ህዝባዊ ተቃውሞ በቱርክ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ህዝባዊ ተቃውሞ በቱርክ

በቱርክ ዐብይ ከተማና የንግድ ማዕከል በኢስታንቡል በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ረችብ ታይብ ኤርዶጋን ስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ። ባለፈዉ ሳምንት መጠናቀቅያ ላይ በቱርክ የታየዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ከአስር አመት ወዲህ የመጀመርያዉ እንደሆንም ተነግሮአል።

በቱርክ መዲና አንካራ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጢስ ተጠቅሞአል። የአዉሮጳዉ ህብረት ፖሊስ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ የወሰደዉን እርምጃ አዉግዞአል፤  

በኢስታንቡል ቱርክ በሚገኝ የመዝናኛ ፓርክ ዉስጥ ለቀናቶች የሰፈሩ የተቃዎሞ ሰልፈኞችን በሳምንቱ መጠናቀቅያ የጸጥታ ፖሊስ  ለመበተን ባደረገዉ ጥረት በርካቶች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸዉ ተነግሮአል። በኢስታንቡል «ጌዚ» የተሰኘዉ የመዝናኛ ፓርክ ፈርሶ የንግድ ማዕከል ግንባታ ስራ እንዲካሄድ  መንግስስት የወጣዉን ትእዛዝ በመቃወም በርካታ ተቃዋሚዎች፤ ለቀናቶች ማደርያ መዋያቸዉን ፓርክ ዉስጥ በማድረጋቸዉ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ራችብ ኦርዶጋን ተቃዋሚዎች በሃይል ከቦታዉ እንዲነሱ በማዘዛቸዉ ነበር ባለፈዉ ሳምንት አርብ ምሽት በተቃዋሚዎች እና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የተነሳዉ ግጭት የጠነከረዉ።

ፖሊስ በፓርኩ የሰፈሩትን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከቦታዉ ለማስነሳት ዉሃ በመርጨት እና  አስለቃሽ ጋዝን ተጠቅሞአል። አርብ ምሽት የቀተቀሰቀሰዉ ግጭት ቅዳሜ ዕለትም  በኢስታንቡል ታክዚም በሚባል አደባባይ እና ጌዚ የመዝናኛ ፓርክ አቅራብያ በፖሊስ እና በተቃዋሚ ሰልፈኞች መካከል ቀጥሎ ነበር የዋለዉ፤ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ፤ የመዝናኛ ፓርኩ እንዳይፈርስ ብሎም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ራችብ ኤርዶጋን ስልጣን እንዲለቁ ይጠይቃሉ።  አንድ የኢስታንቡል ነዋሪ እንደተናገሩት

«ፖሊስ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ነዉ የጣለዉ፤ በእዉነቱ ከሚገባዉ በላይ የሆነ ጥቃት ነዉ። በእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ ፖሊስ ህዝቡን በጠበቅ እና መከላከል ነበር የነበረበት»

ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶጋን የፀጥታ አስከባሪዎች በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ስህተት መሆኑን ቢቀበሉም፤ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ስርዓት አልባ የሆኑ  የዲሞክራሲ ጠላቶች ናቸዉ ሲሉ ኮንነዋል።

«ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ መሪት ላይ የተነጠፈዉን  የተጠረበ ድንጋይ ፈነቃቅለዉ የሱቅ መስኮቶች ላይ ወርዉረዋል። እና ይህ ዴሞክራሲ ነዉ? ራችብ ታይብ ኤርዶጋን አንባገነን ነዉ ብለዋል። ለህዝቡ ምቾት የሚሰራዉን ሰዉ ነዉ፤ አንባገነን  ብለዉ ከጠሩ የምለዉ ነገር አይኖርም»

በኢስታንቡል በሚገኘዉ የመዝናኛ ፓርክ፤ ትናንት እሁድ፤ ከብጥብጥ ይልቅ ሰላም ነግዞ ነዉ የዋለዉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች፤ በመዝናኛ ፓርኩ የሚበላ የሚጠጣ በማምጣትና ሙዚቃን በመክፈት ባለፉት ቀናት የነበረዉን ሃይል የቀላቀለ ብጥብጥ እና የተቃዉሞ ሰልፍ ፊቱን እንዲቀይር ለማድረግ ሞክረዋል። በመዝናኛ ፓርኩ አቅራብያ ያለዉ ክፈለ ከተማ ነዋሪዎች ጌዚ ፓርክ ተነስቶ ለንግድ ማዕከል የሚሆን ግንባታ ስራ እንዳይደረግ ትግላቸዉን ቀጥለዋል። ይኸዉም ታኪዚም አደባባይ ላይ መንገድን በአትክልት፤ በአግዳሚ ወንበር እና በአዉቶቡስ በመከለል ፖሊስ ወደ ስፍራዉ እንዳይገባ ከልለዋል። በኢስታንቡል መሃል ከተማ የህዝቡ ቁጣ እንዳየለ ነዉ። በኢስታንቡል በተቃዋሚ ሰልፈኞች እና ፖሊስ መካከል የደረሰዉን ብጥብጥ ተከትሎ በቱርክ ትላልቅ ከተሞች ማለት አንካራ እና ኢዝሚር በተቃዋሚዎች እና በጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች መካከል ብጥብጥ መቀስቀሱም ተነግሮአል። በፖሊስ እና በተቃዋሚ ሰልፈኞች መካከል በደረሰዉ ዉጥረት በተከሰተዉ አደጋ እስካሁን የስምንት ሚሊዮን ይሮ ንብረት መዉደሙን የቱርክ የአገር ዉስጥ ሚኒስትር ሙአመር ጉሊየር ይፋ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በብጥብጡ የደረሰዉን የንብረት መጥፋት ምክንያት በማየት የተቃዋሚ ወገኖች የሚቃወሙ የኢስታንቡል ነዋሪዎችም አሉ፤

«አላስፈላጊ የሆነ የተቃዎሞ ሰልፍ ነዉ። አንድ ሰዉ የማይፈልገዉን ነገር ለማሳየት ወይም ለመናገር ከፈለገ ሌላ ሌላ ፍላጎትን የሚገልጽበት ዘዴ አለ። እኔ እንደሚመስለኝ እዚህ የታየዉ ሁሉ ትክክለኛ ነገር አይደለም »   

የቱርኩን ጠቅላይ ሚኒስትር ራችብ ኤርዶጋንን በመቃወም በቱርክ በተለያዩ ከተሞች የተቃዎሞ ሰልፍ  ቢቀሰቀስም ጠቅላይ ሚኒስትር ራችብ ኤርዶጋንን  ዉጭ ሃገራትን  ለመጎብኘት ቀደም ሲል የያዙትን ቀጠሮ ጀምረዋል። ኤርዶጋን ከሚጎበኝዋቸዉ አገሮች መካከል ሞሮኮ እና አልጀርያ ሲገኙበት ጉብኝታቸዉን የፊታችን ሃሙስ አጠናቀዉ ወደ አገራቸዉ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።  

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic