተኞች አገልግሎት ለምትጠቀም መርከብ ቅናሽ ያደርጋል። ሁለተኛው ዕገታን የሚመለከተው ፓኬት ነው። አንዲት መርከብ በሶማልያውያኑ የባህር ላይ ወንበዴዎች ከታገተች፡ የመድን ዋስትና ሰጪው ድርጅት ወዲያውኑ ያኔ የመርከቢቱን ባለቤት ተቋም የሚደግፍና ከአጋቾቹ ጋር ተቋሙን በመወከል የሚደራደር አንድ ቡድን ስራውን ይጀምራል። ለአጋቾቹ የሚከፈለውና ከጊዜው ጋር ተስማሚ የሆነው ቤዛም በዚሁ አገልግሎት ውስጥ ተጠቃሎዋል። ይኸው የመድን ድርጅት አሰራር ከሶማልያውያን ዘንድ ሂስ ተሰንዝሮበታል። የሶማልያ የአሳ ሀብት ሚንስትር አብዱራህማን ኢብራሂም ስለመድን ድርጅቱ ጥሩ አመለካከት የለውም።
« እነርሱ ናቸው የባህር ላይ ወንበዴዎቹን የሚያበረታቱት። የትኛውም የትኛውም የግል የመድን ድርጅት ችግሩን ለማስወገድ ቃል ሲገባ ይሰማል። ግን የባህር ላይ ወንበዴዎች ከጠፉ እነዚህ ድርጅቶች ምን ሊሰሩ ነው? ከሁሉም የባሱት የመድን ድርጅቶቹ ናቸው። የሚፈልጉት ክፍያቸውን ማሳደግ ብቻ ነው። በሶማልያ የባህር ክልል የሚተላለፉ ሁሉ ተጨማሪ ገንዘብ መክፈል አለባቸው። ይህ እነርሱን የሚጠቅም ነውና። »
የአውሮጳ ህብረት የጀመረውን ጸረ የባህር ላይ ውንብድና ተልዕኮ ዓላማን ሚንስትሩ መልካም ሲሉ ቢያሞግሱም፡ የቀረጥ ከፋዩን ገንዘብ ማባከን አድርገው ተመልክተውታል። ምክንያቱም ችግሩን በባህር ላይ የጸጥታ ጥበቃ ማድረእግ ብቻውን ችግሩን አያስወግደውም፡ እንደ ሚንስትሩ አባባል።
« የባህር ላይ ወንበዴዎችን ለማጥፋት ከተፈለገ ሁነኛው መንገድ የሶማልያን የሽግግር መንግስት መደገፍ ነው። የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ከባህሩ ሳይሆን ከመሬት የመጡ ናቸውና፤ ወደ ባህሩ ከመኬዱ በፊት የባህር ላይ ውንብድናን የችግሩ መንስዔ ባለበት ግዛት መተገሉ ይበጃል።
ሚንስትሩ ኢብራሂም በአውሮጳ ህብረት፡ በግል ተቋማቱና በሀገራቸው መካከል ትብብር እንዲኖር ይሻሉ። የውጭ ሀገር ዜጎቹ ስነ ቴክኒኩን እንዲሰጡ ይፈልጋሉ፡ ሶማልያዎያኑ ደግሞ የጸጥታ ኃይላትን ሊያቀርቡ ይችላሉ፥ ሆኖም በወቅቱ ይህ ዓይነቱ የመእፍትሄ ሀሳብ በወቅቱ ቦታ ያለው አይመስልም። በዚህ ፈንታ እኛ አፍሪቃውያኑን ስለምናውቃቸው ለችግሩ መፍትሄ እናስገኛለን የሚል መፈክር የያዘ አንድ የደቡብ አፍሪቃውያኑ ድርጅት በዚሁ የስራ መስክ ተሰማርቶዋል።

ኤስተር ሳውብ/አርያም ተክሌ/ሸዋዬ ለገሠ