1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሆሮ ጉዱሩ ግድያው ቀጥሏል ተባለ

ዓርብ፣ መስከረም 13 2015

ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ የወረዳ ከተማ ውስጥ መንግሥት «ኦነግ ሸኔ» የሚላቸው እና እራሳቸውን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ዛሬም ጥቃት ማድረሳቸውን የዐይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4HG53
Äthiopien | Straßenszene in Mendi
ምስል Negassa Deslagen/DW

በአጎራባች ወረዳዎችም የተኩስ ድምፅ ይሰማል

ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ የወረዳ ከተማ ውስጥ መንግሥት «ኦነግ ሸኔ» የሚላቸው እና እራሳቸውን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ዛሬም ጥቃት ማድረሳቸውን የዐይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናገሩ።  በአጎራባች ወረዳዎች በተለይም ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ድረስ ዛሬም የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በአካባቢው ውጥረት እንደሰፈነ እና ግድያውም መቀጠሉን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ገልጠዋል። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ስለጥቃቱ እና የነዋሪዎች ስጋት ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የፀጥታ እና አስተዳደር እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም። 

ዛሬ ለዶይቸ ቬለ ከኪረሙ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪ የሟቾች ቁጥር ዐሥራ አምስት መድረሱን ተናግረዋል። በጥቃቱ ስለተገደሉ እና ስለቆሰሉ ሰዎች ብዛት ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት አልተቻለም። ትናንት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የወረዳዋ ነዋሪ እንዳሉት ታጣቂዎቹ የወረዳዋን ከተማ በመቆጣጠር ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽመዋል። ሰላማዊ ዜጎችን የማፈናቀል ጥቃቱንም የከፈቱት ማለዳ ከ12፡00 ሰዓት ጀምሮ ነው ብለዋል። የዐይን እማኙ ትናንት ከሰዓት እንደገለጹት በታጣቂዎች እና በአከባቢው ሚሊሻዎች መካከል የሚደረግ የተኩስ ልውውጥ ከጠዋት ጀምሮ ቀጥሎ ነበር። በአከባቢው ውጥረት ዛሬም እንደ ነገሠ ነው። 

የዐይን እማኙ የ“ሸኔ” ታጣቂዎች በጃርደጋ ጃርቴ ከተማ 01 ቀበሌ ትናንt ማለዳ ከፍተዋል ባሉት ጥቃት ቤቶች ማውደማቸውንና የ15 ዓመት ልጅ ሕይወት ጭምር አልፏል ብለዋል። ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው ቁስለኞችን እንኳ ወደ ተሻለ ህክምና ለመውሰድ የመንገድ ላይ የፀጥታ ስጋት እንቅፋት እንደሆነባቸው አመልከተዋል። ጥቃት እና ሥጋቱ ዛሬም እንዳልተቀረፈ፤ በአካባቢው የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠም ለመረዳት ተችሏል። 

ሥዩም ጌቱ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ