ህገ ወጥ ስደተኞችና የጅብላልተሩ መቆጣጣሪያ መሳሪያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 30.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ህገ ወጥ ስደተኞችና የጅብላልተሩ መቆጣጣሪያ መሳሪያ

የዕንቅስቃሴ መከታተያ መሳሪያ ህገ ወጥ ስደተኞችን መከላከያ መፍትሄ ይሆን ?

አፍሪቃውያን ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በካናሬ ደሴቶች

አፍሪቃውያን ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በካናሬ ደሴቶች

ስፔይንና ሞሮኮን መሀከል የሚገኘው የጅብላልተር ወሽመጥ እስካለፉት ጥቂት ዓመታት ድረስ ከአፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ አፍሪቃውያን መሸጋገሪያ ነበር ። በዚህ በኩል አውሮፓና አፍሪቃ አስራ አራት ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚራራቁት ። በዚህ የተነሳም በርካታ አፍሪቃውያን በጅብላልተር አድርገው ወደ አውሮፓ ሲጎርፉ ኖረዋል ። በአሁኑ ሰዓት ግን በዚህ ወሽመጥ በኩል ለዘመናት ሲካሄድ የቆየውን የአፍሪቃውያን ፍልሰት ለማስቀረት በስፍራው አንድ እጅግ የተራቀቀ የኤሌክትሮኒክስ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ተተክሏል ። የመሳሪያውን ወጪ የሸፈነው የአውሮፓ ህብረት ነው ። ይኽው መሳሪያ በብዙ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘውን የካናሪ ደሴቶችንም በመጠኑም ቢሆን ይቆጣጠራል ። በአሁኑ ሰዓት አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ ካናሪ ደሴቶች መሻገርን ነው የሚመርጡት ። ታዲያ ይህ የዕንቅስቃሴ መከታተያ መሳሪያ ህገ ወጥ ስደተኞችን መከላከያ ተዐምራዊ መፍትሄ ይሆን ? ወደ ስፋራው የተጓዘው የዶይቼ ቬለው ስቴፈን ላይድል ያቀረበው ዘገባ ሁኔታ በመጠኑ ያስቃኘናል ።
አትሞ.......................................................
ናይጀሪያዊትዋ አውጉስቲና ከባለቤትዋ ጋር ወደ አውሮፓ ለመሻገር ስትነሳ ድርስ ርጉዝ ነበረች ።እስከ ሞሮኮ ድረስ በመኪና ነበር የተጓዙት ከዚያም ወደ ስፔይኖቹ የካናሪ ደሴቶች የሄዱት በጀልባ ነበር ። በመንገድ ላይም ጀልባቸው ሲገለበጥ በአንድ ሞሮኮአዊ አሳ አጥማጅ ዕርዳታ ነው ህይወታቸው የተረፈው ። ከዚያም እነ አውጉስቲና በስፔይን ፖሊስ እጅ ወደቁ ። ባልዋ ወደ ሀገሩ ሲባረር እርስዋ ወደ ደቡብ ስፔይን ተወሰደች ። ወንድም ኢዚዶሮ እንደ አውጉስቲና ያሉ እርጉዝ ስደተኞችን ወደ ደቡባዊ ስፓኝ እንዲገቡ ይረዳሉ ። ኢዚዶሮ እንደሚሉት ፖሊስ እርጉዝ ሴቶችን ምን መድረግ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ወደኔ ያመጡዋቸዋል እስከሁን ቁጥራቸው ሀያ ደርሷል ይላሉ ። አፍሪቃውያንን ወደ ስፔይን የሚያጓጓዙት ጀልባዎች በስፓኝ ቋንቋ ፓቴራ ነው የሚባሉት ። አውጉስቲና እንደምትለው እነዚህ ጀልባዎች ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ናቸው ።
«ፓቴራ የተባሉት ጀልባዎች ጥሩ አይደሉም ። በጀልባዋ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይሞታሉ ። ባለቤቴ በዚህ ጀልባ እንዲመጣ አልፈልግም ። »
አውጉስቲና ባልዋ እንዲመጣላት ትፈልጋለች ። ነገር ግን እርስዋ በተሳካላት መንገድ ባልዋ ከአሁን በኃላ ስፔይን መግባት መቻሉ አጠራጣሪ ነው ። በጅብላልተር ወሽመጥ በኩል ወደ ስፔይን የሚገቡ ህገ ወጥ ስደተኞች ቁጥር አሁን ቀንሷል ። ምክንያቱን ኢዚዶሮ እንዲህ ያስረዳሉ ።
«ከቀን ወደ ቀን ሁኔታው በድንገት እየተቀየረ ነው ። በወሽመጡ አድርጎ የሚመጣ የለም ። የዚህ ምክንያቱም የፀጥታ ኃይሎች የተከሉት አዲሱ ቴክኖሎጂ ውጤት ነው ። በዚህ ብቻ አይደለም በካናሪ ደሴቶች በኩል የሚመጡትም ጥቂት ናቸው ።»
ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር አንስቶ እስከ ሰኔ ባለው የስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ አስራ ስምንት ሺህ የሚጠጉ ህገ ወጥ ስደተኞች በጀልባዎች ስፓኝ ገብተዋል ። ሁሉም ማለት ይቻላል በካናሪ ደሴቶች በኩል አድርገው ነው ወደ ዚህች አገር የተሻገሩት ። ከዘንድሮ ታህሳስ አንስቶ እስካሁን ግን ወደ ስፔይን የሚመጣው ስደተኛ ቁጥር ቀንሷል ። ከስምንት ሺህ የሚያንስ ስደተኛ ነው በዚህ ጊዜ ውስጥ ስፔይን የገባው ። አሁን ማንም በጅብላልተር ወሽመጥ በኩል አይመጣም ማለት ይቻላል ። ቀደም ባሉት ዓመታት ግን ከልክ በላይ የሆነ የአፍሪቃ ስደተኛው ነበር በወሽመጡ አድርጎ ወደ አውሮፓ የሚጎርፈው ። በሁለት ሺህ ብቻ አስራ ሶስት ሺህ ስደተኛ ነው በዚህ በኩል ያቋረጠው ። አሁን ግን በጅብላልተር የተተከለው የኤሌክትሮኒክስ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ለህገ ወጥ ስደተኞች መከላከያ ጥሩ መድኃኒት ተደርጎ ነው የተወሰደው ። የስፓኝ መንግስት በአውሮፓ ህበረት ዕርዳታ እአአ ከሁለት ሺህ ሁለት አንስቶ ነው መሳሪያውን ለመስራት ጥረት ማድረግ የጀመረው ። ከሶስት መቶ ሚሊዮን ዩሮ በላይ በፈጀው በዚህ የኤሌክትሮኒክስ መቆጣጠሪያ መሳሪያ አማካይነት በአንድ ሺህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚካሄድ ዕንቅስቃሴን መከታተል ይችላል ። በዚህ መሳሪያ ላይ ካሜራ የተገጠመ ሲሆን ባለ ቀለም ምስልም ያሳያል ።
ሳልቫዶር ጎሜዝ የመቆጣጠሪያው መሳሪያ የሚገኝበት መስሪያ ቤት ባልደረባ ናቸው ።
« የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያው ማናቸውንም በእውሀ ላይ የሚዋኙ ነገሮችን አቅርቦ ያሳያል ። ከአንድ ሜትር ያነሰ ርዝመት ያላቸውንም ጭምር ። ዛሬ ጠዋት ከወሽመጡ መሀከል ሁለት ወጣቶችን አግኝተን አውጥተናል ። ወጣቶቹ የተሳፈሩት ከየትኛውም ቦታ ሊገዛ በሚችል በትንሽ ጀልባ ነበር ። »
በኤሌክቶኒኩ መሳሪያ ከሚካሄደው ክትትል በተጨማሪ በፈጣን ጀልባዎችና በመርከቦች የፀጥታ ኃይሎችም በንቃት ጥበቃ ያካሂዳሉ ። የቁጥጥር ዘዴው ህገ ወጥ ስደተኞችን ብቻ ሳይሆን የአደንዛዥ ዕጽ ንግድንም ለመቆጣጠር እየረዳ ነው ። በምህፃሩ ሲቨ የሚባለው አዲሱ መሳሪያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ ስደተኞችን በውሀ ከመበላት በማዳን ረገድም ትልቅ ሚና ይጫወታል ። ሆኖም አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አሁን ስራ ላይ የዋለው የመቆጣጠሪያ ስርዓት ህይወት ለማዳን አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም ነው የሚሉት ። ወይዘሮ ባርባራ
«ሲቨ እጅግ ብዙ ገንዘብነው የፈጀው ። ወደ ሶስት መቶ ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ። አሁን ስደተኞቹ ሌላ መንገድ እየተጠቀሙ ነው ። ሌላ ረዥም መንገድ ። የአሁኑ ጉዞአቸው ደግሞ አደገኛ ነው የሚሆነው ። ሲቨ የጥፋት መንገድ ነው ። ይህ ብቃት ያለው ፖሊሲ አይደለም ። ይህ ገዳይ ፖለቲካ ነው ። »
ሲቨ አሁንም ማወዛገቡን እንደቀጠለ ነው ። ለአንዳንድ የዕርዳታ ሰራተኖች ደግሞየመቆጣጠሪያው መሳሪያ መተከል በበጎ ተግባር ነው የተወሰደው ። ማኑዌል ፌሊክስ የቀይ መስቀል ድርጅት ባልደረባ ናቸው ። ሲቨ ህይወት እያዳነ ነው ይላሉ ።
«ሲቨ ህይወት ያድናል ማለት ይቻላል ። ምክንያቱም መሳሪያው ጀልባዎችን ከርቀት በማየት ችግር ላይ ከሆኑም ሊደረስላቸው ይችላል ።ከዚህ ቀደም ግን ከመሞት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም ። እንደ አለመታደል ሆኖ ወሽመጧ የሰዎች መቃብር ናት ። »