ህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር በዛምቢያ | አፍሪቃ | DW | 30.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር በዛምቢያ

ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ከአገር ወደአገር የማዘዋወር ተግባር ዓለም ዓቀፍ ችግር ነዉ። ዘመናዊ ባርነት በሚል የሚታወቀዉ ይህ ወንጀል በተለይ ሴቶችንና ሕጻናትን ለጉልበትና ወሲብ ብዝበዛ ማጋለጡ እየታየ ነዉ። ዛምቢያ ወንጀሉ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በዓመት ከአንድ መቶ በላይ ይመዘገባል።

የደቡብ አፍሪቃዋ ማዕከላዊ አገር ዛምቢያ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰዎች በህገወጥ መንገድ የማሸጋገሩ ንግድ የጦፈባት መሆኗ ነዉ የሚነገረዉ። ዛምቢያ ከሰባት የአፍሪቃ ሃገሮች ማለትም ናሚቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ቦትስዋና፣ ማላዊ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ አንጎላ እና ሞዛምቢክ ትጎራበታለች። አገሪቱ ሴቶችም ሆኑ ልጆች ወንዶችም ጭምር ለጉልበት እና ለወሲብ ብዝበዛ ይቀርቡባታል፤ ወደሌላ ይሸጋገሩባታል፤ ወደእዚያዉም ለዚሁ ተግባር ይሄዱባታል። አብዛኛዉ ሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉር በድንበር አካባቢዎች የሚከናወን ሲሆን በአብዛኛዉ በቤት ሠራተኝነት፣ ወይም በሌሎች የእርሻ፣ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አለያም በግንባታ ዘርፎች በግዳጅ ሥራዎች ጉልበታቸዉ የሚበዘበዝ ሴቶችና ሕጻናት ናቸዉ። የዛምቢያ የሰዎች ሕገወጥ ዝዉዉር ሰለባዎች ደቡብ አፍሪቃ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፤ እንዲሁም ናሚቢያ ይገኛሉ። ታዳጊዎቹ የዛምቢያ ወንዶችም ለወሲብ ንግድ ይወሰዳሉ።

እንዲያም ሆኖ ዛምቢያ በመጠኑም ቢሆን ከማላዊና ሞዛምቢክ ስደተኞች የሚመጡባትና ለጉልበት ሥራ የወሲብ ንግድ የሚሠማሩባት አገር ናት። አና ላኒ የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት IOM የፕሮግራም ኃላፊ ናቸዉ፤ ድርጅቱ ከሚያከናዉናቸዉ ሌሎች ተግባራት በተጨማሪ ሕገወጥ የሰዎችን ዝዉዉር ለመግታት ይንቀሳቀሳል፤
«ምልመላዉና፣ ማጓጓዙ አብዛኛዉን ጊዜ ማታለል ወይም ማስገደድን ጨምሮ አንድን ሰዉ በመዉሰድ ለብዝበዛ የሚጋለጥበት ሁኔታ ዉስጥ ለመክተት የሚደረግ ነዉ። ከዛምቢያ ጋ በተገናኘ በሕገወጥ ሰዎችን ማሸጋገርና ብዝበዛን ስንመለከት አብዛኛዉን ጊዜ ለጉልበት ብዝበዛ ለምሳሌ ለቤት ዉስጥ ሥራ።»

ከኬፕታዉን ደቡብ አፍሪቃ በቀረበላት የማታለያ የሥራ እድል የተማረከችዉ የ23ዓመቷ ዛምቢያዊት ኒና ቻንዳ በዚህ ዉስጥ አልፋለች። አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃቱ፤ እንዲሁም የግዳጅ ሥራዉ ካጎሳቆላቸዉ የሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ሰለባ አንዷ ናት።
«አጎቴ ኬፕታዉን ዉስጥ ሥራ እንደማገኝ ቃል ገባልኝ፤ እዚያ ስደርስ ግን አላግባብ ለአንድ ዓመት ያህል ያለ ደመወዝ እንድሠራ አደረገኝ፤ እረፍት የሚባል ነገር የለም፤ ጓደኛዬ ለፖሊስ እንዳመለክት ረዳችኝ፤ አሁን አገሬ ገብቻለሁ፤ ህይወቴ በመትረፉ እድለኛ ነኝ።»
ሚምቦ ዚየላ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ መንግስታዊ ያልሆነዉ ለሴቶች መብት የሚሟገተዉ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ድርጅት አስተባባሪ ናቸዉ። የወንጀሉ ከፍ እያለ መሄድ ያሳስባቸዋል፤
«ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ማሸጋገር ጾታን መሠረት ካደረጉ ጥቃቶች ጎን ለጎን የምንታገለዉ ጉዳይ ነዉ፤ ይህም ቢሆን ራሱ ብዙ ያልተነገረለት ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሆኑ እሙን ነዉ፤ እኛ አገር ደግሞ ችግርነቱ ከዕለት ወደዕለት እየባሰበት በመሄድ ላይ ነዉ።»


መንግስታዊ የሆነዉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የመብት ጥሰቶችን በቅርበት ይከታተላል። የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሳሙኤል ካሳንካ እንደሚሉት ኅብረተሰቡ ስለሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ምንነት እንዲረዳ ለማስቻል በቂ ሥራ ተሰርቷል ብለዉ አያምኑም።
«ኮሚሽኑ ገና አሁን ነዉ ጉዳዩ በሚመለከታቸዉ ወገኖች ሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉርን በሚመለከት ሚናዉ ምን እንደሆነ ሲጠየቅ ነዉ ሁኔታዉን ለማስተዋል የተገደደዉ። በመሠረቱ በማሳወቂያ ሂደቱ ያደረግነዉ ምንድነዉ፤ ህዝቡ ሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉር መኖሩን እንዲያዉቅ ለማድረግ ነዉ የሞከርነዉ።»
መንግስት ሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉርን ለማስቆም የሚረዳ ጠንካራ ሕግ እንደሌለዉ ያመለከቱት የተቃዉሞ ፖለቲከኛና የምክር ቤት አባል የሆኑት ቪክቶሪያ ካሊማ በበኩላቸዉ ችግሩን ለመግታት ከዚህም በላይ ሊሠራ ይገባል ይላሉ፤
«መንግስትን ችግሩን ለመቆጣጠር እና ሴቶችም ራሳቸዉን የቻሉ እንዲሆኑ የሚረዳ ሕግ እስከሌለዉ ድረስ ነገሩ እየተባባሰ ሲሄድ ማየታችን አይቀርም። መንግስት ሴቶችን ለዚህ ተግባር የሚያጋልጡትን ሰዎች እንዲገታ ብቻ ሳይሆን ለጥቃት የተጋለጡ ናቸዉና ለእነሱ የሚሆን ነገርም እንዲያሰናዳ እንጠይቀዋለን።»
በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም ዛምቢያ ዉስጥ ስላለዉ የሰዎችን ሕገወጥ ዝዉዉር የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ያወጣዉ ዘገባ የአገሪቱ መንግስት የወንጀል ድርጊቱን ለመከላከል ጥረት ለማድረግ ቢሞክርም እንኳ ሙሉ በሙሉ ያንን ማድረግ የሚያስችለዉን ደረጃ እንዳላሟላ አሳይቷል።

ካቲ ሲኮምቤ

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic