ህወሓት ጤና ተቋማት ላይ አደረሰ የተባለው ጥፋትና ዝርፊያ  | ኢትዮጵያ | DW | 31.08.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ህወሓት ጤና ተቋማት ላይ አደረሰ የተባለው ጥፋትና ዝርፊያ 

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ህወሓት በወረራ በቆየባቸው ቀናት «የጤና ተቋማትን በማውደሙና በመዝረፉ ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል» ሲሉ ባለሞያዎችና የአካባቢው ባለስልጣናት አመለከቱ። ተቋማቱን ሥራ ለማስጀመር በትጋት እየተሠራ እንደሆነም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00

ብርቱ ውድመት ተከስቷል

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ህወሓት በወረራ በቆየባቸው ቀናት «የጤና ተቋማትን በማውደሙና በመዝረፉ ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል» ሲሉ ባለሞያዎችና የአካባቢው ባለስልጣናት አመለከቱ። ተቋማቱን ሥራ ለማስጀመር በትጋት እየተሠራ እንደሆነም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። 

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ጉና ቤጌምድር ወረዳ ጤና ጣቢያዎች ህወሓት ወደ አካባቢው በመጣበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በመጎዳታቸውና በመዘረፋቸው ኅሙማን ሕክምና ማግኘት እንዳልቻሉ ነዋሪዎቹ ተናግራዋል። የወረዳው የጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አቶ ግርማ ደምሌ በስልክ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት የየጤና ጣቢያው መድኃኒቶች ተዘርፈዋል፣ ሆን ተብሎ እንዲበላሹም ተደርገዋል። እንደ አቶ ግርማ ከመድኃኒት ዝርፊያና ብልሽቱ በተጨማሪ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የጤና ጣቢያዎቹ መሳሪያዎችም በተመሳሳይ እንዳይሰሩ ተደርገዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ ተወስደዋል ብለዋል።

በዚሁ ዞን የነፋስ መውጫ ሆስፒታልም በደረሰበት ውድመት ከነሐሴ 6 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ መጀመር እንዳልቻለ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃን ሙሉ ገልጠዋል። አንድ የነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪ በሆስፒታሉ መደኃኒት ባለመኖሩ ሌላ ቦታ እንዳስመጡ አመልክተዋል። የደቡብ ጎንደር ዞን የጉና ቤጌምድር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢምረው መውደድ በበኩላቸው ህወሓት በወረዳው በቆየባቸው ቀናት ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት አካሂዷል ብለዋል። በገጠርና በከተማ ያሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ዘርፏል፣ ባንኮችንና አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ሰነድ አበላሽቷል፣ የቢሮ ኮምፒዩተሮችንና ተሸከርካሪዎችን ዘርፏልም ነው ያሉት። በአጠቃላይ ተቋማት አገልግሎት ከሚሰጡበት ደረጃ ላይ እንዳልሆኑ አስረድተዋል። 

ተቋማቱን ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ቢሆንም በተለይ የአሌክትሪክ ብልሽቱ ከባድ በመሆኑ ሥራውን አድካሚ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። የነፋስ መውጫን ሆሰፒታል ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ርዳታ ከዩኒቨርሲቲዎች ማግኘታቸውን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሐን ገልጠዋል። በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት በተለይ ለወላጅ እናቶች ፈተና መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመው፣ ያለባለሞያ እገዛ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው በቤት ውስጥ እንዲወልዱ እየተገደዱ መሆኑንም አመልክተዋል። በአጠቃላይ ቡድኑ በዞኑ የፈፀመው ጥፋት ከፍተኛ በመሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ባለስልጣናቱ ጥሪ አቅርበዋል።


ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ 
 

Audios and videos on the topic