ለሁለተኛ ቀን የዘለቀው የኦሮሚያ አድማ | ኢትዮጵያ | DW | 24.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ለሁለተኛ ቀን የዘለቀው የኦሮሚያ አድማ

የኦሮሚያ አድማ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል። አድማው ግብይት ገትቷል፤ሱቆች አዘግቷል፤የመጓጓዣ አገልግሎትም አስተጓጉሏል። ታዛቢዎች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ያልተመለሱ ጥያቄዎች አድማውን ወልዷል ሲሉ ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:00 ደቂቃ

ያልተመለሱት ጥያቄዎች እና የኦሮሚያ አድማ

መላው ኦሮሚያን ያዳረሰው የአምናው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በጪሊሞ ጫካ ጦስ ነበር። ዘንድሮም ከትናንት ጀምሮ ለአምስት ቀናት የተጠራው አድማ በጪሊሞ ጫካ አቅራቢያ ያሉ ከተሞችን አዳርሷል። አድማው ሽው ካለባቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን ከጊንጪ ከተማ አጠገብ የምትገኘው ጋሊሴ አንዷ ነች። አንድ የከተማዋ ነዋሪ እንደሚሉት ዘወትር ረቡዕ በከተማይቱ የሚካሔደው ገበያ ትናንት አልቆመም።

"መኪና አይንቀሳቀስም። ሱቅ እንዳለ ዝግ ነው። ካርድ እንኳ የሚገዛበት ቦታ የለም። ሕዝቡ ከቤት አይወጣም። ጸጥታ ኃይሎች በግዳጅ በር እንዲከፈት፤መኪና እንዲሔድ ህዝቡን እያስገደዱ ነው። ሕዝቡ ደግሞ ቄሮ የሚባል የኦሮሞ ልጆች ለዚህ መፍትሔ ሊፈልግ የወጡትን ፈርቷል። ጸጥታ ኃይሎች ደግሞ እነሱን ማግኘት አልቻሉም።" የሚሉት የጋሊሴ ነዋሪ ሱቆች መታሸጋቸውንም ተናግረዋል።

የገቢ ግብር፤በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች አያያዝ እና የድንበር ማካለልን በመቃወም በተጠራው እና ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የሥራ አድማ የተጫነው ትንሿን ጋሊሴ እና ጎረቤቷን ጊንጪን ብቻ አይደለም። ግብይት የተስተጓጎለባቸው፤የመጓጓዣ አገልግሎቶችም የተቋረጡባቸው ከተሞች ብዙ ናቸው።

በዋትአፕ ትዝብታቸውን ያደረሱን አንድ የአይን እማኝ  "እኛ ባለንበት አከባቢ ማለትም ከሆለታ እስከ አሽዋ ሜዳ እንቅስቃሴ የለም።" ይላሉ። የአይን እማኙ እንደሚሉት "ሱቆች ተዘግተዋል። ትራንስፖርት የለም። በቃ ሁሉም ዝግትግት ነው ያለው። ሱቅ እከፍታለሁ ያለ ቤንዚል ተርከፍክፎ ከእሳት እንደመጫወት ይቆጠራል።"

ሌላ ስማቸውን ያልገለጡልን የክልሉ ነዋሪ  "በወሊሶና በአካባቢው ዛሬ ጠዋት የተጀመረው አድማ ብዙም ሳይቆይ ወደ ነበረበት ተመልሶ ገበያው ቆሞ ነበር።ከወሊሶ ወጣ ብላ በምትገኘው በዲለላ ግን ጠንከር ያለ ነበር። አንድ የመንግስት እና አንድ የህዝብ ማመላለሻ መኪናዎች ተሰባብረዋል።" የሚል መልዕክት አድርሰውናል።

አድማው የክልሉን አጎራባች ከተሞችም የተጫነ ይመስላል። "ወደ ድሬደዋ ከክፍለ ሐገር የሚመጡ ተሽከርካሪዎች መስታወታቸው እየተሰበረ አይተናል።" ይላሉ ሌላ የዶይቼ ቬለ ተከታታይ-"የአትክልት እና ጫት ዋጋው ቢጨምርም እንደልብ አይገኝም። ረቡዕ እና ሐሙስ ድሬደዋ ፀጥ ረጭ ብላለች።" ሲሉ ያክላሉ። 

የሥራ ማቆም አድማው አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮችን አያያዝ የሚቃወም ይሁን እንጂ ፓርቲው አልጠራውም። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ እንደሚሉት ጥያቄዎቹ ግን ቀድሞ ፓርቲያቸው ያነሳቸው ናቸው።

ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአዳማ ከተማ ነዋሪ አሁን የስራ ማቆም አድማውን ከፊት ሆኖ የሚመራው ወጣት ክልሉን በሚያስተዳድረው ፓርቲም ይሁን በፌዴራላዊው መንግሥት ቆርጧል ሲሉ ይናገራሉ። ወጣቱ ለመቃወም መነሻ ነው የሚፈልገው የሚሉት ታዛቢ አገሪቱ ወዴት እየሔደች እንደሆነ አይታወቅም ባይ ናቸው።

"ወጣቱ በአገሪቱ መንግሥትም አካባቢውን በሚያስተዳድረው ድርጅትም ተስፋ ቆርጧል። ሕዝቡን የሚሰማው አካል የለም። የሚያደራድር አካል የለም። የሚጠይቅ አካል የለም። ሕዝቡም ደግሞ ጠይቆ አቅቶታል። ምክንያቱም የጠየቀው ጠባብ ነው የሚባለው። እስር ቤት ነው የሚገባው። መንገላታት ነው፤ ስድብ ነው፤ ንቀት ነው። ወጣቱ የሚፈልገው መነሻ ምክንያት ነው።"

አቶ ሙላቱ ገመቹም ሕዝብ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ አለማግኘቱ ለሌላ ተቃውሞ መነሻ መሆኑን ይስማማሉ። መንግሥት በ"ጥልቅ ተሐድሶ" እና የካቢኔ ለውጥ መፍትሔ አበጃለሁ ቢልም ጥያቄዎቹ እንደነበሩ ናቸው የሚሉት አቶ ሙላቱ አሁንም መፍትሔው በመንግሥት እጅ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

"ሕዝብን የሚያነሳሳው ሕዝብ ሰላማዊ ትግል የሚያካሒደው፤ልዩነትን የሚያመጣው ጥያቄን ያለመፍታት ነው። ባለፈው ሕዝብ ጥያቄ በሚጠይቅበት ጊዜ መንግሥት ጥልቅ ተሐድሶ አካሒጄ መልሶቹን እሰጣችኋለሁ {አለ} ። ያ ጥልቅ ተሐድሶ ተካሔደ ካቢኔዎች ተለወጡ ጥያቄዎቹ እንደነበሩ ናቸው።"

የትንሿ ጋሊሴ ከተማ ነዋሪ የሥራ ማቆም አድማው ወዴት እየሔደ እንደሆነ "አልታወቀም" ባይ ናቸው። ሁነኛው አማራጭ ግን ቁጭ ብሎ መነጋገር መሆኑን አላጡትም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች